begena 16

አቡነ ጎርጎርዮስ የሥልጠና ማእከል የበገና ተማሪዎችን አስመረቀ

ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.

በታመነ ተክለ ዮሐንስ

begena 16የማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በዜማ መሣሪያ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች እሑድ ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም አስመረቀ፡፡ ማእከሉ በመደበኛ የትምህርት መርሐ ግብሩ የአስኳላ ትምህርትን የሚሰጥ ሲሆን፤ በማታ እና በእሑድ ቅዳሜ የሥልጠና መርሐ ግብሩ ደግሞ የአብነትና የዜማ መሣሪያዎችን ሥልጠና ያካሄዳል፡፡ በያዝነው ዓመት በማታው መርሐ ግብር ለተከታታይ ዘጠኝ ወራት ሲሰጥ በነበረው የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና 208 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ከ170 በላይ የሆኑት በበገና እንዲሁም ቀሪዎቹ 30 ደግሞ በመሰንቆ የሠለጠኑ ናቸው፡፡

በተቋሙ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብዮት እሸቱ እንደገለጹት “በትምህርት መርሐ ግብሩ የሚሰጡት የአብነት ትምህርቶች (ግዕዝና የቅዳሴ ተሰጥኦ) እንዲሁም የዜማ መሣሪያዎች (በገና፣ መሰንቆ፣ ዋሽንትና ከበሮ) ሥልጠና፤ በዋነኝነት ዓላማ አድርገው የያዙት የሠልጣኞቹን የመንፈሳዊ ሕይወት ተመስጦ ለማሳደግ ሲሆን፤ በተያያዥነትም ወደቀጣዩ ትውልድ የሚደረገውን  የመንፈሳዊ ቅርስ የቅብብል መንገድ ለማጠናከር ነው” ብለዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ከምረቃ በኋላ በ2003 ዓ.ም በተመሠረተው የበገና ቤተሰብ ማኅበር በመታቀፍ ጥምቀትን በመሰሉ ታላላቅ መንፈሳዊና የሕዝብ ክብረ በዓላት ላይና በሌሎች ወሳኝ መድረኮች ላይ የበገና አገልግሎትን ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ካለው የአቅም እጥረት እና የጥያቄ ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት ለምእመናኑም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ማበርከት እንዳልተቻለ አሳውቀዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ “የትምህርትና የሥልጠና ዘርፉን በመምህራን ከማጎልበት አንጻር የመምህራን የትምህርት ማስረጃ የተሟላ ካለመሆን የተነሣ የበገና መምህራን እጥረት የሚታይ ሲሆን፤ እንደመፍትሄ እየተወሰደ ያለ እርምጃ ቢኖር ከምሩቃን መካከል የላቀ ብቃት ያሳዩትን በመምረጥና ልዩ ሥልጠና በመስጠት ተተኪ መምህራንን የማፍራት ሥራ ነው” ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሌሎች የዜማ ትምህርት ዘርፎች መሰል ችግሮች እንደማይታዩ ገልጸው፤ ይልቁንም ከቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ቤት በሚወጡ መምህራን በመታገዝ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡ ማእከሉ ከያዘው የተደራሽነት  ዓላማ አንጻር ሥልጠናውን ለማንኛውም አካል በግልጽ የሚሰጥ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት አሥር ያህል የውጭ ዜጎች በበገና ላይ ያተኮረ ሥልጠና ወስደዋል፡፡

የሥልጠና ማእከሉ በቀጣይ የተደራጀ መዋቅር በመቅረጽ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና አስተምህሮ አንጻር የተፈቀዱትን የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና፤ የአብነት ትምህርትን በተጠናከረ መልኩ ለመቀጠልና ከተቋሙ የሚመረቁ ተማሪዎች ሕጋዊ የሆነ እውቅና እንዲያገኙ እንዲሁም ማእከሉን ወደ TVT ደረጃ ለማሳደግ ከትምህርት ሚኒስቴር እውቅናን ለመጠየቅ ተቋሙ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ሓላፊው  ባስተላለፉት መልእክት  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይ የሀገር ቅርስ የሆነውን የበገና ትምህርት ቢማር በመጪው ትውልድ ከሚመጣ ወቀሳ መዳን እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