addis yemeseraw bete

አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳም

 ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

addis yemeseraw beteበሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በቀይት ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር በጉዶ በረት አካባቢ የምትገኘውን ጥንታዊትና ታምረኛዋን ገዳም እንድንዘግብላቸው በተደጋጋሚ ቢሯችን በመምጣትና ስልክ በመደወል ቀጠሮ ያስያዙንን የርዕሰ አድባራት ወገዳማት ዳግሚት ፅዮን አዲስ ዓለም ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ ንቡረ ዕድ አባ ገብረ ሕይወት መልሴ ጋር በነበረን ቀጠሮ መሠረት ሚያዚያ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሌሊቱ 12፡30 ወደ አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳም ለመጓዝ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በር ላይ እና ላም በረት አካባቢ ከሚገኘው መናኸሪያ በር ተገናኝተናል፡፡

ሰላምታ ተለዋውጠን ንቡረ ዕድ በመስቀላቸው ባርከውን ጉዟችንን ለመቀጠል ስንዘጋጅ ንቡረ ዕድ “ጸሎት እናድርግ” አሉ፡፡ የዘውትር ጸሎት፣ የዕለቱን ውዳሴ ማርያም በማድረስ ጉዞው ተጀመረ፡፡ ሾፌራችን ኢንጂነር መኮንን ለቤተ ክርስቲያንና ለንቡረ ዕድ ካላቸው ፍቅርና አክብሮት የተነሣ ላንድ ክሩዘር መኪናቸውን ለአገልግሎት ይዘው የመጡ አባት ናቸው፡፡ በተገቢው ፍጥነትና ምቹ አነዳድ በሰሜን ሸዋ ይዘውን እየሄዱ ነው፡፡

leke lekawent astedadaryንቡረ ዕድን በረድእነት እያገለገሏቸው የሚገኙት ታናሽ ወንድማቸውን ቀሲስ እንግዳወርቅ መልሴ ድርሳናትንና ገድላትን እንዲያነቡ አዘዟቸውና እያደመጥን በየመሐሉ አቡነ ዘበሰማያት እየተሰጠን እየጸለይን ደብረ ብርሃን ከተማ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ቤት ደረስን፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤፍሬምና ንቡረ ዕድ የፍቅርና የአክብሮት ሰላምታ ተለዋውጠው የመጡበትን ሁኔታ አስረዷቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬምም ጸሎት አድርገው እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሁን ብለው ሸኙን፡፡ ደብረ ብርሃን ከተማ ሲጠብቁን የነበሩትን የቀይት ወረዳ ሊቀ ካህናት ቀሲስ ብርሃኑ ለገሠ እና ጸሐፊያቸውን ይዘን ጉዶ በረት ደረስን፡፡

በጉዶ በረት የሚገኙትን አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም የልማት ኮሚቴ አባላት እነ ዲ/ን ይስማን ይዘን ከጉዶ በረት በ6 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደምትገኘው አሰግድመኝ ማርያም የአስፋልቱን መንገድ በመልቀቅ የአምስት ቀበሌ ሕዝብ ጉልበቱን ሳይቆጥብ ቆፍሮ ያስተካከለውና አሁንም አስቸጋሪ የሆውን ጥርጊያ መንገድ ተያያዝነው፡፡ ወጣ ገባውን መንገድ ለማለፍና ለመኪናችን ክብደት ለመቀነስ በእግራችን መጓዙን በመምረጥ ከመኪናው ወርደን ተከተልናቸው፡፡

አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳም ስንደርስ የተመለከትነው ሰፊ ሜዳ ላይ በቆርቆሮ የተራች መቃኞ ሆና አገኘናት፡፡ ከአዲስ አበባ ስንነሳ ተነግሮን የነበረው ዋሻ ቤተ ክርስቲያን ስለነበር ግር አለን፡፡ ዋሻ ቤተ ክርስቲያኑን ከማየታችን በፊት መቃረቢያውንና አሁን በመገንባት ላይ የሚገኘውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንድንጎበኝ ተነገረን፡፡ ከመቃኞው አጠገብ መሠረቱ ከፍ በማለት ላይ የሚገኝ ጅምር ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይታያል፡፡ ይህንን ጅምር ቤተ ክርስቲያን በበላይነት እያስተባበሩ የሚያሠሩት ንቡረ ዕድ መሆናቸውን፤ ከትጋታቸውና የአካባቢው ምእመናን ለንቡረ ዕድ ካለው ከበሬታና ምስክርነት አንጻር ለማወቅ ችለናል፡፡ ግንበኞች ግንባታቸውን ቀጥለዋል፤ እኛም ስለ ቤተ ክርስቲያኑ መጠየቃችንን ቀጠልን፡፡

