‹‹ብርሃን ይሁን!›› (ዘፍ.፩፥፫)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በሥነ ፍጥረት መጀመሪያ ቀን ‹‹ብርሃን ይሁን›› በማለት የተናገረው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ (ዘፍ.፩፥፫) ‹‹ብርሃን ይሁን›› በማለት በተናገረ ጊዜም ጨለማ ተገፈፈ፡፡ መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንደሚነግረን ቅዱሳን መላእክትም ይህ ብርሃን ዕውቀት ሆኗቸው አምላካቸው እግዚአብሔርን ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› በማለት በአዲስ ምስጋና አመሰገኑት፡፡ ‹‹እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ›› ያለ የሰይጣን ክህደትም በብርሃኑ ተጋለጠ፡፡ (ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት)

በቅዱሳት መጻሕፍት አባቶቻችን ብርሃንን መሠረት አድርገው አያሌ ትምህርቶችን አስተምረውናል፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣውን ፈጣሪውን ‹‹እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው›› በማለት አመስግኗል፡፡ (መዝ.፳፮፥፩) ነቢየ ልዑል ቅዱስ ኢሳይያስም የጌታችንን ልደት አስመልክቶ በተናገረበት የትንቢት ክፍል ‹‹በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው›› በማለት በቤተልሔም ዋሻ በከብቶች በረት የተወለደ ጌታችን ብርሃን መሆኑን መስክሯዋል፡፡ (ኢሳ.፱፥፪)

እግዚአብሔር በባሕርይዩ ብርሃን ነው፡፡ ቅዱስ ያዕቆብም በሐዲስ ኪዳን ‹‹መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ›› በማለት የእግዚአብሔርን ብርሃንነት ታላቅነት በግሩም ቃል ያስተምረናል፡፡ በጨለማ አንዳች እንደማይታይ በጨለማ በሚመሰል ክፋት፣ ኃጢአት፣ ቂም፣ በቀል፣ ቅንአት፣ ጠብ በጥቅሉ እግዚአብሔርን በሚያሳዝን ነገር ተሰማርቶ የሚኖር ሰውም መልካም የሆኑ ነገሮች አይታዩትም፡፡ ሐዋርያው ስካርን፣ ዘፋኝነትን፣ ዝሙትን፣ መዳራትን፣ ቅንአትንና ክርክርን የጨለማ ሥራዎች በማለት ይገልጣቸዋል፡፡ (ሮሜ ፲፫፥፲፪-፲፫)

ከዚህም ባሻገር በኑሯችን እንደ ጨለማ ከብደውብን ያሉ ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያለ ሰው ‹‹ያለሁት በጨለማ ውስጥ ነው›› ሲል ሰምተህ አታውቅምን? ጨለማ ባለበት ስፍራ ነገሮች ይሰወራሉ፡፡ ብርሃን በሌለበትም እንፈልጋቸው ብንል መርመስመስ፣ መተረማመስና መገጫጨትን ያስከትላሉ፡፡ በወንጌል እንደተጻፈልን ያች ሴት ድሪምዋ (ጌጥዋ) በጠፋባት ጊዜ የጠፋባትን ጌጥ ፈልጋ ለማግኘት መጀመሪያ ያደረገችው ነገር ቢኖር ብርሃንን ማብራት ነው፡፡ በጽኑ ጨለማ የጠፋን መፈለግ ከንቱ ድካም መሆኑን ተረድታለችና፡፡ (ሉቃ. ፲፭፥፰-፲)

