እርባ ቅምር

መምህር በትረማርያም አበባው
ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ላይ ‹‹ንዑስ አገባብ›› በሚል ርእስ አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ስለ ‹‹እርባ ቅምር›› እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!

የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ!
፩. እንቋዕ ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አብጽሐክሙ
፪. አሌ ለነ
፫. አንትሙሂ ተሐውሩ ግድመ ግድመ
፬. ሰማይ ወምድር የኀልፍ
፭. ነዋ ወልድኪ ነያ እምከ

የጥያቄዎች መልሶች
፩. እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ።
፪. ወዮልን
፫. እናንተም አግድም አግድም ትሄዳላችሁ።
፬. ሰማይና ምድር ያልፋል።
፭ እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ

የሚከተሉትን የአማርኛ ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ተርጉሙ!
፩. ሞት ሳይመጣ እንዋደድ
፪. ስምህ ማን ነው?
፫. የጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው?
፬. ዕድሜህ ስንት ነው?
፭. ከትላንት እስከዛሬ

የጥያቄዎች መልሶች
፩. ንትፋቀር እምቅድመ ይምጻእ ሞት
፪. መኑ ስምከ?
፫. አይቴ ብሔራ ለጥበብ?
፬. ስፍን መዋዕሊከ
፭. እምትማልም እስከ ዮም

እርባ ቅምር
እርባ ቅምር የሰዋስወ ግእዝን አጠቃላይ አዋጅ የምንማርበት ትምህርት ነው። በጠቅላላ ሰዋስው በሁለት ይከፈላል። እነዚህም ዘር እና ነባር ናቸው። ዘር የሚባሉት ከግሥ የሚወጡ ስሞች፣ ቅጽሎች እና ሌሎችም እርባታዎች ናቸው። ነባር የሚባሉት ደግሞ ከግሥ የማይወጡ አገባቦች፣ ስሞች፣ የሀገር የቦታ እና የሰው ስሞች እንዲሁም ቀዳማይ እያላቸው ካልዓይ ሣልሳይ የሌላቸው አንቀጾች ናቸው።

አዋጅ ፩
ሳቢ ከተሳቢ ዘርፍ ከባለቤት በሁለት ነገር ይያያዛል። እኒህም ‘ለ’ እና ‘ዘ’ ናቸው።’ዘ’ በንዑስ አንቀጽ ሲነገር ብሂል ዘጊዮርጊስ ይባላል። ‘ለ’ በንዑስ አንቀጽ ሲገባ ብሂሎቱ ለጊዮርጊስ ይባላል። ብሂሉ ለጊዮርጊስ ወይም ብሂሎት ዘጊዮርጊስ ግን አይባልም። ዘርፍ ከባለቤት የሚባለው መናበብ የሚችል ሁሉ ነው። ንዋዩ ለባዕል፣ ንዋይ ዘባዕል፣ ንዋየ ባዕል ሦስቱም አንድ ዓይነት ትርጉም አለው። የሀብታም ገንዘብ ማለት ነው። ከዘ በተጨማሪ “እለ እና እንተ” ዘርፍ ያያይዛሉ። “እንተ” ከብዙ ወደ አንድ፣ ከአንድ ወደ አንድ ያያይዛል። ለምሳሌ ሰማይ እንተ አምላክ፣ አምላክ እንተ ሰማያት ይባላል። “እለ” ከአንድ ወደ ብዙ ከብዙ ወደ ብዙ ያያይዛል። ለምሳሌ መላእክት እለ አምላክ፣ መላእክት እለ ሰማያት ይባላል። “ዘ” እና “ለ” ግን ሁሉንም ያያይዛሉ። የ”ለ” የዘርፍ ዘርፍ ድፋት የለውም። አስካለ ወይነ ቄርሎስ ለማለት ለቄርሎስ አስካለ ወይኑ አይልም። ቤታ ለማርያም፣ ለማርያም ቤታ፣ ቤት ዘማርያም፣ ዘማርያም ቤት፣ ቤተ ማርያም ቢል ተማሳሳይ ነው ትርጉሙ ሁሉም የማርያም ቤት ማለት ነው። ቤተ ማርያም ሲል ማርያም የቤት ዘርፍ ይባላል። ቤት ዘማርያም ሲልና ቤታ ለማርያም ሲል “ለ እና ዘ” ዘርፍ አያያዥ ይባላሉ። ዘማርያም ቤት ሲልና ለማርያም ቤታ ሲል ደግሞ “ለ እና ዘ” ዘርፍ ደፊ ይባላሉ።

