“ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ”

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው

ታኅሣሥ ፳፬፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የካህን ልጅ ካህን፣ ምድራዊ የሆነ ሰማያዊ፣ ሰው ሲሆን መልአክ፣  ከሱራፌል ጋር የእግዚአብሔርን ዙፋን ያጠነ፣ ከመላእክት ጋር የተባበረ፣ ግዙፍ ሲሆን የረቀቀ፣ ባሕታዊ ሲሆን መምህር፣ ኢትዮጵያን በወንጌል ያበራ፣ የምድር ጨው፣ ስለአባታችን ተክለ ሃይማኖት ይህን እወቁ!

የፀጋ ዘአብ ዘር ምን ያህል ቡርክት ነች፤ የእግዚእኃረያ ማኅፀን ምን ያህል ለምለም ነች!? አንደበቱ ለምስጋና የተፈታ፣ መላእክት የሚደሰቱበት፣ የሃማኖት ተክል፣ በዛፍ ጥላ ከፀሐይ ሙቀት እንድንጠለል የሃይማኖት ጥላ የሆነ፣ የበረከት ፍሬ፣ የበረከት ምንጭ፣ የጽዮን ደስታ፣ ፍስሐ ጽዮንን አስገኝተዋልና።

ገድለ ተክለ ሃይማኖት እንዲህ ይላል፦ “ጸጋ ዘአብ ደጋግ ከሆኑ ሰዎች ወገን ሣራ የምትባል ሴት አግብቶ ተቀመጠ። እግዚአብሔርን በማገልገልም እጅግ ደግ ሆኑ፤ ጾም በመጾም፣ ጸሎት በመጸለይ፣ ትዕግሥትንም ገንዘብ በማድረግ፣ ከቀን ወደ ቀን በጎ ሥራን እያበዙ ሔዱ። እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ፣ እንደ ኤልሳቤጥና እንደ ዘካርያስ እጅግ ይዋደዱ ነበር። ሣራ ከአማቷ ቤትም ሳለች በሕግ ጸንታ ሥራዋን ሁሉ ገለጠች፤ ለአንደበቷ መወሰንን፣ ክንዷን ለመፍተል አጸናች። አማቷ የሥራዋን ሁሉ ደግነት ባየ ጊዜ ስሟን ለውጦ እግዚእኃረያ አላት።

የጸጋ ዘአብ ሥራው ጠዋትም ማታም በማልትም በሌሊትም ወደ ቤተ ክርስቲያን መገሥገስ ነበር። ቅዱስ ዳዊት “አምላኬ አምላኬ ወደ አንተ እገሠግሳለሁ።” እንዳለ (መዝ.፷፪፥፩) ዕጣን ለማጣነ የሚሔድበት ጊዜ አለ፤ መሥዋዕት ለመሠዋት የሚሔድበት ጊዜ አለ፤ ዳዊት ለመድገም የሚሔድበት ጊዜ አለ፤ መጻሕፍት ለማንበብ የሚሔድበት ጊዜ አለ፤ ወንጌልም ለማስተማር የሚሄድበት ጊዜ አለ፤ የትሩፋት ሥራ ለመሥራትና ጸሎት ለማድረግ የሚሄድበት ጊዜ አለ። እየተፋጠን ከሚሠራው ሥራ ሁሉ ጋር ወደ ቤተ እግዚአብሔር ባዶ እጁን አይሄድም። ለቤተ ክርስቲያን የሚሆን እጅ መንሻ ይዞ ይመጣል እንጅ። (ገድለ ተክለ ሃይማኖት ም.፱)

እግዚእኃረያና ፀጋ ዘአብ በቅድስና የሚኖሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለተቸገረ የሚያበሉ፣ ለታረዘ የሚያለብሱ፣ በትሕትና ያጌጡ ደጋግ ባልና ሚስት ነበሩ። ነገር ግን ልጅ መውለድ ባለመቻላቸው ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት ያቀርቡ ነበር። እግዚእኃረያም በጸሎቷ “እግዚአብሔር ሆይ አንተን የሚያገለግል አንተ የምትከብርበት ደስ የምትሰኝበት ልጅ ስጠኝ አንተን የማያገለግል ከሆነ ግን ማኅፀኔን ዝጋው” በማለት ትጠይቅ ነበር። (ገድለ ተክለ ሃይማኖት ም.፱)

ክርስቲያኖች እኔና እናንተስ እግዚአብሔር የምንለምነው ምን ዓይነት ልጅ እንዲሰጠን ነው? አንድ ጥያቄ ልጠይቅና ወደ ተነሳሁበት ሐሳብ ልመለስ፡፡ በእውነት ልጆቻችሁን ትወዷቸዋላችሁን? እንግዲያውስ የሚጠፋ ምግብ ሳይሆን ዘለዓለማዊውን ማዕድ መግቡአቸው፤ ያማረ ያጌጠ ልብስ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስንም እንዲለብሱ አድርጓቸው፤ “ክርስቶስን ልበሱት” እንዲል፤ (ሮሜ ፲፫፥፲፬) ሥጋቸው እንዲወፍር ሳይሆን የተራበች ነፋሳቸው እንድትለመልምና እንድትወፍርና እንድታፈር መግቧት። የነፍስ ምግቧ ቃለ እግዚአብሔር ነውና። ፀሐይ አጥታ እንደ ጠወለገች፤ ዕፅዋት የገረጣች ነፍሳቸው የማይጠፋ የማይጠልቅ የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስን እንዲሞቁ አድርጓቸው፤ እንዲህ ካደረጋችሁ እውነትም ልጆቻችሁን ትወዳላችሁ።

