ኒቆዲሞስ

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
መጋቢት ፳፪፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ቅዱስ ያሬድ ንብ የማትቀስመው አበባ እንደሌላት ሁሉን ቀስማ ያማረ የጣፈጠ ማር እንድትሠራ እርሱም ሐዲሳትን ከብሉያት እያስማማ ለጀሮ የሚስማማ ኅሊናን የሚመስጥ ድንቅ ዜማ ባዘጋጀልን መሠረት የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሊቁ “ኒቆዲሞስ ስሙ ዘሖረ ኀቤሁ ቀዲሙ ሌሊተ ወይቤሎ በጽሚት ረቢ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጽአከ ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻአከ ከመ ትኩን መምሕረ ወበምጽአትከ አብራህከ ለነ ወሰላመ ጸጎከነ አንሥእ ኃይለከ ወነዓ አድኅነነ፤ አስቀድሞ በሌሊት ወደርሱ ይሔድ የነበረ ስሙ ኒቆድሞስ የሚባል ሰው በቀስታ “ሊቅ ሆይ ከአብ ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” አለው። ኒቆዲሞስም ወደ እርሱ ሔደ፤ ረቢ ኢየሱስንም ሊቅ (አዋቂ) እንደሆንክ ለማስተማር ከአብ ዘንድም እንደመጣህ እኛ እናውቃለን፤ በምጽአትህም አበራህልን፤ ሰላምንም ሰጠኸን፤ ኃይልህን አንሳ፤ መጥተህም አድነን አለው” ይለናል። (ጾመ ድጓ)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር የአይሁድ አለቃ የሚሆን ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው በሌሊት መጣ፤ ስለምን በሌሊት መጣ ቢሉ ከንቱ ውዳሴን ሽቶ አንተ የአይሁድ አለቃ ስትሆን እንዴት ትማራለህ እንዳይባል ሰው በማይመጣበት ከሰው ተለይቶ ሊማር ሽቶ በሌሊት መጣ። እንደዚሁም ምሁረ ኦሪት ነውና ምሥጢር ሊያደላድል ነው። በቀን ጌታን አምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው ስለነበር ለመጠየቅ አልተመቸውም ነበር፡፡ ጌታም በአእምሮ ያልጎለመሱ ሰዎችን ያስተምር ነበርና በምሳሌ እየመሰለ ያስተምራቸው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ “እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?” እንዲል አጥንት ለመቆርጠም አልደረሱም ነበር። (፩ኛቆሮ.፫፥፩-፫) ኒቆዲሞስ ግን ምሁረ ኦሪት ነውና ጠንከር ያለ ትምህርት ሽቶ በሌሊት መጣ። በተጨማሪም የቀን ልቡና ባካና ነው ኅሊና ይሠረቃልና ክት ሊኅና ሽቶ በሌሊት ሊማር መጣ።

አባቶቻችን በሠሩት የትምህርት ሥርዓትም ምንኛ ጥበበኛ እንደ ሆኑ አስተውሉ! በቀን ጆሯችን የአካባቢ ድምጽ ይሰማል፤ ዓይናችን ሌላ ይመለከታል፤ ወጭ ወራጁ አላፊ አግዳሚው ይረብሻል። በሌሊት ግን ኅሊናን የሚሠርቅ ምንም ነገር የለምና ሐሳብን ሰብስቦ ለማስተማር እንዲመች የአብነት ትምህርቱን የሌሊትና የቀን ብለው ከፍለው የቃል ትምህርቱን በሌሊት እንድንማር አደረጉን። የጠቢቡ ሰሎሞን “ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት” የሚለው ቃል ምነኛ ይደንቃል! (መኃ.፫፥፩) ኒቆዲሞስ ነፍሱ የፈለገችውን ሊፈልግ በሌሊት መጣ። ሌሊት ሁሉ ሰው ተኝቶ ባለበት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር መቻል እንዴት መታደል ነው። ክርስቲያኖች እስኪ አስቡት! ማንም በሌለበት፣ ሁሉ በተኛበት ሰዓት አልጋችሁ ላይ ሁናችሁ ክርስቶስን መፈለግ በጨለማ ውስጥ ውሳጣዊ ዓይናችሁ ብቻ ተከፍቶ ከአምላካችሁ ጋር መነጋገር እጅግ ልዩ ነውና ሌሊቱን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን አሳልፉት።

ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ በመሆኑ ቀን ሥራ ውሎ ሌሊት በእግዚአብሔር ቃል ያርፍ ነበር። ይህ ሐሳብ ለእኛ ዘመንም የሚጠቅም ነውና እንማርበት ዘንድ ወደድኩኝ። ዛሬ የሕዝብ አለቃዎች ሹማምንቶች መኳንንቶች እናንተስ መቼ ነው የምትማሩ? የምትበልጠዋን ጸጋ ታገኟት ዘንድ ያገኛችኋትን ታጸኗት ዘንድ ኑ! የእግዚአብሔር አካል በሆነችዋ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል እየሰማችሁ ዕረፉ። ዛሬ ብዙ ሰው ለምን አትማርም ሲባል ሥራ በዝቶብኝ፣ ቢዚ ሁኜ በማለት መመለሱ እየተለመደ መጥቶአል። እኔ ግን እንዲህ ብዬ እጠይቃችኋለሁ፣ በውኑ የእናንተ ሥራ ከኒቆዲሞስ ይበልጣልን? ወይስ ከዳዊት በላይ ትሠራላችሁ? ወይንስ ከላል ይበላ በላይ ሠርታችሁ ነው? እኔ ግን በመኃልየ መኃልይ እንደ ተጻፈ በምክንያት እየራቃችሁ ነው። “እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፤ የውዴ ቃል ነው፥ እርሱም ደጁን ይመታል፤ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ። ቀሚሴን አወለቅሁ፤ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፤ እንዴት አሳድፈዋለሁ?” በማለት እንደተናገረችው ሰው የሆን ይመስለኛል። (መኃ.፭፥፪) ይህች ሰው ከረፈደ በኋላ ፍለጋ ብትወጣም ማግኘት ግን አልቻለችም፤ እናም ሁላችንም ዛሬ ሳይረፍድብን ታግለን መጣል ሩጠን መቅደም በምንችልበት ጊዜ ምክንያት በመደርደር አንራቅ ለማለት እወዳለሁ።

