አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማሰብ ትርጉም አልባ ነው!

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

የካቲት ፳፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

የየካቲት ወር በኢትዮጵያውያን ዘንድ በብዙ መልኩ የሚታሰብ ወር ነው፡፡ ከአድዋ ድልና “ከሰማዕታት” መታሰቢያ በዓላት ጋር ተያይዞ አዎንታዊም አሉታዊም ስሜቶች እየተፈራረቁባቸው የሚያሳልፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ አድዋ የካቲት ፳፫ ቀን ፲፰፻፹፰ ዓ.ም በአድዋ ተራራ ላይ ጥቁር ሕዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የማይቻል የሚመስለውን የቻሉበት፣ አይሆንም የተባለው የሆነበት፣ “ነጮች” “በጥቁሮች” የተሸነፉበት፣ ታላቅ ሁነት የተፈጸመበት፣ የድል በዓል መታሰቢያ ሲሆን የካቲት ፲፪ ቀን ፲፻፳፱ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የማይረሳ ሌላኛው ዕለት ነው፡፡ እርሱም ጣሊያን ከ፴ ሺህ የሚበልጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በግፍ የጨፈጨፈበት መታሰቢያ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ልናየው የወደድነው ግን የአድዋን የድል ታሪክና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ምን ያገናኛቸዋል? የሚለውን ነው፡፡ የአድዋን ድል ልዩ ያደረገው አንድ ሕዝብ በጦር ሜዳ ተዋግቶ ያሸነፈበት ታሪክ ስለ ሆነ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ዓለምን የተቆጣጠረውን “ጥቁር ሕዝብ ተፈጥሮውም፣ ኑሮውም ነጭን ለማሸነፍ አያስችለውም” የሚልና እንኳን ገዥዎችን ተገዥዎችንም ጭምር አሳምኖ የነበረ አስተሳሰብን የሻረ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለት ለንጽጽር የማይገቡና ያልተመጣጠነ አሰላለፍ የነበራቸው ሕዝቦችና መንግሥታት ተዋግተው እንደ ጎልያድ በሰይፍ የመጣው ሳይሆን እንደ ዳዊት በእምነት ጠጠር የወነጨፈው ያሸነፈበት የማይታመን እውነታ በመሆኑም ነው፡፡
በአድዋ እንዴት ልናሸንፍ ቻልን?

የቤተ ክርስቲያናችን አስተዋጽኦ የሚገለጠው “እንዴት አሸነፍን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስንመረምር ነው፡፡ ይህ ዓለምን በብርቱ ጠፍንጎ የያዘና አንዱን ባሪያ ሌላውን ጌታ የሚያደርግ፣ ሰውን ያህል ፍጡር እንደ ከብት ነድቶ፣ እንደ ዕቃ ጎልቶ፣ ለገበያ አቅርቦ የሚሸጥ እኩይ አስተሳሰብ ከመሠረቱ የናደ፣ ነጻነት ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ለሌሎች ያሳየ፣ የአስተሳሰቡ ሰለባ የነበሩ ነጮችንም ያስደነገጠ ድል ኢትዮጵያውያን እንዴት ሊቀዳጁ ቻሉ? ዓቅሙና ብርታቱስ ከየት ተገኘ? ምዕራባውያን ያላቸው የሠለጠነ ወታደር፣ የጦር መሣሪያ ልዩነት እና ዓለምን የተቆጣጠረው “የነጮች” የበላይነት አስተሳሰብ እያለ የመግጠምስ ሞራሉና እምነቱ ከወዴት መጣ? ኢትዮጵያውያንን ከዚህ የአስተሳሰብና የሞራል ከፍታ ያደረሳቸው ገፊ ምክንያትስ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ስንጠይቅ መልሱ ቤተ ክርስቲያናችን ዘንድ ያደርሰናል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ብላ ያስተማረችው ትምህርት፣ በነገሥታቱ እና በሕዝቡ ላይ ያሳደረችው በጎ ተፅዕኖ፣ “የእኔም ጦርነት ነው፤ በህልውናዬ ላይ የመጣ ነው” ብላ በማሰብ ደወል ደውላ፣ ዐዋጅ ነግራ ታቦት ይዛ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆኗ ለኢትዮጵያውያን የአስተሳሰብ ከፍታ የነበራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በእግዚአብሔር የሚያምኑ፣ የካህናትን ትእዛዝ የሚቀበሉ፣ እግዚአብሔርን መፍራትንና ንጉሥ ማክበርን የሚያውቁ፣ መመካት ቢገባቸውም ምሕረትን፣ ፍርድንና ጽድቅንም በምድር ላይ በሚያደርገው በእግዚአብሔር እንጂ በጉልበት፣ በሠራዊት ብዛት፣ በመሣሪያ ጥራት እንዳልሆነ ሲሰበኩ የኖሩ፣ ይህን እውነትም በልባቸው የጻፉ ስለ ነበሩ ነው፡፡ (ኤር.፱፥፳፬)

