‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ››

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

መጋቢት ፲፯፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፉት ሁለት ክፍሎች ‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ›› በሚል ርእስ ጽሑፍ አድርሰናችኋል፡፡ አንብባችሁ ቁም ነገር እንዳገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አሁን ደግሞ ክፍል ሦስትን ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ!

ቤተ ክርስቲያን አሁን የገጠማትን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት አሸንፋ ለመጩ ትውልድ ከእነ ሙሉ ክብሯና መታፈሯ መሻገር አለባት፡፡ በየዘመኑ ከክፉዎች ጋር ታግላ አሸንፋለች፤ ተዋግታ ድል አድርጋለች፤ ጠላቶቿን ሁሉ አሳፍራ ከዚህ ዘመን ደርሳለች፡፡ ምክንያቱም የዚህች ቤተ ክርስቲያን የቅድስና፣ የመከበርና የመታፈር፣ የአሸናፊነትና የድል አድራጊነት ምሥጢር ክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና ስለ ነበሩ ነው፡፡

የነገዋ ቤተ ክርስቲያንና ክብረ ክህነት፡-

ክብረ ክህነት ሲከበር ሲኖዶሳዊ ልዕልና ይከበራል፡ ፡ክብረ ክህነት ሲኖር ቤተ ክርስቲያን የታፈረችና የተከበረች ትሆናለች፤ ክብረ ክህነት ሲኖር የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ያድጋል፤ ክብረ ክህነት ካለ ሃይማኖት ይጸናል፤ ምግባር ይቀናል፤ ትውልዱ ሰላማዊና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ይሆናል፡፡ ክብረ ክህነት ካለ መልካም አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን ይሰፍናል፤ የምእመናን አንድነት ይጸናል፤ ክፉ ሠራተኞች ቦታ ያጣሉ፤ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ ይሳካል፤ ሰላም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ሰላም በአባቶች መካከል፣ ሰላም በምእመናን ሕይወት ዘንድ ይሰፍናል፤ አልፎ ተርፎ ትሩፋቱ ለሌላም ለሀገር ይተርፋል፡፡ ድኃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ የሚል መሪ ይመጣል፡፡ በዘመናችን ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት የክብረ ክህነትና የገዳማዊ ሕይወት ወይም ክብረ ምንኩስና መዳከምና ቅቡልነት መቀነስ ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡
ለመሆኑ ክህነት ምንድን ነው?

ክህነት በቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ተክህነ›› ተሾመ፤ አገለገለ፤ ዲቁና፣ ቅስና፣ መንፈሳዊ ሥልጣን ተቀበለ›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ ለአገልግሎት መመረጥን፣ መሾምን ሹመቱም መንፈሳዊ እንደሆነ ሲያመለክት ነው፡፡ (ኪዳነ ወልድ፣ ገጽ ፭፻፳፪)

ካህን፡- ማለት ደግሞ የሕዝብ መሪ፣ አስተማሪ አባት፣ አገልጋይ ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ክህነት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሆን ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የማቅረብያ፣ ከእግዚአብሔር የተገኘ ስጦታና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ ሥልጣን ስለፈለግን የምናገኘው ስለወደድን የምንሾመው ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ለተመረጡት ከሚሰጣቸው ሀብታት አንዱና ትልቁ ነው፡፡

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው…፤ ለሁሉም ጌታ እየረዳ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳዱ በግልጥ ይሰጠዋል›› በማለት እንደገለጸው ክህነት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንጅ ብዙ ገንዘብ፣ ዘመድና ሀብት ስላለን የምናገኘው አይደለም፡፡ (፩ኛቆሮ.፲፪፥፬)

ሥልጣነ ክህነት በማናቸውም ሥጋዊ ደማዊ መመዘኛዎች የሚሰጥ አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ሲያስረዳ ‹‹መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ›› በማለት እንደገለጸው አገልግሎቱ ፍጹም መንፈሳዊ መሆኑን ከዓለማዊ ሥልጣን እና ሹመት መንገዱም ተግባሩም የተለየ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ (፩ኛጴጥ.፪፥፭)

