ተንሥኡ!

ሚያዚያ ፲፩፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በከበረና ድንቅ ሥራው ሰውን ሕያው አድርጎ ሲፈጥረው እግዚአብሔር አምላክ እስትንፋስና ሕይወትን ሰጥቶ ካለመኖር ወደ መኖር ባመጣው ጊዜ የሕይወቱን ዘመናት አሐዱ ብሎ እንደጀመረ መጽሐፈ ኦሪት ያወሳናል፡፡ ወደ አፈር እስኪመለስ ድረስም ሞትን አልቀመሳትም ነበር፡፡ ጊዜው ሆነና ግን ሞተ፤ ተቀበረ፤ አፈርም ሆነ፤ በምድር ላይም ታሪኩ እንጂ ሥጋው አልቀረለትም፤ እናስ መቼ ይሆን የቀደመ ክብሩና ጸጋውን አግኝቶ፣ ሥጋውም ከነፍሱ ጋር ተዋሕዳ በሰማያዊት ቤቱ የሚኖረው?

የመጀመሪያው ሰው አዳም የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ሞትን ቀምሷልና የሰው ዘርም ይህ መርገም አልቀረለትም፡፡ የዓለም ፈጣሪና የሁሉ ገዢ እግዚአብሔር አምላክ ዕፅ በለስን በልቶ ሞትን በራሱ ላመጣው ሰው ግን እስከመጨረሻው ቅጣቱን አላጸናበትም፡፡ የልቡን ጸጸት፣ ኀዘንና ልቅሶ ተመልክቶ ራርቶና ይቅር ብሎ ወደ ቀደመ ክብሩ ሊመልሰው ቃል በገበላት በ፶፻፭፻ ዘመን ቃል ሥጋ ሆነና ተገለጠ፤ በጥቂቱም አድጎ በ፴ ዓመቱ ልጅነቱን ላጣው አዳም ፀጋውን ሊመልስለት ጥምቀትን አደረገ፤ ከሰው ጋርም ተመላለሰ፤ አስተማረ፤ ፈወሰ፤ አዳነም፤ በ፴፫ ዓመቱም መከራና ሥቃይን ተቀብሎ በመልእልተ መስቀል ተሰቅሎ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን ተነሥቶ በትንሣኤው ከሞት በኋላ መነሣት እንዳለ ሰውን አበሠረው፡፡ የጌታው መነሣት ለእርሱ በእርሱም እንደሆነ አመለከተው፡፡ እርሱ ሞቶ አልቀረምና በመለኮቱ ኃይል ሞትን ድል አድረጎ ነጻ አወጣው፤ ነፍሳትንም አዳነ፤ ሲኦልንም አራቁቶ ጠላት ዲያብሎስን አሳፈረው፡፡

አዳምም ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ፤ ለብዙ ዘመናት በናፍቆት ያነባላትን ገነት መልሶ አያት፤ በሰላም ኖረባት፤ እስከ መጨረሻውም ሐሴት ያደርግባት ዘንድ በመላው ክብሩ ሊኖርባት እንደሚገባ የአምላክ ቃል የጸና ነው፡፡
ከሞት መነሣት የሰዎች ትንሣኤ መግለጫ ነው፤ ትንሣኤ ስንል መነሣት ማለት ነውና፤ በሰዎች ሕይወት ትንሣኤ በአምስት ዓይነት መንገድ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አስቀድሞ የሚታወቀው ።ትንሣኤ ኅሊና’ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚኖረው ኅሊና ነው፡፡ ሰው በኅሊናው አምላኩ እግዚአብሔርን ያስባልና ሕልውናውን የሚያውቅበትና የሚያወሳበት ነው፡፡

ሰው ከኅሊናው ቀጥሎ ‘ትንሣኤ ልቡና’ ሊኖረው ይገባል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ፣ ሊያውቅና ሊረዳ የሚችለው በልቡናው መንቃት በመሆኑ ለዚህም አንኩሮ ይሰጣል፡፡ በኃጢአት የታወረ ልቡናና ያደፈች ነፍስ በንስሓ ልትነጻ የምትችለው በትንሣኤ ልቡና ነው፡፡

የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ መጨረሻ ሥጋው ከነፍሱ ተለይቶ በመቃብር ከዋለ በኋላ አፈር ይለብሳል፤ ነፍስና ሥጋውም የሚዋሐዱት በዳምግም ምጽአት ነው፡፡ ስለዚህም ‘ትንሣኤ ሙታንን’ ሰው ያስባል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣባት ‘ትንሣኤ ዘክርስቶስ’ ግን ከሁሉ የከበረች ናት፤ በእርሱ መነሣት መርገምት ቀርቶልናልና፤ ከኃጢአት ባርነት ነጻ ወጥተናልና፤ በትንሣኤው ድኅነታችንን አብሥሮናል! ሰው ንስሓ ገብቶ፣ ከኃጢአት ነጽቶና ለሥጋ ወደሙ በቅቶ በክብር ሲሞት ነፍሱ ትድናለችና ሐሴትን ያደርጋል፡፡ ባይሆን ግን በኃጢአት ባርነት ኖሮ ለፍርድ ሲቀርብ የዘለዓለም ሞት ይጠብቀዋልና የሞት ሞትና ይሞታል እንጂ ‘በትንሣኤ ዘጉባኤ’ ለድኅነትና ለክብር አይነሣም፡፡

ተንሥኡ!