ተአምራትን ፍለጋ

ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ተአምር የሚለው ቃል የግእዝ ሲሆን ትርጕሙም ምልክት ማለት ነው፡፡ የማይታይ ረቂቅ እግዚአብሔር ኃይሉን፣ ከሀሊነቱንና ጌትነቱን የሚገልጥበት የሥራ ምልክት ነው፡፡ በሌላም መልኩ ተአምር በእግዚአብሔር አማካኝነት ለሃይማኖታዊ ዋጋ ሲባል የሚፈጸም ትርጕም ያለው ተግባር ነው፡፡ ተአምር፡- በእግዚአብሔር ቸርነት የሚፈጸም፣ ሃይማኖታዊ ቃጋ እና ትርጕም ያለው ተግባር እንዲሁም የተፈጥሮ ክስተት ነው፡፡

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በዘመነ አበውና በዘመነ ኦሪት በቅዱሳን ነቢያት እጅ ተአምራትን ሲያደርግ ኖረዋል፡፡ (መዝ.፻፴፭፥፬) በሐዲስ ኪዳንም በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ ለድኅነት ዓለም በተገለጠ ጊዜ አያሌ ተአምራትን አድርጓል፤ ሙታንን አስነሥቷል፤ ለምጻሞችን አንጽቷል፤ ድውያንን ፈውሷል፤ ጐባጦችን አቅንቷል፤ ሽባዎችን ተርትሯል፡፡ (ማቴ.፰፥፪‐፫፣፱፥፪‐፯፣ሉቃ.፲፫፥፲‐፲፯፣ዮሐ.፲፩፥፵፫‐፵፬) ጌታችን እነዚህን ተአምራት ያደረገው ተአምራትን ማድረግ የባሕርይ ገንዚቡ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱ በባሕርዩ የሚያደርገውንና ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎችና ተአምራት ወዳቾቹ ሲሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያትና ደገኛ አባቶች እንዲሁም እናቶች በጸጋ አድሏቸዋል፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፡፡ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፡፡›› (ዮሐ.፲፬፥፲፪)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን በእግረ ሥጋና በእግረ ልቡና በፍጹም የተከተሉ ወዳጆቹ የሚያደርጉትን ተአምራት በተመለከተ ሲናገር ‹‹ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል›› ማለቱ እርሱ በዚህ ምድር በመዋዕለ ሥጋዌ ሲመላለስ ሊያደርጋቸው አስፈላጊ ባለመሆናቸው ምክንያት ያላደረጋቸውን ተአምራት በኋላኛው ዘመን አስፈላጊ በሚሆኑበት ጊዜና ሁኔታ ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ የሚያስተምረን ኃይል ነው፡፡ ለዚህም ምስክር እንዲሆን እርሱ በልብሱ ዘርፍ ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም ሲፈሳት የነበረቸውን ሴት አማካኝነት እንደፈወሳት የእርሱ ምርጥ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ በሰውነቱ ጥላ አጋንንትን ያወጣ ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ (ሉቃ.፰፥፵፫፣የሐዋ.፭፥፲፭) ይህ የጌታችን ትምህርት ተአምራት የሚፈጸሙት አስፈላጊ ሲሆኑ ብቻ መሆኑንም ጭምር ያስተምረናል፡፡ ጌታችን ይህን በትምህርት ከማስተማሩም ባለፈ ተአምራትን እንዲደርጉ ጸጋን አድሏቸዋል፤ ሥልጣንም ሰጥቷቸዋል፡፡ (ማቴ.፲፥፭‐፱፣ማር.፲፮፥፲፯‐፲፰)