በአጠቃላይ ክህነት ማለት አገልግሎት ማለት ሲሆን በእግዚአብሔርና በምእመናን መካከል ተገኝተው የእግዘዚአብሔርን ፈቃድና ትእዛዝ ለመፈጸምና ምእመናንን ለመጠበቅ፣ ለማስተማር፣ ለማስታረቅና ለማጽናት እንዲሁም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለመፈጸም እንዲችሉ ለማድረግ ለተመረጡ ሰዎች የሚሰጥ ሥልጣን ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ እነዚህን ምሥጢራት ስናስብ ያለ ክህነት የሚከወኑ ወይም የሚፈጸሙ አይደሉም፡፡ ያለ እነርሱ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንንም ክርስትናንንም በማሰብ አገልግሎቱን ማሟላት አይቻልም፡፡

ክህነት የሚያገለግሉበት እንጅ የሚገለገሉበት ሹመት አይደለም፡፡ በኦሪትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሙሴ ‹‹የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ፤ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ›› በማለት ነግሮታል፡፡ (ዘጸ.፵፥፲፫) በዚሁ በኦሪት መጽሐፍ ላይም ‹‹ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አሮን ቅዱስ ይሆን ዘንድ ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላባቸው በልባቸው ጥበበኛ ለሆኑት ሁሉ ተናገር›› በማለት እንኳንስ የተሾመው ካህኑ የእርሱን ልብስ እንኳን የሚያዘጋጁት የጥበብ መንፈስ በልባቸው የሞላባቸው ጥበበኞች እንደሆኑ፣ የተሾመው ካህንም ቅዱስ ሆኖ ቅዱሱን እግዚያብሔር የሚያገለግል ካህን እንደሆነ መመረጡ፣ መሾም መሸለሙም ለአገልግሎት መሆኑን እንረዳለን፡፡ (ዘጸ.፳፰፥፫) በዘመናችን ክህነት ይህን ትርጉም ይዞ ይገኛል ወይ? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ አገልግሎቱም ማስተማር፣ መምከር፣ መገሠፅ፣ መሥዋዕትን በመሠዋትና ጸሎትን በመጸለይ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከላይ ከቀረበው ትርጉም ስንነሣ በአብዛኛው የሚያመለክተው ካህን/ቄስ/የምንለውን የሚገልጽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይሁን እንጅ ክህነት ሦስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን የሹመቱ ባለቤቶችም እንዲሁ ሦስት ደረጃዎች አሏቸው፡፡ ዲቁና/ዲያቆን/፣ ቅስና/ቄስ/ እና ኤጲስ ቆጶስነት/ኤጲስ ቆጶስ/ ናቸው፡፡

ሁሉም ግን የክህነት ባለቤቶች ሲሆኑ የስማቸው ትርጉምም “አገልጋይነት” ነው፡፡ እነዚህ የክህነት ደረጃዎች የክርስትናችን የአምልኳችን መሠረቶች ናቸው፡፡ ክብረ ክህነት ስንል ስለ ሁሉም ማለትም ስለ ክብረ ዲቁና፣ ስለክብረ ቅስና እንዲሁም ስለ ክብረ ኤጲስ ቆጶስነት (ጵጵስና) እየተናገርን ነው፡፡ ክብረ ዲቁና፣ ክብረ ቅስና፣ ክብረ ጵጵስና ትናንትና ዛሬ ምን መልክ አለው? ነገስ ምን ሊሆን ይችላል? ምንስ ሊሆን ይገባዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅና ጥያቄዎቹን መመለስ ትርጉም ያለው ጉዳይ ነው፡፡

የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ጽንዕ ለማድረግና ቤተ ክርስቲያን በምድር ያላትን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እንድትወጣ ክብረ ክህነት መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ መሆኑን እኛ የዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ባላደራዎችና የነገው ትውልድ አስረካቢዎች መረዳት ብቻ ሳይሆን ክብረ ክህነት የገጠመውን ተግዳሮት አስወግደን የተሟላ ማንነት ያላት ቤተ ክርስቲያን ለነገ ማሸጋገር ግዴታችን ነው፡፡ የዚች ቤተ ክርስቲያን መሠረት ክህነት በመሆኑ ከተግባባን ክብረ ክህነት በዘመናችን ምን ሁኔታ ላይ ነው? በትናንትና በዛሬ መካከልስ ምን ለውጥ ታይቶበታል? አሁን ላይ ክብረ ክህነት በብዙ መልኩ እየተፈተነ ነውና ከዚህ እንዴት ልንወጣና ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና፣ የንጽሕና፣ የመልካም አስተዳደርና የክብር መገለጫ፣ የምእመናን ኩራትና ክብር ሆኖ ይቀጥል? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን መወያየት ያስፈልጋል፡፡

ክህነት ትናንትና የሚያገለግሉበት እንጅ የሚገለገሉበት፣ የሚያበለጽጉበት እንጅ የሚበለጽጉበት፣ ሌሎችን የሚያከብሩበት እንጅ ራስን የሚያከብሩበት አልነበረም፡፡ በክህነት ብዙዎች ምግበ ሥጋ ምግበ ነፍስ አግኝተዋል፤ የታመሙ ተፈውሰውበታል፤ ያዘኑ ተጽናንተውበታል፤ የተሰበሩ በሥጋም በመንፈስም ተጠግነውበታል፤ የተበተኑ ተሰብስበውበታል፤ የራቁ ቀርበውበታል፤ ለብዙዎች የንጽሕና፣ የቅድስና፣ የመታደስ እንዲሁም የተሰደዱ የተመለሱበትም ምክንያት ነበር፡፡

ክህነት ትናንት የብዙዎች አንደበት ነበር፤ የተጣሉ ታርቀውበታል፤ የተበደሉ ተክሰውበታል፤ አምባገነኖችና ክፉዎች ተገሥፀውበታል፤ እግዚአብሔርም ሰውም ከብሮበታል፤ አጋንንትና የአጋንንት ማደሪያ የሆኑ ሁሉ ተዋርደውበታል፡፡ በአማናዊ ክህነት ዓይኑ ያልበራለት፤ የድንቁርና ጨለማን ያላስወገደ በክብረ ክህነት ያልከበረ ማንም አልነበረም፡፡

መጠራታቸውን ያወቁ፣ መመረጣቸውን ያጸኑ፣ ራሳቸውን አክብረው ክብረ ክህነትን ያስከበሩ በክብረ ክህነት በአርአያ ክህነትና በመታፈር በመከበር የነበሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለአገልግሎታቸው ሰማያዊ ዋጋን እንጅ ምድራዊ ደመዎዝን የማያስቡ፣ እውነተኛ አገልጋዮች የአገልግሎትን ዋጋ የሚያውቁ፣ የክህነትን ታላቅነትና የተልእኮውን ክብደት የተረዱ ለማገልገል ቅድመ ሁኔታ ያልነበራቸው፤ አገልግሎታቸው በቦታና በሁኔታ ያልተገደበ የክህነት ሰዎች ነበሩ፡፡

ባሉበት በተሾሙበት አጥቢያ ቀርቶ መንገድ ሲጓዙ በመንገድ ምናልባት ቅዳሴ ሊታጎል ይችላል ብለው ምግብ ሳይበሉ የሚጓዙ ጸጋቸውን በውል የጠበቁ ክህነትን ተከብረው ያስከበሩ አባቶች የነበሩባት ቤተ ክርስቲያን ስለነበረች በወዳጆቿ ተከባሪ በጠላቶቿ ተፈሪ ሆና ዘመናትን ተሻግራለች፡፡

ውድ የዚህ ጽሑፍ ተከታታዮች! “ክብረ ክህነት ዛሬስ ምን ደረጃ ላይ ነው? ነገስ ምን መሆን አለበት?” የሚሉ ጉዳዮችን በቀጣይ ክፍል ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ሰላመ እግዚአብሔር አይለየን!