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው መልካም አድርጎ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደሠራቸው እነሆ ይህን ብቻ አገኘሁ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (መክ.፯፥፳፱) መልካም አድርጎ የፈጠረው የሰው ልጅ ግን ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው ከፈጠረው አምላክ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ለሥጋና ለዓለም እንዲሁም ለሰይጣን የተመቸ ሌላ ብልሃትን ፈለገ፤ በዚህም ጥፋትና መከራ አገኘው፡፡ ክርስቲያኖች ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበልነው ብዙ መልካም ነገር አልተሠወረብንም? ምን ሠወረው? የት ተሠወረ? ብዙዎቻችን ‹‹የትናንት ብርታትና ቅንነቴና ሰላሜ ተለይቶኛል›› ስንል እንደመጣለን፡፡ ‹‹ተለይቶኛል፤ ከውስጤ ጠፍቷል›› የምንለው መልካም ነገር ከውስጣችን እንዲገኝ መልካም ነገራችንን የሸፈነውን ጨለማ የሚያስወግድ ብርሃን ያስፈልገናል፡፡ ያም ብርሃን የብርሃናት አባት የተባለ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ በጥንተ ተፈጥሮ አምሳሉ የሆነ ብርሃንን ‹‹ብርሃን ይሁን›› በማለት ተናግሮ በመፍጠር ጨለማ የሰይጣን ክህደትን እንዲሁም በጨለማ የተመሰለ አለማወቅን እንዳጠፋ በሕይወታችንና በኑሯችን ጨለማ ሆነው የጋረዱን እንዲወገዱ ዛሬም ‹‹ብርሃናችሁ እኔ ወደ ሕይወታችሁ ልግባ በኑሯችሁ ልንገሥ›› ይለናል፡፡ እርሱ ወደ ሕይወታችን ሲገባና በልቡናችን ሲነግሥ ጨለማው ይደረመሳል፡፡ ጌጥዋ በጠፋበት ሴትም እንደሆነው ጠፋ የተባለው ነገር በእርሱ ብርሃንነት ይገኛል፡፡ ብርሃን በምልዓት ሳለ ቡላድ ካልመቱ እንደማይገለጥ፤ ብርሃን እግዚአብሔርም በሕይወታችን እንዲገለጥ ቡላድ ያስፈልገዋል፡፡ ቡላዱ ቤቱ ወደ ተባለች ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ ነው፡፡ አምላካችን እንደተናገረው የእርሱ የምሕረት ዓይኖቹ ለጻድቃን ጸሎት ክፍት የሆኑ ጆሮዎቹም ይቅርታውም ቸርነቱም የሚገኙት በቤቱ ነውና፡፡ (፪ዜና. ፯፥፲፭፣መዝ. ፭፥፯፣ መዝ. ፺፩፥፮፣ ፩ጢሞ.፫፥፲፭)

የእውነት ቃሉን ፈልገን፣ እርሱን ተጠምተን ትኩረታችንን በሰዎች ላይ ሳይሆን በእርሱ ላይ አድርገን ከቀረብን ከቤቱ ቅዱስ ቃሉን እንማራለን፤ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው›› በማለት እንደተናገረውም ቅዱስ ቃሉ ብርሃን ነውና ብርሃን ወደ ሆነ ወደ እርሱ ይመራናል፡፡ (መዝ.፻፲፰፥፻፭) እርሱ ባወቀም ከቤቱ በረከትን እንጠግባለን፡፡ ‹‹ከቤትህ በረከት እንጠግባለን ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው፤ በጽድቅም ድንቅ ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (መዝ.፷፬፥፬-፮) ብርሃንን የሚገልጡልን ወደ ብርሃን ወደ እግዚአብሔር የሚመሩን ቡላዶች የእግዚአብሔር ቅዱሳን ናቸው፡፡ ‹‹ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለ አባታችሁን እንዲያከብሩት ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ›› በማለት የተናገረውን ቃል በእምነት ተቀብለው በእምነታቸው፣ በትሕትናቸው፣ በፍቅራቸው፣ በትዕግሥታቸው ፋናነት በኑሯችን ያለ ጨለማን አስወግደው ሕይወታችንን ወደ እግዚአብሔር ያደርሱታልና፡፡ (ማቴ. ፭፥፲፬-፲፮) መጽሐፍ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፤ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው፡፡›› እንዲሁም ‹‹እንደተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ›› ያለው ለዚህ ነውና፡፡ (ዕብ.፲፫፥፯፣ኤፌ.፭፥፩) ለቅዱሳን ‹‹ብርሃናችሁ›› የተባለ እግዚአብሔር አይደለምን? ጨለማ የወረሰውን ሩጫውን ያልፈጸመውን ገና በዚህ ዓለም በመፍገምገም ያለውን ሰው እየተመለከትህ ለምን ጨለማው ይወርስሃል? ይልቁንም የእግዚአብሔር ብርሃንነት በገጸ ነፍስህ እንዲበራና የነፍስህ ጨለማ ኃጢአት እንዲጠፋልህ ብርሃን አምላካቸውን በእምነትና በበጎ ሥራ በመሸለም የገለጡ ቅዱሳንን ተመልከት፤ ወደ እነርሱም ቅረብ፡፡