የአድዋ አርበኞች “እኛኮ ዘመናዊ ትጥቅ የለንም፤ እኛኮ “ጥቁሮች” ነን፤ “ነጭን” ማሸነፍ አንችልም፤ እኛኮ እንበርበት አውሮፕላን፣ እንሽከረከርበት አውቶሞቢል የለንም፤ እንዴት እናሸንፋለን? እንዴትስ ይቻለናል?” የሚል ጥያቄ በፍጹም አልጠየቁም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኀ ሠራዊቱ ወያርብኅኒ በብዝኀ ኃይሉ….፤ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፤ ኀያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም›› የሚል ትምህርትን ያስተማረችው፣ የእምነት ስንቅም ያስቋጠረችው ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡ (መዝ.፴፪፥፲፮) ብዙዎች የሚዘነጉት ጉዳይ ጦርነትን የሚያሸንፈው የሠራዊት ብዛት፣ የመሣሪያ ጥራት ብቻ ስለሚመስላቸው ነው፡፡

ይህ የአስተሳሰብ ችግር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ረጅም ዘመናትን የተሻገረ፣ አሁንም ድረስ ያልተቀረፈ አስተሳሰብ ነው፡፡ ብዙ ሰው መግደል ማለት ጦርነትን ማሸነፍ ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ሠራዊት ያላቸው፣ ብዙ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሁሉ ብዙ ሰው ይገድሉ ይሆናል እንጂ ጦርነትን ያሸንፋሉ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ አሸናፊነት፣ እውነተኛ ድል የሚገኘው እግዚአብሔርን ከሚያምን ንጉሥ፣ እግዚአብሔርን ከሚያምኑ ሠራዊት ወይም ከእውነተኛ ተዋጊዎች ነውና፡፡ ድል የሚነሡት ‹‹ድል መንሣት ዕውቀትም ካንተ ይገኛል፤ ጌትነትም ያንተ ገንዘብ ነው፤ እኔም ያንተ ባሪያ ነኝ›› የሚሉ ነገሥታትና ሠራዊት ናቸውና፡፡ (ዕዝ.ካልእ ፬፥፶፱)

ጣሊያን መካናይዝድ ጦር አሰልፎ፣ የሠለጠነ ሠራዊት አሰማርቶ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን ትጥቆች ታጥቆ በባዶ እግራቸው በሚሄዱት፣ ሰይፍና ጎራዴ በታጠቁት ሊሸነፍ የቻለው ኢትዮጵያውያኑ ‹‹ድል መንሣት በእግዚአብሔር ኃይል ነው›› ብለው በመግጠማቸው ነው፡፡(፩ኛ መቃ.፳፩፥፫) ቁም ነገሩ ስለ ጣሊያን ሽንፈት ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያውያኑ አሸናፊነትና የሥነ ልቡና የበላይነት ምክንያቱን ማንሣት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን በእምነት፣ በሥነ ልቡና፣ በአብሮነት፣ የገነባችው ሰብእና አድዋ ላይ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ባለ ርእይ የነበሩ ሊቃውንቶቿ በጸሎት ተግተው፣ ራእይ አይተው፣ በቅኔያቸውና በስብከታቸው የጦርነቱን አይቀሬነት እየገለጹ፣ ዝግጅት እንዲደረግ እያሳሰቡና የሥነ ልቡና ግንባታ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ታሪክ መሥራታቸው ቤተ ክርስቲያን በአማኞቿ ላይ በሠራችው ሥራ በገነባቸው የሥነ ልቡና የበላይነትና የአሸናፊነት መንፈስ ነው፡፡

