አማናዊቷ መቅደስ!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ሰኔ ፲፱፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ለነበረው ጽልመት ጨልሞት፣

ለጨነቀው ብርሃን ሰቆት፡፡

በኃጢአት ቁር ቆርፍዶ፣

በቅጣት ፍም ፍሞ ነዶ፣

ከጽድቅ አገር ከክብር ሕይወት ተወግዶ፣

ተጸጽቶ ለነበረው መዳን ወዶ፡፡

ተቋም ሆና ለማኅቶት ለአማናዊ ብርሃኑ ፣

አዳምና ልጆቹ ከመከራ እንዲድኑ፣

ከባርነቱ ተላቀው ዳግም ልጆች እንዲሆኑ፡፡

ለዘመናት በአዳም ሰውነት በርታ ኑራ ሆና ዕንቁ ፣

ምክንያተ ድኂን ከመከራ ለመለቀቁ፡፡

ለንጽሕናችን መሠረቱ መፈጸሚያ ለትንቢቱ፣

ተቋም የሆነች ለማኅቶቱ ፣

የፀሐይ መውጫ ምሥራቂቱ፡፡

በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና ወልዳ፣

ረዳችው ድንግል ማርያም እንዲወገድ የአዳም ዕዳ፡፡

እርሱ መሥዋዕት፣ እርሱ ሠዊ፣ መሥዋቱንም ተቀባዩ፣

እርሱ ካሹ እርሱ ራሱ ተበዳዩ፡

ሆኖ ለእኛ!….

ባፈሰሰው ክቡር ደሙ በመስቀል ላይ ውሎ፣

ቤተ ክርስቲያንን አጸናት መሠረቷን ያኔ ጥሎ፡፡

የገሃነም ደጆች የማይችሏት ምን ቢጥሩ፣

እንዳትፈርስ አነጻት በይቅርታና በፍቅሩ፡፡

መሰብሰቢያ እንድትሆን ለአምልኮ መፈጸሚያ፣

ሕንጻዋንም ሲመሠርት በምድር ላይ መጀመሪያ፡፡

በተአምራት በእናቱ ስም  በሦስት አዕባን አቆመ፣

የአማናዊቷን መቅደስ ምሳሌዋን በራሷ ስም ሰየመ፡፡

ማኅቶት ሆኖ ለፍጥረቱ ጨለማውን ከሰው አራቀ፣

ቃላት በማይገልጸው ፍቅሩ እኛን ከራሱ ጋር አስታረቀ፡፡

የበደላችን ማስወገጂያ፣ የዕንባችን መታበሻ፣

የሰላም ወደባችንን ከኃጢአት ደዌ መፈወሻ፡፡

ትዕቢተኛው ሲቀርባት በአዳራሽ ሲታደም፣

ትሕትናን ካባ አልብሳ ተስፋ ወንጌልን የምታሸክም ፣

ንፉጉን መጽዋች አድርጋ ለሰነፉ ትጋት የምትሸልም፡፡

በጴጥሮስ ዐለትነት በገባው ቃል እንደሚሠራት፣

መቅደሱን በእናቱ ስም በፊሊጵሲዩስ አቆማት፡፡

ከቅዱሳኑ ከምርጦቹ ከድንግል ከተቋሙ፣

የሚዘከሩበት ወዳጆቹ የሚጠራበትን  ቅዱስ ስሙ፣

ይድረሰው ግናይ ውዳሴ ለሰጠን መሥርቶ በደሙ!