ብፁዕ አቡነ ሚካኤል አረፉ፡፡

የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ነሐሴ 8 ቀን 2003 ዓ.ም አርፈዋል። በአንብሮተ እድ ከተሾሙበት ከነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ በአሁኑ ሀገረ ስብከታቸው የተሾሙ ሲሆን በመካከል ለተወሰኑ ወራት የወላይታ፣ ዳውሮና ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።

የሐሞት ጠጠር ሕመም የነበረባቸው ብፁዕነታቸው የቀዶ ጥገና ህክምናቸውን በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በመከታተል ላይ የነበሩ ሲሆን በመካከል ከሰመመናቸው መንቃት ሳይችሉ እንደቀሩ ምንጮቻችን ገልጸዋል። ቀጣይ የአስከሬን ምርመራ ከተደረገ በኋላ ምክንያቱ ሊገለጽ እንደሚችልም ይገመታል።

በቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የተሾሙት የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት አባ ተክለሚካኤል ዓባይ አሁን ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በቀድሞው አድዋ አውራጃ በአምባ ሰነይቲ ወረዳ በላውሳ ቅዱስ ገብርኤል አካባቢ ከአለቃ ዓባይ ወ/ገብርኤልና ከወ/ሮ ታደለች ንጉሤ በ1942 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

በታላቁ በደብረ ዓባይ ገዳም ከመምህር አበራና ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ከመሠረተ ትምህርት እስከ ጸዋትወ ዜማ፣ ከመምህር የኔታ የኋላእሸት መዝገበ ቅዳሴ ጠንቅቀው ከተማሩ በኋላ በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

በዋልድባ ገዳም መዓርገ ምንኩስና ተቀብለዋል፡፡ ጎንደር ክፍለ ሀገር በወገራ አውራጃ በጉንተር አቦ ከመሪጌታ ሐረገወይን፣ ጎንደር ከተማ ከመምህር እፁብ ቅኔ ተምረው ተቀኝተዋል፡፡

በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እያገለገሉ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት በአዳሪነት ገብተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በውጪ አገር እንግሊዝ ለንደን ሴንት ኤድዋርድስ ኮሌጅ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለአንድ ዓመት፣ ግሪክ አገር በአቴንስ ዩኒቨርስቲ ለስድስት ዓመታት ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት በመማር በቲኦሎጂ ማስትሬት ዲግሪ፣ በአሜሪካ ሆሊ ክሮስ በተባለው የግሪክ ሴሚናሪ ከሲስተማቲክ ቲኦሎጂ ዲፕሎማ፣ በቦስተን ዩኒቨርስቲ የኤስ.ቲኤም ወይም በፓስተራል ካውንስሊንግ /ሳይኮሎጂ/ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የእስኮላር ሽፕ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ ገዳማት መምሪያ ኃላፊ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ዲን፣ በወቅቱ የኤርትራ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የዕቅድና ጥናት መምሪያ ኃላፊ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኃላፊ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ፣ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ሐላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነሥርዓት ዛሬ ነሐሴ 10 ቀን 2003 ዓ.ም ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና እንግዶች እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 19ኛ ዓመት ቁጥር 12