በጎ ኅሊና

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በዓለም የምናያቸው መልካምም ሆኑ ክፉ ነገሮች ሁሉ መነሻቸው ሐሳብ መሆኑን ስናስተውል ኅሊና ምን ያህል ታላቅ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ኅሊና የሚለው ቃል ሐሳብ፣ ምኞት፣ ከልብ የሚመነጭ ሐሳብ ማለት ነውና፡፡ በሰው ልጆችም የአእምሮ ሥራ ሂደት ውስጥ ሐሳብ ሲደጋገም ወደ አመለካከት፣ ከሐሳብ የተነሣ አመለካከት ሲያድግም ክፉ ወይም በጎ ወደ ሆነ ማመን፣ አንድ ሰው ከሐሳቡ ወደ ማመኑ የደረሰበት መንገድም ማንነቱን እንደሚወስኑት ባለሙያዎች ያስተምሩናል፡፡ ከሐሳባችን ተነሥቶ ወደ ማንነታችን የደረሰ ነገርም ፍጻሜያችንን ይወስነዋል፡፡ ኅሊና ምኞት ነው መባሉም መልካም ነገርን በውስጣችን የምንመኝ ከሆነና ለመልካሙ ነገር የምንተጋ ከሆነ መጽሐፍ ‹‹ለጻድቃን ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች›› ብሎ እንደተነገረ የምኞታችንን (የበጎ ኅሊናችንን ውጤት) እናገኛለን፡፡ በአንጻሩም ምኞታችን ሁልጊዜ ክፉ ከሆነ የምኞታችን ውጤት ክፉ ነገር ይደርስብናል፡፡ (ኪወክ መዝገበ ቃላት ገጽ ፬፻፸፮፣ ምሳ. ፲፥፳፬፣መዝ.፻፲፰፥፻፲፰፣ዘኁ.፲፩፥፴፬)

በጎ ኅሊናን ገንዘብ ማድረግ እንደሚገባ በሥነ ልቡና፣ በሥነ አእምሮና በፍልስፍና ዘርፎች ብዙ ሲባል እንሰማለን፡፡ በጎ ኅሊና ያለው ሰው በማናቸውም ፈታኝና ደስ የማያሰኙ ሁኔታዎች ውስጥ መልካም ነገሮች ላይ ያተኩራል፤ እግዚአብሔርንም ተስፋ ያደርጋል፡፡ የሥነ ልቡናም ሆነ የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በጎ ኅሊና በአካላዊም ሆነ በአእምሮአዊ ጤና ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ዛሬ በእጅጉ እየተስፋፉ ላሉ ተላላፊ ላልሆኑ ሕመሞች (እንደ ደም ግፊት፣ ጭንቀትና ድብርት የመሳሰሉት) እንደ መነሻ ከሚነሡ አያሌ ምክንያቶችም መካከል አንዱ ክፉ ኅሊና (አሉታዊ አስተሳሰብ) ነው፡፡ ሰው በጎ ኅሊናን (አዎንታዊ አስተሳሰብን) ሲያጎለብትና ገንዘብ ሲያደርግ ልዑል እግዚአብሔር የሰጠውን የአእምሮው ድብቅ ችሎታ በአግባቡ ይጠቀምበታል፡፡ በግላዊ፣ በማኅበራዊና በሌሎችም መስተጋብሮች ለሚፈጠሩ ችግሮችም መፍትሔ የመስጠት አቅም እድገቱም ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ በየዕለቱም ከሚሰማው የጨፈገገ ስሜትና ሐሳብ ማምለጫ አንዱ መንገድ በጎ ኅሊና ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚታየው ሰው በጎ ኅሊናን ከመያዝ ይልቅ ወደ ክፋትና ጠማማነት ሲያዘነብልና እነርሱንም የሙጥኝ ሲል ይስተዋላል፡፡