በዚህም መሠረት አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በሚያስተምሩበት ወቅት ብዙ ተአምራትን አድርገዋል፡፡ (የሐዋ.፫፥፪‐፰፣፭፥፲፪‐፲፮፣፲፱፥፲፩) ተአምራትን ማድረግ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣር ጸጋና ሥልጣን ቢሆንም አምላክ ሰው ከሆነበት፣ በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና ከተወለደበት ከሥጋዌ የሚበልጥ ግን አንዳችም ተአምር እንደሌለ ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡ የአምላክ ሰው መሆንን ነገር በምልዓትና በስፋት ያስተማረ ቅዱሳ ዮሐንስ አፈወርቅ የሥጋዌውን ምሥጢር አስተምህሮ የልደቱ ነገር ቢረቅበት ‹‹እንግዲህ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረ እርሱ ትንሽ ሕፃን ሆነዋልና›› ብሎ እንደተናገረ፡፡ (ኢሳ.፯፥፲፬፣፱፥፮፣ሚክ.፭፥፪፣ ዮሐ.፩፥፩‐፫)

ተአምራት አስፋላጊ ሊሆኑ ቢችሉም እነርሱን አብዝቶ መፈለግ ግን አመንዝራነት ነው!

በዚህ ምድር እንደ ክርስቲያን ሆነን ስንኖር የሚገጥሙን ፈተናዎችና አጣብቂኞች ይኖራሉ፡፡ (ዮሐ.፲፮፥፴፫፣ ያዕ.፩፥‐፬) የሚገጥሙንም አንዳንድ ፈተናዎችም ከማስጨነቃቸው የተነሣ በእግዚአብሔር ተአምር እናመልጣቸው ዘንድ እንመኝ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናዎቹ ጸጋና ክብር ሊያሳጡንም ጭምር ስለሚችሉ ተአምራት ተደርገውልን ከምናመልጣቸው በሃይማኖትና በምግባር ጸንተን፣ በጾም በጸሎት ታግሠናቸው ድል ብንነሣቸው የበለጠ ክብርን ልናገኝባቸው እንችላለን፡፡ (ምሳ.፳፰፥፲፪፣፩ጴጥ.፬፥፲፪‐፲፮) ከጻድቁ ኢዮብ፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ከደቀ መዝሙሩ ከቅዱስ ጢሞቴዎስም ተግባራዊ ሕይወት ይህን እንማራለን፡፡ (ኢዮ.፩፥፩‐፳፪፣፪፥፩‐፱፣፪ቆሮ.፲፪፥፯‐፲፣፩ጢሞ.፭፥፳፫)

እግዚአብሔርን ለማመን በቤቱ ጸንቶ ለመኖር ለሚገጥሙን የዚህ ዓለም መሰናክሎች ሁል ጊዜ ተአምራትን መሻት እግዚአብሔር የሚወደው መንገድ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ በሚያስተምርበት ወራት ጻፎችና ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹መምህር ሆይ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን›› አሉት፡፡ እርሱ ግን መልሶ ‹‹ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፤ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፡፡ አነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ›› አላቸው፡፡ (ማቴ.፲፪፥፴፰‐፵፪)

ምልክትን (ተአምርን) የሚፈልግ ትውልድ ለምን ክፉና አመንዝራ ተባለ? ክፉ የተባለው እምነቱን በተአምራት ላይ ስላስደገፈና ስለሚያስደግፍ ነው፡፡ አመንዝራ የተባለበትም ምክንያት አመንዝራ ሰው ነገሩ አንድ ሲሆን ዕለት ዕለት ሴት (ወንድ) ሊለወጥለት እንዲወድ አይሁድና የአይሁድን መንገድ የሚከተሉ ሰዎችም ዕለት ዕለት ትምህርትና ተአምራት ሊለወጥላቸው ይወዳሉና ነው፡፡ (ወንጌል ቅዱስ ንባቡና ትርጓሜው)