በመጽሐፍ እንደተነገረን የእግዚአብሔር ቅዱሳን በገቡበት ከተማና ስፍራ ሁሉ የጨለማ ሥራ ይወገድ ነበር፡፡ የካዱ ሲያምኑ፣ የወደቁ ሲነሡ፣ የተሰበሩ ሲጠገኑ፣ በአምልኮተ ጣዖት የነበሩ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲመለሱ አንብበናል፡፡ (የሐዋ. ፭፥፲፫-፲፮፣፲፫፥፵፮-፵፰) ደካማ ሰዎችን ተመልክተህና በእኩይ ምግባራቸው ተሰነካክለህ በዚህም ምክንያት አንተም በአጉል ልማድ ተይዘህ ሊሆን ይችላል፡፡ አንባቢ ሆይ በዚያ ምን ተጠቀምህ? ምን አተረፍክ? ውስጥህ ሰላምን አግኝቷል? መልስህ አዎንታዊ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለሆነም ዓይንህን በጨለማ ሥራ ካሉ ሰዎች አንሣና ብርሃን እግዚአብሔር ወደሚነበብባቸው ብርሃናት ወደ ቅዱሳን አድርግ፤ ዜና ገድላቸውን አንብብ፤ በሕይወትህ የጎደለህን ትዕግሥት፣ ርኅራኄ፣ ቸርነት፣ ብርታትና ተስፈኝነት ከሕይወታቸው ታገኛለህ፡፡ በእነዚህም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች መሰላልነት ወደ ፈጣሪህ ትደርሳለህ፡፡ ሐዋርያው ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር ደስታ ሰላም ትዕግሥት ቸርነት በጎነት እምነት የዋኅነት ራስን መግዛት ነው፡፡ እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም›› በማለት የሰላም መሠረት የሆኑትን እነዚህን ፍሬዎች ከዘረዘረ በኋላ እነዚህንማ ማን ሊፈጽማቸው ይችላል? እንዳንል ‹‹የክርስቶስ የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ›› ብሎ ቅዱሳንን አብነት አድርጎ አነሣልን፡፡ (ገላ.፭፥፳፪-፳፫)

መልካምነት ብርሃን ነው፤ እግዚአብሔር ‹‹ብርሃን ይሁን›› ብሎዋልና ክፋትን ትተን መልካምነትን እንያዝ፡፡ ያለ መልካምነት መልካም ነገሮችን ማግኘት አይቻልም፡፡ ላጨለሙብን አናጨልም፤ ጨለማ በብርሃን እንጂ በጨለማ አይጠፋምና፡፡ ቂም ጨለማ ነው፤ በቀልም ድቅድቅ ጨለማ፡፡ ሌብነት ጨለማ ነው፤ መዝረፍ ጉቦን በልቶ ፍትሕን ማዛባትም ድቅድቅ ጨለማ፡፡ ያመኑንን ማታለል ጨለማ ነው፤ አሳልፎ መስጠትም ድቅድቅ ጨለማ ነው፡፡ ስለሆነም ቂምና በቀልን በይቅርታ ብርሃን እንዲሁም ሌብነትንና ዘረፋን በታማኝነት ብርሃን እናጥፋው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት ይጠብቀን!

ይቆየን!