የሮም ካቶሊክ መሣሪያ ባርካ ለወረራ ልካለች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሠራዊቱን በጸሎት ባርካ ራስን፣ ሀገርን፣ ሃይማኖትን ለመከላከል ልካለች፤ ካቶሊክ በመሣሪያ ተማምናለች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በጸሎት ተማምናለች፤ እነርሱ በታንክ ሊያሸንፉ መጡ፤ እኛ በታቦት ልናሸንፍ ታቦት ተሸክመን ወጣን፤ እኛም አሸነፍን፤ እነርሱም ተሸነፉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር መታመንን አስተማረች፤ ካቶሊክ በሠራዊትና በመሣሪያ ታምኖ ለወረራ የሚሄድን ባርካ ሸኘች፡፡ እናም ምዕራባውያኑ እስከ ክፉ መሻታቸው ተሸነፉ፡፡ አሸናፊነት ከእግዚአብሔር ነውና፡፡ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ‹‹አንተ ከሠራዊታቸው ጋር በከሃሊነትህ አጠፋሃቸው፤ ቤተ መቅደስህን ያጎሳቁሉ ዘንድ የስምህ ጌትነት ማደሪያ የሆነች ደብተራ ኦሪትንም ያሳድፉ ዘንድ መክረዋልና በብረትም የመሠዊያህን ቀንዶች አፍርሰዋልና›› ይላል፡፡ (ዮዲት ፱፥፰)

ሌላኛው የአድዋ ድል ምክንያት ደግሞ ካህናቱ ዘምተዋል፤ ሊቃውንቱ ዘምተዋል፤ ታቦቱ ዘምቷል፤ በየድንኳኑ ሰዓታት እየቆሙ ቅዳሴ እየቀደሱ፣ የሚያቆርቡ ነበሩ፤ የሞቱ እየተፈቱ በጸሎትና በምሕላ፣ በሞራልና በስንቅ ንጉሡንና ሠራዊቱን እየተራዱ ብዙ ሥራ የሠሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡ የጦርነቱን ፍትሐዊነት፣ ለሃይማኖት፣ ለርስት፣ ለሚስት፣ ለልጅ ተብሎ የሚከፈል መሥዋዕትነት መሆኑን እና አሸነፊነት ደግሞ ከእግዚአብሔር መሆኑን፣ ቤተ ክርስቲያን አስተምራለች፤ አበረታታለች፤ ብዙዎቹም ሊቃውንትና ካህናት ከአርበኞች ጋር በግንባር ተሠውተዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፤ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ ይህም ለተዋጊዎች ኃይልና ብርታት ሰጥቷቸዋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል፤ ታሪክ አለ፡፡ ‹‹ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጎድጓድ አንጎደጎደ፤ አስደነገጣቸውም፤ በእስራኤል ፊት ድል ተመቱ›› ይላል የሚገርም ነው፡፡ (፩ኛ ሳሙ.፯፥፲) አድዋ ላይ የሆነውም ይህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትም በጦር ግምባር በድንኳን በቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርጉ፣ ንጉሡም ቅዳሴውን ሲያስቀድሱ፣ የልዳው ኮከብ የፋርሱ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣሊያኖቹ ላይ አንጎደጎደባቸው፤ አስደነገጣቸውም፡፡ በእነዚያ ልበ ሙሉዎች ጎራዴ ይዘው በመድፍ ፊት በሚቆሙ ደፋሮች ኢትዮጵያውያን ድል ተመቱ፡፡