ጌታችን በግልጽ እንዳስተማረንም እርሱ ሞትን ድል አድርጐ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ከተነሣበት፣ ከትንሣኤውና ከሥጋዌው የሚበልጥ አንዳች ተአምር የለም፡፡ ትውልዱ ቢያስተውል ከአምላክ ሰው መሆን የሚበልጥ ምን ተአምር አለ? (ኢሳ.፯፥፲፬፣፶፫፥፩) ሌላ ተአምር ከመሻት ወደ ልቡና ተመልሶ ወደ ራስ ጠልቆ በመግባት ኃጢአትን አስቦ ንስሓ መግባት እንደሚበልጥ የነነዌ ሰዎችን ታሪክ ስቦ በእምነት የሚፈጽሙት ነገር እንደሚልቅም የንግሥተ ሳባን ታሪክ አንሥቶ አስተምረን፡፡ ላስተዋለ በንስሓ ሥርየትን ማግኘት በእምነትም መመላለስ በየቀኑ በሕይወታችን የሚፈጸም ተአምራት መሆኑን ትመለከታለህን? ለሁሉ ነገር ተአምራትን የሚሻ ሰው ሰይጣንና ክፉዎች በሚፈጽማቸው ምትሐታዊ ተአምራት ተታሎ የመውደቅ ዕድሊ ሰፊ ነው፡፡

ተአምራትን ስለምናደርግ አንድንም

በእምነት ለሚኖር ሰው ተአምራት በቀዳሚነት የሚመጡና የሚነሡ ጉዳዮች ሳይሆኑ እንደ ትርፍና በእምነት ከሚፈጸሙ መልካም ምግባራትም ተካክለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ሁሉ ብናውቅ ተራሮችንም እስከምናፈልስ ድረስ ተአምራትን የማድረግ ስጦታ ቢኖረን ፍቅር (ሌሎችን እንደ ራስ ሲልቅም እንደ ቅዱሳን ከራስ በላይ መውደድ) ከሌለን ከንቱ የከንቱ ነን፡፡ (፩ቆሮ.፲፫፥፩‐፫) ‹‹ሌሎችን የሚወድ ተአምራትን ከሚያደርግ ይበልጣል›› የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግራማ መለኮት በክበበ ትስብእት በሚገለጥበት በዳግም ምጽአቱ ክብርና አግኝተው የመንግሥቱ ወራሽ የስሙ ቀዳሾች የሚሆኑት እነማን እንደሆኑ ሲያስተምረን ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚሉኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችሁም እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ›› ብሎ አስተምሮናል፡፡ (ማቴ.፯፥፳፩‐፳፪)

የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ተአምራትን ከማድረግ እንደሚበልጥ ተመልከቱ፡፡ ሀብተ ትንቢት፣ ሀብተ መርገም ተሰጥቶት የነበረው በለዓለም ስለ ጌታችን ሰው መሆን ‹‹እመለከተዋለሁ፤ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤ ከእስራኤል በትር ይነሣል›› ብሎ ትንቢት ተናግሯል፤ (ዘኅ.፳፬፥፲፩) በዚህ ግን አንደበት በሌለው አህያ ቃል ከመገሠጽ አላዳነውም፡፡ (፪ጴጥ.፪፥፲፭‐፲፮) አጋንንትም እያወጡ ይዞሬ የነበሩ የአስቄዋ ልጆችም በዚያ አልተጠቀሙም፤ ይልቁንም አጋንንት በሰው አድረው እየዘለሉ አቁስለው እስኪሸሹ ድረስ በረቱባቸው እንጂ፡፡ (የሐዋ.፲፱፥፲፫‐፲፱) እንኳን ስመ አጋንንትን እየጠሩ በምትሐት በሚያደርጉት የማታለያ ተአምራት ቀርቶ ክርስቶሳውያን ነን እያሉ ያለ በጐ ሥራ ከጾም፣ ከጸሎትና ከስግደት እንዲሁም ‹‹ክርስቶስን ነን›› ከመምሰል ተራቁተው በሚያደርጉት ተአምራት መዳን አይቻልም፡፡

ምንጭ፡- ‹‹ፍኖተ አርሲሳን›› በመምህር ቢትወደድ ወርቁ፤ ሁለተኛ ዕትም፤ ታኅሣሥ ፳፻፲፫ ዓ.ም