አዋጅ ፪
የግሥ መነሻ ፊደላት መራኁት ይባላሉ። መራኁት አምስት ናቸው። እነዚህም ግእዝ፣ ራብዕ፣ ኃምስ፣ ሳድስ እና ሳብዕ ናቸው። በግእዝ ቀደሰ፣ በራብዕ ባረከ፣ በኃምስ ሴሰየ፣ በሳድስ ክህለ፣ በሳብዕ ጦመረን የመሳሰሉ ናቸው። ከእነዚህ በቀር ግሥ በካዕብ እና በሣልስ አይነሳም። የግሥ መድረሻዎች ሁለት ናቸው። እነዚህም ግዕዝና ኃምስ ናቸው። በግእዝ ከ ‘ሀ’ እስከ ‘ፈ’ ያሉ ግሦች ናቸው። በኀምስ ግን ይቤ ብቻ ነው። ‘ይቤ’ም ነባር አንቀጽ ይባላል።

አዋጅ ፫
“ወ” እስከ ሦስት ያወርዳል። ይህም ማለት ለምሳሌ ዘሐመ ወሞተ ወተቀብረ ወተንሥአ ይባላል። ይህም ዘሐመ ወዘሞተ ወዘተቀብረ ወዘተንሥአ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ትርጉም አለው። ‘ዘ’ ለሦስቱ ማለትም ለሞተ፣ ለተቀብረ እና ለተንሥአ እንደወረደችላቸው አስተውሉ! በዋዌ የማይወርዱ ቀለማት ሦስት ናቸው። እነዚህም “ሀ፣ ከ፣ ዊ” ናቸው። ጸውዐ ሙሴሀ ወአሮን አይልም። ሙሴንና አሮንን ጠራ ለማለት የግድ ወአሮንሀ መባል አለበት። አምላክ ሰማያዊ ወምድራዊ ይባላል እንጂ “ወ” ያወርድልኛል ብለን አምላክ ሰማያዊ ወምድር አንልም፡፡ “ወ” ሦስቱን ማለትም “ዊ፣ሀ፣ከ” ን አያወርድምና። በላዕነ ሥጋከ ወሰተይነ ደመከ ይባላል እንጂ ወሰተይነ ደመ አይልም።

አዋጅ ፬
ሳይጠሩ የሚያስሩ ሦስት ናቸው። እነዚህም ውእቱ፣ ሀለወ እና ደለወ ናቸው። ለምሳሌ አምላክ ሀያል ብሎ አምላክ ሀያል ነው ይላል። “ነው” የሚለውን ፍች ያመጣው “ውእቱ” ሳይጠራ (ሳይጻፍ) ነው። አነ በአብ ሲል ትርጉሙ እኔ በአብ አለሁ ማለት ነው። “አለሁ” የሚለውን ያመጣው “በ” ነው። ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ስንል ትርጉሙ ለአብ ምስጋና ይገባል! ለወልድ ምስጋና ይገባል! ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል! ማለት ነው። “ይገባል” የሚለውን ትርጉም ያመጣው “ለ” ነው። ተጠርተው የሚያሥሩ ሦስት ናቸው። እነዚህም ቀዳማይ አንቀጽ፣ ካልዓይ አንቀጽና ሣልሳይ አንቀጽ ናቸው።

አዋጅ ፭
ባዕድ ቀለማት ሦስት ናቸው። እነዚህም “መ፣ተ፣አ” ናቸው። ከእነዚህም ‘መ’ ከግእዝ እስከ ሳብዕ ይነገራል። ‘መ’ ሲገባ ቀደሰ ብሎ መቅደስ፣ ‘ሙ’ ሲገባ ወረደ ብሎ ሙራድ፣ ‘ሚ’ ሲገባ ነሐሰ ብሎ ሚንሓስ፣ ‘ማ’ ሲገባ ኀደረ ብሎ ማኅደር፣ ‘ሜ’ ሲገባ ተኬነው ብሎ ሜኮኖት፣ ‘ም’ ሲገባ ቆመ ብሎ ምቅዋም፣ ‘ሞ’ ሲገባ ወፀፈ ብሎ ሞፀፍ ይላል። ‘ተ’ በግእዝ፣ በራብዕ፣ በኃምስ እና በሳድስ ይነገራል። ‘ተ’ ሲገባ ወደሰ ብሎ ተውዳስ፣ ‘ታ’ ሲገባ ኀሠሠ ብሎ ታኅሣሥ፣ ‘ቴ’ ሲገባ ረግዐ ብሎ ቴሮጋ፣ ‘ት’ ሲገባ ሐረመ ብሎ ትሕርምት ይላል። ‘አ’ በግእዝና በሳድስ ይነገራል። ‘አ’ ሲገባ መሰለ ብሎ አምሳል፣ ሠገረ ብሎ እግር ማለቱን ያሳያል።