ንቡረ ዕድ አባ ገብረ ሕይወት መልሴ የገዳሙ የበላይ ጠባቂና ሌሎችም የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች ስለገዳሙ መረጃ መስጠታቸውን ቀጠሉ፡፡ ንቡረ ዕድ ርእሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ አለም ገደምን በማስተዳደር ፣ደብረ ገሊላ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያንን በማሠራትና በማስተዳደር፣ አሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ገዳምን በማስተዳደርና አሁንም ከፍተኛ እገዛ በማድረግ፣ሳር አምባ ኪዳነ ምረትን በማራትና እና ሌሎች ገዳማትና አድባራትን በማደራጀትና በማቋቋም የሚታወቁ አባት ናቸው፡፡ የንቡረ ዕድ የመንፈስ ጥንካሬና ትጋታቸውን እያደነቅን ቦታውን እንዴት እንደሚያውቁት ጠየቅናቸው፡፡

“አስግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳምን ከሕፃንነቴ ጀምሮ አውቃታለሁ፡፡ እንደ ጻድቃኔ ማርያም ገዳም ታላቅ በረከት ያላት ቦታ ናት ፡፡ በዚህ ቦታ ሰፊ ጉባኤ ነበር፡፡ ታቦቷም ስዕለት ሰሚና ተአምረኛ መሆኗን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ከአስፋልት ገባ ያለና መንገዱ ለመኪና አመቺ ባለመሆኑ ምክንያት ማንም አይጎበኛትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት አንዷ ናት፡፡ የቀድሞ እውቅናዋን ለመመለስና ታሪኳ ተደብቆ መቅረት የለበትም በሚል ሀሳባችንን ለተለያዩ ሰዎች ስናካፍል እንረዳችኋለን በርቱ አሉን፡፡ ጊዜው ሲደርስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ለመሥራትና ታሪኳን ለማስተዋወቅ ተነሳሳን፡፡” ይላሉ ፡፡

memera telayeመምሬ ጥላዬ በአስግድመኝ ማርያም አካባቢ ተወላጅና ለረጅም ዘመናት ታቦቷን በማገልገል የሚታወቁ የእድሜ ባለጸጋ አባት ናቸው፡፡ ስለ አሰግድመኝ ማርያም የሚያውቁትን እንዲነግሩን ጠየቅናቸው፡፡

“አሰግድመኝ ማለት በሁለት የተለያየ አቅጣጫ እየሄዱ የነበሩ ሰዎች አንድ ሰው ብቻ ማሳለፍ በሚችል ጠባብ ቦታ ላይ ተገናኙ “አሰግድመኝ” – አሳልፈኝ – አሳልፈኝ በመባባል በየተራ ያለፉበት ቦታ ስለሆነ አሰግድመኝ የሚለውን ስያሜውን እንዳገኘ ይነገራል” አሉን መምሬ ጥላዬ፡፡ ንቡረ ዕድም ቀድመው ይህንን ስያሜ ነግረውን ስለነበረ አጠናከሩልን፡፡ አብረውን ያሉ አገልጋዮችም ራሳቸውን በመነቅነቅ በአዎነታ አጸኑልን፡፡

ቀጠሉ መምሬ ጥላዬ “አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳም ከተመሠረተች ከ800 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችና ዐፄ ይኩኖ አምላክ እንደመሠረቷት ይነገራል፡፡ ዐፄ ይኩኖ አምላክ ከላስታ ወደ ተጉለት አውራጃ በመምጣት በላስታ የተጀመረውን ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን የማነጽ እንቅስቃሴ በዚህም ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ በፄ ይኩኖ አምላክ አማካኝነት ፀሐይ ልዳ፤ ልዳ ጊዮርጊስ፤ ብፅዐተ ጊዮርጊስ በተባሉ አባቶች የዋሻ ቤተ ክርስቲያኑ ተፈልፍሎ አገልግሎት መስጠቱን ከአባቶቻችንና ከአያቶቻችን ስንሰማ አድገናል” ይላሉ መምሬ ጥላዬ፡፡