እነሆ ዛሬ እኛ የድል አድራጊዎች ልጆች ተባልን፤ “ነጭም” “በጥቁር” ተሸነፈ፤ የነጻነትን ጣዕም ጥቁሮች ቀመሱ፤ የነጭ ፍልስፍና ተሻረ፤ ሰውን ያህል ፍጡር ባሪያ የሚያደርገው፣ አንዱን ገዥ ሌላውን ተገዥ የሚያስብለው የቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብም ታሪኩ በጥቁር መዝገብ ተጻፈ፤ ይህም ከሆነ እነሆ ፻፳፰ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ አባቶቻችን ድል አድርገው ታሪክ ሠሩ፤ እኛ ደግሞ ድል ማድረግ፣ ታሪክ መሥራት ቀርቶ ታሪክን መሸከም ከብዶን ለመውደቅ እንፍገመገማለን፡፡

አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዘከር የሚፈልግ ትውልድ መጣ፡፡ አድዋ ነጻነት ነው፤ አድዋ የሰው ልጆች የከፍታ፣ የእኩልነት ምልክት ነው፤ አድዋ የአሸናፊዎች ዓርማ ነው፡፡ አድዋ አንድነት የታየበት፣ የመለያየት ግንብ የፈረሰበት፣ ንጉሥ ከሠራዊቱ፣ ካህናት ከታቦቱ፣ ሳይለዩ በጋራ ለነጻነት የተሰለፉበት፣ የብርቱዎች ሰልፍ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የአድዋ ባለቤቶች ተገፍተዋል፤ ለፍላጎታቸው ባሪያ የሆኑ በተሸናፊው ጣሊያን ሐሳብ የተማረኩ፣ ኢትዮጵያዊ ሳሉ በግብራቸው ጣሊያናዊ የሆኑ አሸናፊዎቹን ሲሳደቡ የማይደነግጡ አንደበታቸው ያልተገራ፣ ውኃ የሌለባቸው ጉድጎዶች፣ ዝናብ አልባ ደመናዎች ዛሬ አገሩን ሞልተውታል፡፡

ታሪክ መሥራት አቀበት የሆነባቸው ታሪክንና ባለ ታሪኮችን የሚያዋርዱ፣ የድሉ መሐንዲስ፣ የጦሩ ፊታውራሪዎችን የሚያናንቁ፣ ድንቁርናቸው በሱፍና በከራባት የተሸፈነ ብዙዎች ዛሬ የአድዋ ባለውለታዎችን ያራክሳሉ፤ ቤተ ክርስቲያንንም ከአድዋ ነጥለውና ውለታዋን አቃለው ይናገራሉ፡፡ አይችሉም እንጂ ክብሯን ለመዳፈር፤ ልዕልናዋን ለዋረድ ይመረምራሉ፤ ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር እህል ላበደረ አፈር›› የሚሉት ብሂል ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፈጽሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከአድዋ ለመነጠል ጥረት ተደርጓል፡፡

በጥቅሉ አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አርበኞቿን አስተባብራ ባዕዳንን አሸንፋ ጠማማ ልጆቿን ማሸንፍ ተስኗታል፡፡ የሀገር አንድነትን የጠበቀች በአንድነት መቆም ርቋታል፡፡ ቁሳዊ ፍላጎቱን ያሸነፈ፣ ለእግሩ ጫማ ለሰውነቱ ሸማ የማይጨነቅ፣ ለሀገርና ለሃይማኖት ቅድሚያ የሚሰጥ ማኅበረሰብ የፈጠረች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የቁስ ፍላጎታቸው ጦር ሆኖ የሚወጋቸው አገልጋዮች ሞልተዋታል፡፡ ይህም ለታሪካዊ ጠላቶቿ በቀል በር የከፈተባት ትልቁ ክፈተት ነው፡፡

አድዋ አንድነት ነው፤ አድዋ እኩልነት ነው፤ አድዋ ነጻነት ነው፡፡ አድዋ የድሉ ባለቤቶችን መዘከር ነው፡፡ እነዚህን ዘንግቶ፣ የድሉ ፊታውራራዎችን በማንኳሰስ፣ የቤተ ክርስቲያንንም ሚና በመዘንጋት የሚከበር የአድዋ በዓል ትርጉም አልባና ታሪክን የማጥፋት ሴራ ነው፡፡