አስተርዮ ማርያም

ጥር ፳ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም

በዘመነ አስተርዮ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ የሆነበትና የአምላካችን አንድነትና ሦስትነት የተገለጠበት ብቻም ሳይሆን በጥር ፳፩ የከበረች እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የዕረፍት ቀን በመሆኑ “አስተርዮ ማርያም” በማለት በዓልን አናደርጋለን፡፡

የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ላይ ፷፬ ዓመታትን ከኖረች በኋላ መንፈስ ቅዱስ ባስገነዘባት መሠረት በክብር ዐርፋለች፡፡ የዚህን ዓለም መከራና ሥቃይ ለሰዎች ድኅነት የተቀበለችው ክብርት እናታችን በሥጋ ብትሞትም እንደ ልጇ ደግሞ በትንሣኤዋ ተነሥታለች፤ ይህም የሆነው በተቀደሰች ዕለት ነሐሴ ፲፮ ነው፡፡

እመ ብርሃን ከእናትና ከአባቷ ጋር ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ ፲፪ ዓመት፣ ከተወዳጁ ልጅዋ ጋር ፴፫ ዓመት ከሦስት ወር፣ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር ፲፭ ዓመት፣ በድምሩ ፷፬ ዓመት በዚህ በኃላፊው ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓመተ ምሕረት በክብር ዐርፋለች፡፡

ክርስቲያኖች በሙሉ ይህንን በዓል ልናከብር ይገባልና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትን ሠርታልናለች፡፡ “አስተርዮ ማርያም” በሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ የሚከበር በዓል በመሆኑ በሀገራችን ኢትዮጵያ እና በመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ማኅበረሰብ ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡ በዓሉን የምናከብረውም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከዚህ ዓለም ድካም ማረፍ በማዘከር ብቻ ሳይሆን አማላጅነቷና ተረዳኢነቷን በማሰብና ተስፋ በማድረግ ነው፡፡

ስለዚህም እመ ብዙኃን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዐሥራት ሀገሯን ኢትዮጵያን እንድታስባት፣ ለእኛም ለሕዝቦቿ ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ታሰጠን እንዲሁም ለነፍሳችን ድኅነትን ትለምልን ዘንድ ዕረፍቷን መዘከር ይገባል፡፡

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ አሜን!!!