“ለገዳሙ መተዳደሪያ ፄ ይኩኖ አምላክ ሦስት ጋሻ መሬት አንደኛው ጋሻ መሬት መዘዞ ላይ፤ ሁለተኛውን ደግሞ ሞጃና ዳራ ወረዳ ላይ፤ ሦስተኛውን መሐል ተጉለት ላይ ሰጥተው እስከ ደርግ መንግሥት ለውጥ ድረስ ለገዳሙ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል” አሉን መምሬ ጥላዬ፡፡

የቀይት ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ቀሲስ ብርሃኑ ለገሠ ስለ አሰግድመኝ ማርያም ከተለያዩ መረጃ ምንጮች እንዲሁም ከአባቶች የተረዱትን ሲያጫወቱን፡፡ “አሰግድመኝ ቅድስት ማርያምናkeyet wereda ወንበሮ ኪዳነ ምሕረት በአንድ አቅራቢያ የሚገኙ አድባራት በመሆናቸው አንድ ላይ አገልግሎት ይሰጥባቸው ነበር፡፡ በተለይ በወንበሮ ኪዳነ ምሕረት በርካታ የአብነት ተማሪዎችና መሪ ጌቶች ይገኙ ነበር፡፡ በዚህ ሥፍራም የንባብና የዜማ ትምህርት ሲሰጥበት የቆየ ሲሆን ዛሬም የአገልጋዮቹ ቁጥር ቢቀንስም አገልግሎት እየተሰጠበት ነው፡፡ ድሮ አባቶች አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ቀድሰው እዚያው መክፈልት አይቀምሱም ነበር፡፡ ለቦታው ካላቸው አክብሮት የተነሣ በገዳሙ ዙሪያ ምግብ ስለማይበላ ከቅደሴ መልስ ወንበሮ ኪዳነ ምሕረት እየሄዱ ነበር ምግብ የሚቀምሱት፡፡”

“ገዳሙ ከተመሠረተ በኋላ የፄ ይኩኖ አምላክ ታናሽ ወንድም አባ ሂሩተ አምላክ በምእራብ ጎጃም ዳጋ እስጢፋኖስን ያስተዳድሩ ስለነበር በሀገር እና በህዝቡ ላይ ረሃብ፣ ቸነፈርና ጦርነት ሲከሰት ወደ አሰግድመኝ ማርያም በመምጣት ጸሎት ያደርሱ ነበር፡፡ የመጣውም መቅሰፍት በእመቤታችን ምልጃ በምረት ይመለስ ነበር” አሉን ሊቀ ካህናት፡፡ ሌላም ታሪክ ይነግሩን እንደሆነ ለመረዳት ሌላስ? አልናቸው፡፡

“በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት ፄ ዘርዓ ያዕቆብ ወደ ጻድቃኔ ማርያም ሲሔዱና ሲመለሱ በአሰግድመኝ ቅድስት ማርያም እረፍት አድርገው ይሄዱ እንደነበር ይነገራል፡፡ እረፍት ያደርጉበት የነበረው ጠፍጣፋ ድንጋይም በአሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ከፍተኛ ግፍና ጭካኔ በመፈጸም ቀሳውስቱን በማረድ፤ አብያተ ክርስቲያናትን በማቀጠል ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው አሕመድ ግራኝ ወደ አካባቢው ሲመጣ ጉልላት ያላቸውንና በግልጽ የሚታዩትን አብያተ ክርስቲያናት ሲያቃጥል አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳም ግን ጉልላት ስላልነበራትና ሊደርስበትም ስላልቻለ ምንም አይነት ዝርፊያና ቃጠሎ ሳይደርሰባት ድናለች” በማለት በዝርዝር አጫወቱን፡፡

የዋሻውን ቤተ ክርስቲያን ማየት ጓጓንና ንቡረ ዕድን ዋሻው ወዴት ነው? አልናቸው፡፡ ንቡረ ዕድም “ እኔ ቁልቁለቱን መውረድ፤ ዳገቱን መውጣት ስለሚያዳግተኝ ካህናቱ ያሳይዋችሁ” ስላሉን ልብሰ ተክህኖ የለበሱና ሌሎች ምእመናን ወደ ዋሻው ይዘውን ሄዱ፡፡

ይቀጥላል