በመጋቢት በሃያ ሦስት ቀን ለሃያ አራት አጥቢያ ጸጋ ዘአብ የሚያጥንበትን ቀን ጨርሶ ወደ ቤቱ ገባ። አባታችን ተክለ ሃይማኖትም ተፀነሱ። ሌሊት በአንድነት ተኝተው ሳሉ እግዚእ ኃረያ ራእይ አየች። ራእዩም እንዲህ ነበር፤ የብርሃን ምሰሶ ከቤቷ ውስጥ ቆሞ፣ የምሰሶው ራስ ከሰማይ ደርሶ፣ በዓለም ያሉ ሕዝብ ሁሉ ነገሥታቱም ጳጳሳቱም በዙሪያው ቁመው፣ እኩሌቶቹም ሲሰግዱለት፣ እኩሌቶቹም እርሱን ጥግ አድርገው ሲቀመጡ፣ በእርሱም ላይ ብዙ አዕዋፍ ተቀምጠውበት፣ ይህን ስታይ ጸጋ ዘአብ በእንቅልፍ ልቡ ስለተነጋገረ ሕልም ማየቷን አቋረጣትና ነቃች። እርሱንም አነቃችውና “ለምን ትጮኻለህ” አለችው። “ድንቅ ሕልም አይቼ ነው” ቢላት “ምንድን ነው” አለችው፡፡ እርሱም ከምንተኛበት አጎበር ሥር ፀሐይ ሲወጣ፤ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ብሩሃን ከዋክብት በክንፉ ላይ ተቀምጠው፣ ለዓለሙ ሁሉ ሲያበሩ፣ ከብርሃኑም ብዛት የተነሣ ሀገሩ ሁሉ ሲያበራ አይቼ ደንግጬ ጮኹኩ አላት። እግዚእ ኃረያም “ይህ ነገር እጅግ ድንቅ ነው፤ ማንም ሊሰማው አይችልም። እኔም እንጅ እንዳንተ ድንቅ ሕልም አየሁ” ብላ ያየችውን ነገረችው። (ገደለ ተክለ ሃይማኖት ም.፲፭)

ከዘጠኝ ወርም በኋላ መልኩ እንደ ፀሐይ የሚያበራ ያማረ የተወደደ ልጅ ፍስሐ ጽዮን ተወለደ። እናትና አባቱም ደል ተሰኙ። በቤታቸውም ግብዣን አደረጉ ነዳያንን ጠርተው መገቡ፤ በእነርሱ ልጅ ማግኘት የተጠራው ሰው ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ፍስሐ ጽዮን በተወለዱ በሦስተኛው ቀን የካህን ልጅ ናቸውና የክህነት ሥራን ጀመሩ። እጆቹን ዘርግቶ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አንሥቶ “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገን። (ገድለ ተክለ ሃይማኖት ም.፲፮) ቅዱስ ዳዊት “እም አፈደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” እንዳለ፡፡ (መዝ.፰፥፪)

ካህኑ ጸጋዘአብና እግዚኀረያም ልጃቸውን ፍስሐ ጽዮን አሉት። ትርጉሙም “የጽዮን ተድላዋ ወይም ደስታዋ” ማለት ነው፡፡ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ የተመረጠው ፍስሐ ጽዮንንም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምረው በሕገ እግዚአብሔር አሳደጉት፡፡ በአንድ ወቅትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ሃይማኖት» ብሎ ሰየመው፡፡ ትርጓሜውም “የሃይማኖት ፍሬ፤ የአብ ተክል የወልድ ትክል የመንፈስ ቅዱስ ተክል” ማለት ነው፡፡

ከዚህም በኋላ ድቁናና ቅስና ተሾመው ካገለገሉ በኋላ ከሐይቅ እስጢፋኖስ ለዐሥር ዓመታት በመመንኮስ በተጋድሎ ኖረዋል፡፡ ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ በመሄድ በገድልና ትሩፋት ኖሩ፡፡ ኢየሩሳሌምም በመጓዝም ከጎበኙ በኋላ በኢትዮጵያ በተለይም በደቡቡ አካባቢ ለዐሥር ዓመታት አስተምረዋል፡፡ በመቀጠለም በደብረ ሊባኖስ ገብተው አገልግለዋል፡፡ በዚህም ወቅት አምላካቸውን በጸሎት በሚማጸኑ ጊዜ አንድ እግራቸው ተቆርጧል፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ስድስት ክንፍ ሰጣቸው፡፡ እርሳቸውም እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ተጋድሏቸውን ፈጽመዋል፡፡ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት የወንጌልን ቀንበር ተሸክመው ሀገራችን ኢትዮጵያን በዕርፈ መስቀል ያረሱ ሐዲስ ሐዋርያ እንዲሁም ቅዱስ ናቸው፡፡

የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አማላጅነታቸውና ተረዳኢነታቸው እንዲሁም በረከታቸው ይደረብን፤ አሜን!