አዋጅ ፮
ከቀዳማይ አንቀጽ ላይ በባዕድነት እየተጨመሩ ካልዓይ አንቀጽን፣ ዘንድ አንቀጽን እና ትእዛዝ አንቀጽን የሚያስገኙ ፊደላት አሥራው ይባላሉ። እነዚህም አራት ናቸው። “ተ፣ነ፣አ፣የ” ናቸው። እነዚህም በአመል ሲገቡ ግእዝ፣ ራብዕ ይሆናሉ። ያለ አመል ሲገቡ ሳድስ ይሆናሉ። በግእዝ ሲገቡ አእመረ ብለን የአምር እንላለን። በራብዕ ሲገቡ አጽደልደለ ብለን ያጽደለድል እንላለን። በሳድስ ሲገቡ ቀደሰ ብለን ይቄድስ እንላለን። ‘ተ’ በይእቲ፣ በአንተ፣ በአንቲ፣ በአንትሙ፣ እና በአንትን ይገባል። ‘የ’ በውእቱ፣ በውእቶሙ፣ እና በውእቶን ይገባል። ‘አ’ በአነ ሲገባ ‘ነ’ ደግሞ በንሕነ ይገባል። አሥራው በሁለተኛ መደቦች ማለትም በአንተ፣ በአንትሙ፣ በአንቲ እና በአንትን በትእዛዝ አንቀጽ አይገኙም።

አዋጅ ፯
በአንተ ትእዛዝ ሁለት ቀለም ሆኖ በሳድስ የደረሰ ሥርዓተ ንባቡ ተጣይ ነው። ኩን፣ ሑር ተጣይ ናቸው ‘ለ’ እና ‘ኢ’ ግን ሥርወ ቀለሙን አውርደው ጥለው ያስነሱታል። አትቁም ለማለት ኢትቁም ይላል። ቁም ለማለት ደግሞ ለትቁም ይላል። ሑር ንባቡ ተጣይ ነው። ‘ወ’ ሲጨመርበት ወሑር ሲል ግን ሰያፍ ይሆናል።

አዋጅ ፰
የ ‘የ’ ራብዕ አመሉ ‘አ’ ባለበት ቀለም በአሉታ በአስደራጊና በአደራራጊ ከቀዳማይ እስከ ቦዝ ይገኛል። የአእመረ አሉታ ኢያእመረ፣ የአእምሮ አሉታ ኢያእምሮ፣ የአእሚሮ አሉታ ኢያእሚሮ፣ የአእማሪ አሉታ ኢያእማሪ፣ ማለቱን አስተውሉ!

አዋጅ ፱
አራት ዓይነት ስሞች አሉ። እነዚህም የባሕርይ ስም፣ የግብር ስም፣ የተቀብዖ ስም እና የተጽውዖ ስም ናቸው። የተጸውዖ ስም የሚባለው መጠሪያ ስማችን ነው። ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ኤልያስ፣ የመሳሰሉት ናቸው። የግብር ስም የሚባለው ወታደር፣ ዶክተር፣ ተማሪ፣ ገበሬ የመሳሰሉት ናቸው። የተቀብዖ ስም የሚባለው ስንጠመቅ ስንሾም የምንሰጠው ስም ነው። ይህም ወለተ ሐና፣ ወልደ ሩፋኤል የመሳሰለው ነው። ጳጳሳት ሲሾሙ የተሰጣቸው ስምም ከዚህ ይመደባል። አቡነ ዲዮናስዮስ፣ አቡነ ማትያስ ወዘተ ነው። የባሕርይ ስም ለፈጣሪ ይነገራል። ለፍጡርም ሰው፣ እንስሳት፣ ወፍ ወዘተ የባሕርይ ስም ይባላል። የመድበል ስም የሚባልም አለ። እስራኤላውያን በይሁዳ አይሁድ፣ በያዕቆብ እስራኤል፣ ተብለዋል። በገቢር ጊዜ ይሁዳሀ፣ እስራኤልሀ ይባላል። የመድበሉ ግን አይሁደ፣ እስራኤለ ይባላል። በሱራፊ ሱራፌል፣ በኪሩብ ኪሩቤል ይባላል። ይህም ገቢር ሲሆን ኪሩቤለ ሱራፌለ ይላል።