ኒቆዲሞስ በሌሊት መጥቶ ከጌታችን እግር ሥር ተቀምጦ ሲማር በዓይነ ኅሊናችን እንመልከተው! ግርማ ሌሊቱ ጸብአ አራዊቱ ሳያስፈራው፣ ድካም ሳይበግረው በጌታው እግር ሥር ቁጭ ብሎ ሲማር ቅዱስ ዳዊት ” ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” እንዳለ ከማርና ከሥኳር የሚጣፍጠውን ቃለ እግዚአብሔር ሲሰማ ሰው እንዳያየው ተደብቆ የመጣው ኒቆዲሞስ ከመስቀሉ ሥር የሚገኝ የመከራ ቀን ሐዋርያ ሆነ። (መዝ.፻፲፱፥፻፫-፻፭) ሌሊት በመከራ ይመሰላል፤ በመከራ መጥቶ የተማረው ኒቆዲሞስ ሐዋርያት እንኳን ጥለውት በሸሹ ጊዜ ከመስቀሉ ሥር ተገኘ። ሥጦታ ይሆን ዘንድ የክርስቶስን ሥጋ ገንዞ ለመቅበር የበቃ ሆነ። ክርስቲያኖች! እናንተስ ክርስቶስን ልትገንዙ ትሻላችሁን? በዚያ በመስቀል ላይ ሳለ ቅድስት ሥጋው ከቅድስት ነፍሱ ሲለይ ከመስቀል አውርዶ የሚቀብረው አጥቶ እናቱ ድንግል ማርያም እያለቀሰች ሳለ የተገኘ የእመ ብርሃንን እንባ ያበሰ ቅዱስ ለመሆን በቃ።

አሁንም እንደ ኒቆዲሞስ ሌሊት መጥቶ የሚማር ሰው አጥታ ቤተ ክርስቲያን ስታለቅስ፣ ሰቃልያነ ክርስቶስ ጌታን ዳግመኛ ሊሰቅሉት ሲሹ ከመስቀሉ ሥር የሚገኝ በመከራ የሚጸና ሰው ያስፈልጋልና የዓለም ውጣ ውረድ ሳያግዳችሁ ከቤቱ መጥታችሁ ትማሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። ዛሬ ላይ አንድ ነገር ይደንቀኛል! ሰው ሥልጣን ሲይዝ ከቤተ ክርስቲያን የሚያደርገውን ሽሽት አስተውሉ! ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ቢሆንም ግን ወደ ጌታ ከመምጣት አላገደውም፤ የዛሬዎቹ አለቃ ግን አለመምጣት ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ሆኖ መታየት እንኳን ያሳፍራቸዋል። የልቤ እምነት እንጅ ማተብ ባላደርግስ በሚል ሐሳብም ማተባቸውን የሚፈቱም አይጠፉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለመመሳሰል ሐብል ያደርጋሉ። ክርስቲያኖች ከአምላካችን በእውነት ወዴት እንሄዳለን? እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት “ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት” እንዲል፤ እንዲህ እያልን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ (ዮሐ ፮፥፷፰)

ሊቃውንቱም በቅኔያቸው ረቢ ሰገደ በመንፈቀ ሌሊት ለረቢ አኮኑ አጽባእት እምነ አጽባእት የዓቢ፤ ….. በማለት ጣት ከእጣት እንዲበልጥ የአይሁድ ምሁር የነበረው ኒቆዲሞስ ለጌታችን እንደሰገደ ከቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ በመነሳት ይቀኛሉ። በመጨረሻም ኒቆዲሞስን መምህራችን አድርገን ቀን በሥራችን ስንባክን የምንውል እኛ ማታ ላይ የእግዚአብሔርን ቃል እንማር ምን አልባት እንደ አካብና ኤልዛቤል የሚያሳድደን ንጉሥ መጥቶ ራብተኞች እንዳንሆን፣ ዛሬ እንቅልፋችንን ቀንሰን ከኃጢአታችንን ነቅተን ቃለ እግዚአብሔር እንብላ ” የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው” (፩ኛነገ.፲፱፥፯) እንዲል፡፡

አምላካችን በቸርነቱ ከእንቅልፋችንና ከኃጢአታችን ነቅተን ቃሉን እንደ ውኃ ተጥተን፣ እንደ ምግብ ተመግበን፣ እንድ መጎናፀፊያ ተጎናጽፈን እንድንኖር ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክበር አሜን!!!