በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ከጥቅምት ፲፪ እስከ ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ .. ድረስ የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አስመልከቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

 1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ሆኖ ለምልዓተ ጉባኤው የቀረበው መልእክት በቀጣይ በቤተ ክርስቲያናችን ለሚከናወነው መንፈሳዊውም ሆነ ማኅበራዊ ተልዕኮ ጠቃሚነቱ የጐላ በመሆኑ ጉባኤው የሥራ መመሪያ አድርጐ ተቀብሎታል፡፡
 2. የሀገር ሰላምን ጉዳይ አስመልክቶ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትና የዜጎች ንብረት መውደም፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ ያሳዘነ ሲሆን፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰላምን እንዲያስከብር፣ የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ እንዲያደርግ፣ የተፈናቀሉትም ወደቀያቸው እንዲመለሱና ለጠፋው ንብረታቸው ማቋቋሚያ እንዲደረግላቸው፣ በተለይም በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለው ስደትና መከራ ጐልቶ እየታየ በመሆኑ የጥፋቱ መልእክተኞችን መንግሥት በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ እያሳሰበ መንግሥትም ለሕዝቡ ብርታት የበኩሉን ጥበቃ እንዲያደርግ፣
 3. በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወነውን መንፈሳዊም ይሁን ማኅበራዊ ተግባራት በአግባቡ ማስተላለፍ እንዲቻል የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት በመምሪያ ደረጃ እንዲቋቋም፣
 4. በአገራችን በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተከታዮች በቋንቋቸው ማስተማርና ማገልገል እንዲቻል በየአህጉረ ስብከቶቹ የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር ከልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች አገልጋዮችን ማፍራት እንዲቻል ለትምህርት ቤቶቹ ማጠናከሪያ የሚሆን ቋሚ በጀት እንዲመደብ፣ በቀጣይም በሁሉም አፍ መፍቻ ቋንቋ በማዕከል ማሠልጠኛ እንዲቋቋም፤
 5. የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በአገራችንና በአፍሪካ ጭምር ያበረከቱት የሰላም ተልዕኮ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው፣ በተለይም ለአገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ እውቅና ያስገኘላት ቀድሞም የነበረ ክብሯን አጉልቶ ያሳየ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አድናቆቱን ገልጿል፡፡ ለወደፊቱም ለአገራችን እድገትና ብልጽግና በመንግሥት በኩል ለሚሠራው ማኅበራዊና ልማታዊ ሥራ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ትቀጥላለች፡፡
 6. አገራችን ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት አቅጣጫ በስፋት ለማስቀጠልና በተለይም ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ በእጅጉ ተስፋ የተጣለበት የዓባይ ግድብ በተያዘው የግንባታ ሥራ ተፋጥኖ ግድቡ እንዲጠናቀቅና ሥራ እንዲጀምር ለማስቻል መላው የአገራችን ሕዝቦች አስፈላጊውን ዕገዛ በማድረግ እንዲቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
 7. የቤተ ክርስቲያናችንን አጠቃላይ መሪ እቅድ በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ወደተግባር እየተገባ መሆኑን ጉባኤው ከቀረበው ሪፖርት አዳምጧል፡፡ በቀጣይም ሥራው ተፋጥኖ እንዲቀጥልና ከካህናት ከምእመናን ከወጣቱም ጭምር የሚቀርቡ ወቅታዊ አቤቱታዎች በመሪ እቅዱ እየተጠኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡
 8. በግንቦቱ ርክበ ካህናት በቤተ ክርስቲያናችን የተቋቋመው አገራዊ የሰላምና የእርቅ ኮሚቴ የአራት ወራት ሪፖርት ለጉባኤው አቅርቧል፡፡ ኮሚቴውም ያከናወነው የሰላም ተልዕኮ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎ በቀጣይም ኮሚቴው ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከወጣቶች የተውጣጡ አባላትን አካቶ የሰላምና የእርቅ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ፣ ለዚህም የሚሆን አስፈላጊ በጀት መድቧል፡፡
 9. በአገራችን በኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና ስደት ላይ በመነጋገር በጣም ለተቸገሩ ወገኖች በጊዜያዊነት የሚደርስ ምግብና አልባሳት ለማቅረብ እንዲቻል አስፈላጊውን ገንዘብ እንዲመደብ፣ በቀጣይም በክልሉ ይህንን ችግር እየተከታተለ ዘለቄታዊ ርዳታ የሚያሰባስብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
 10. የጌዴኦና ቡርጂ ዞኖች እስከአሁን ድረስ በሲዳማ ሀገረ ስብከት ሥር ሆነው መንፈሳዊውን አገልግሎት ሲያገኙና ሲተዳደሩ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ራሱን ችሎ ሀገረ ስብከት እንዲሆንላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ራሱን የቻለ ሀገረ ስብከት እንዲሆን ተወስኗል፡፡
 11. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ግኑኝነት መምሪያ በቀረበ ሪፖርት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት የነበረው ጥንታዊ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
 12. በስዊድን ሀገር ሶደርቴሌ ከተማን ማእከል ያደረገ የቅዱስ አግናጥዮስ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ሴሚናሪ በመላው አውሮፓ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን እና አገልጋይ ካህናት ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ የአብነት ትምህርትና ዘመናዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነገረ መለኮት ስልጠና የሚሰጥ ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ዕውቅና እንዲያኝ ተወስኗል፡፡ አገልግሎቱን በስፋትና በብቃት እንዲያከናውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የዕውቅና ደብዳቤ እንዲደርሰውም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
 13. የ፳፻፲፪ ዓ.ም በጀት ዓመት የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ በጀት አስመልክቶ ከበጀትና ሂሣብ መምሪያ በቀረበው እቅድ ላይ በመነጋገር የቀረበው በጀት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የ፳፻፲፪ ዓ.ም. በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡
 14. በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ችግር እንዲያበቃ እግዚአብሔር አምላክ ምህረቱን እንዲሰጠን የተጀመረው ሱባኤ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡

ጥንታዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የአገር ባለውለታ እንደመሆኗ ሁሉ ወደፊትም በአገራችን ኢትዮጵያ በመንግሥትና በሕዝቡ ትብብር ለአገር አንድነትና ለዜጎች መብት መከበር፣ ለሰው ልጆች እኩልነት ለሚደረገው አገራዊ ጥረት የበኩሏን አስተዋጽኦ ከማድረግ አትቆጠብም፡፡

ሆኖም ለዚሁ አገራዊ ስኬት ከሁሉም በላይ በዜጎች መካከል መከባበርና ሰላማዊ አንድነት መኖር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያምናል፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ለአገራዊ አንድነታችን ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አምናችሁ በአንድነት በሰላምና ተከባብሮ በጋራ ለመኖር፣ ለመሥራትም ሆነ ሠርቶ ለመበልፀግ አገራዊ አንድነታችሁን እንድታጠናክሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የአገራችን መንግሥትም የአገር ሰላም፣ የዜጎች ደህንነትና በሰላም ወጥቶ መግባት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን፣ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በምንም መልኩ በከንቱ መጥፋት የሌለበት መሆኑን ተገንዝቦ፣ ሰላምን የማስከበሩን፣ አገር የመጠበቁንና ዜጎችን በአገራቸው በእኩልነት ተሳስበው የሚኖሩበትን መንገድ በመቀየስ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም ከጥቅምት ፲፩ እስከ ፳፬ ቀን ለ፲፫ ቀናት በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰላም ተጠናቅቆ በዛሬው ቀን በጸሎት ተዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