አዋጅ ፲
ሰሚዎች አራት ናቸው። እነዚህም አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ እና አንትን ናቸው። ለምሳሌ አፍቀርከ ጽድቀ እግዚኦ ስንል አቤቱ እውነትን ወደድክ ይባላል። በዚህ “አንተ” ሰሚ ሆኖ የተነግረ ነው። አሰሚዎች ደግሞ አራት ናቸው። እነዚህም አንቀጽ፣ አገባብ፣ ዘርፍ እና ባለቤት ናቸው። የአንቀጽ ሰሚ ከፈቀደው ሆኖ ይሰማል። አፍቀርከ ጽድቀ እግዚኦ፣ እግዚኦ አፍቀርከ ጽድቀ ይላል። የአገባብ፣ የዘርፍና የባለቤት ሰሚዎች ግን ወይ በመጀመርያ ወይ በመጨረሻ ይሰማሉ። አምላክ ደምከ ውሕዘ ሲል የባለቤት ሰሚ፣ አምላክ ደመ ገቦከ ውሕዘ ስንል የዘርፍ ሰሚ፣ መንግሥተ ሰማይ መጽኡ ጻድቃን ኀቤኪ ሲል የአገባብ ሰሚ ይባላል።

አዋጅ ፲፩
ዘርፍ ይዘው፣ አገባብ ወድቆባቸው ወደፊት እንጂ ወደኋላ የማይስቡ አራት ናቸው። እነዚህም ሳቢ ዘር፣ ንኡስ አንቀጽ፣ ሣልስ ቅጽል እና ሳድስ ቅጽል ናቸው። በሳቢ ዘር ሰማየ ለዕርገት ኤልያስ ተግሀ አይልም። ለዕርገት ሰማየ ኤልያስ ተግሀ ይላል እንጂ። ይህ አገባብ ወድቆበት ነው። ዘርፍ ይዞም ሰማየ ዕርገተ ኤልያስ ተዐውቀ አይልም። ዕርገተ ኤልያስ ሰማየ ተዐውቀ ብንል እንጂ በንዑስ አንቀጽ ገነተ ለበዊእ ጻድቃን ተግሁ አንልም። ለበዊእ ገነተ ጻድቃን ተግሁ ይላል እንጂ ገነተ በዊአ ጻድቃን ተዐውቀ አይባልም። በዊአ ጻድቃን ገነተ ተዐውቀ ይባላል እንጂ በሣልስ ቅጽል ምሥጢረ ለአእማሪ ጴጥሮስ ጸውዖ እግዚአብሔር አይልም። ለጴጥሮስ አእማሪ ምሥጢረ ጸውዖ እግዚአብሔር ይላል እንጂ ምሥጢረ አእማሬ ልብ ጴጥሮስ ተጸውዐ አይልም። ጴጥሮስ አእማሬ ልብ ምሥጢረ ተጸውዐ ይላል እንጂ በሳድስ ቅጽል በኀበ እስራኤል ለክቡር ዳዊት አንገሦ ሳሙኤል አይባልም። ለዳዊት ክቡር በኀበ እስራኤል አንገሦ ሳሙኤል ይላል እንጂ በኀበ እስራኤል ክቡረ መንግሥት ዳዊት ነግሠ አይልም። ዳዊት ክቡረ መንግሥት በኀበ እስራኤል ነግሠ ይላል እንጂ፡፡

አዋጅ ፲፪
በዝርዝር ጊዜ ለገቢር ለተገብሮ የሚችሉ አራት ናቸው። እነዚህም የውእቶሙ፣ የይእቲ፣ የውእቶን እና የአነ ዝርዝር ናቸው። ይኸውም ሐነጹ ቤቶሙ፣ ተሐንጸ ቤቶሙ፣ ሐነጸት ቤታ፣ ተሐንጸ ቤታ፣ ሐነጽኩ ቤትየ፣ ተሐንጸ ቤትየ፣ ሐነጻ ቤቶን፣ ተሐንጸ ቤቶን ይላል።

የመልመጃ ጥያቄዎች
፩) የአግመረ አሉታ ማን ነው?

፪) ተንሥኡ ለጸሎት ከሚለው
ሀ) ሰሚው ማን ነው?
ለ) አሰሚው ማን ነው?

፫) ማኅበረ ቅዱሳን የሚለውን ተናባቢ ቃል በለ እና በዘ በዘርፍ አያያዥና በዘርፍ ደፊ ጻፍ?

፬) መስቀል ኃይልነ በሚለው ቃል ሳይጠራ ያሰረ ማን ነው?

፭) የሚከተሉትን ቃላት ሥርዓተ ንባባቸውን ለዩ!
ሀ) ባእ
ለ) ለትባእ

፮) የሚከተሉትን ቃላት ገቢራቸውን አውጣ?
ሀ) መላእክትየ
ለ) ኅብስትከ
ሐ) ሀገሮሙ

፯) የ “አርኂዎ” አሉታ ማን ነዉ?

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!