ብርሃንህን ላክልን!

ታኅሣሥ ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ይህች ዓለም ከንቱ ገፍታ ብትተወኝ
ሥቃይን አብዝታ እጅጉን ብታስመርረኝ
መከራዬም በዝቶ መላ ቅጡ ቢጠፋብኝ
በውስጤ ባስብ “እንዴት ልሁን?” እያልኩኝ
ልቤ ተሸበረ በኀዘንም ተከበብኩኝ!

ድቅድቁ ጨለማ ተጋርዶ ከፊቴ
ሰላም ቢያሳጣኝ ካለሁበት ቤቴ
ነፍሴን ካስጨነቃት ጥንቱ ጠላቴ
በእስራቱ ኖርኩኝ ጸንቶ ፍርሃቴ
ከልጅነት ጸጋ ለይቶኝ ከአባቴ

ምንኛ ያስከፋል ይህስ የሰው ነገር
በሰላም በፍቅር ሲቻለን መኖር
እሾህና አመኬላ አብቅላብን ምድር
የሰቀቀን ኑሩ ሆነብን ሕይወታችን
የት አለ ሰላማችን? የት ይሆን ብርሃንናችን?

ሰዎችን እንለምን እንጩህ በአንድነት
ፈጥሮ ለማይተወን አምላክ በጸባዖት
እንበለው “ማረን! ይቅር በለን በእውነት!
አውጣን ከጨለማ ከዚህች ዓለም ክህደት
ብርሃንህንም ላክልን ከሰማይ ቤት!”