ብፁዕ አቡነ አብርሃም አዲሱን መንበረ ጵጵስና ተረከቡ

 

ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

ሊ/ዲ/ ኤፍሬም የኔሰው

abuna abrham 2006የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በመዛወራቸው አዲሱን መንበረ ጵጵስና ተረክበዋል፡፡

ሰኔ1 ቀን 2006 ዓ.ም. የሀገረ ስብከቱ ርእሰ ከተማ በሆነችው ፍኖተ ሰላም፣ በፍኖተ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተዋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ ከተለያዩ አድባራትና ገዳማት የመጡ ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን፣ ከከተማዋ መግቢያ በር ጀምሮ ብፁዕነታቸውን ደመቅ ባለ መንፈሳዊ ሥነ – ሥርዓት ተቀብለዋቸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት “በእንተ ስማ ለማርያም ብዬ የተማርኩበትን አካባቢ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡ ስለሆነም በርካታ መንፈሳዊ የልማት ሥራዎችን በጋራ እንሠራለን” ብለዋል፡፡ መንበረ ጵጵስናው በብፁዕ አቡነ ቶማስ ዕረፍት ምክንያት ለሁለት ወር ክፍት ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ብፁዕ አቡነ ሰላማ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የበላይ ጠባቂ ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ተዘዋውረዋል፡፡ መንበረ ጵጵስናቸውንም ግንቦት 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ተረክበዋል፡፡