በጎነት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፡፡ ዛሬ በብዙ መንገድ ቀናነትና በጎነት ስለጎደለ ማኅበራዊ አኗኗራችን በእጅጉ እየተበላሸ ለመሆኑ አያሌ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይህን ጽሑፍ የምታነቡ አንባቢያን ሆይ! አንድ ወዳጃችሁ መንገድ ላይ ሳያናግራችሁ  ቢያልፍ ምን ይሰማችኋል? ምን አልባትም በሐሳብ ተወጥሮ ወይም ደግሞ አንዳች ኅሊናን የሚያውክ ነገር ገጥሞት ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ? ወይስ ‹‹ንቀት ነው››‹‹ገንዘብ ካገኘ ዝናን ከተጎናጸፈ በኋላ ሰውን ቸል ማለት ጀምሮዋል›› ብላችሁ ትደመድማለችሁ?  ወዳጃችሁ የስልክ ጥሪያችሁን ባያነሳላችሁስ ምላሻችሁ ምን ይሆን? ‹‹ምን አልባትም ተኝቶ ይሆናል ወይም ደግሞ ስልክ መመለስ በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሊሆን ይችላል›› ብላችሁ ታስባላችሁ ወይስ ‹‹ይኸው የንቀቱ ጥግ እዚህ ደርሶአል!›› ብለህ ባላወቅኸው ትፈርዳለህ? ይህን እንደ ምሳሌ አነሣን እንጂ በጎነትና ቀናነት እየጎደለን ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ (ገላ.፭፥፳፪)

በጎ ኅሊናና ቅን ልቡና ያለው ሰው በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘ እንደሆነ ካወቀ በጉዞው የሚገጥሙትን ክፉ ነገሮችን እንኳን በመልካም ይተረጉማል፡፡ በክፉ ሥራው ክፉ ነገር ከገጠመውም ከክፉ ሥራው ተቆጥቦ ቆሞ በማሰብ በገጠመው ክፉ ነገር ተምሮ ራሱንም መርምሮ ራሱን ያርማል፡፡ የክርስትና ሕይወት ትልቁ ተጋድሎና ጥረትም በጎ ኅሊናንና ቅን ልቡናን ገንዘብ ለማድረግ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በግብረ ሐዋርያት ‹‹ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ኅሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ›› በማለት የተናገረውም ይህንኑ ያስረዳናል፡፡ በጎ ኅሊናን ገንዘብ ማድረግ ተጋድሎን ይጠይቃል፡፡ ያለ ተጋድሎ በጎ ኅሊናን ገንዘብ ማድረግ አይቻልም፡፡ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ገንዘብ ሊያደርጋት በእጅጉ ይተጋላት የነበረችውን በጎ ኅሊና ደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስም ገንዘቡ ያደርጋት ዘንድ ሊተጋ እንደሚገባው ሲያስተምረው ‹‹እምነትና በጎ ኅሊና ይኑርህ፤ አንዳንዶች ኅሊናን ጥለው መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና›› በማለት ጽፎለታል፡፡ (የሐዋ.፳፬፥፲፮፣ ፩ጢሞ.፩፥፲፱)

ያለ በጎ ኅሊና መመላለስ መሪ በሌለው መርከብ በባሕር ላይ እንደ መጓዝ ነው፡፡ መሪ የሌለው መርከብ በውስጡ ያሳፈራቸውን ሰዎችና ንብረታቸውንም ጭምር ይዞ በባሕር እንደሚሰጥም በጎ ኅሊናን ሳይዝ በዚህ ዓለም የሚመላለስ ሰውም ራሱንም በዙሪያው ያሉትንም ሰዎች ይዞ በዚህ ዓለም ክፉ ነገር ተሸንፎ በክፋት ይሰጥማል፡፡ ከበጎ ኅሊና ርቆ ክፉ ኅሊናን አጥብቆ የያዘ ሰው ለማንኛውም ጉዳይ መነሻ የሚያደርገው ክፉ ነገርን ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ለንጹሓን ሁሉ ንጹሕ ነው›› በማለት እንዳስተማረው በጎ ኅሊና ያለው ሰው ማናቸውንም ነገር ከበጎ ተነሥቶ ይመረምራል፤ ካለው እንጂ ከሌለው ከጨበጠው እንጂ ከመሰለው አይነሣም፡፡ (ቲቶ.፩፥፲፭)

ጠቢብ ሰው ከስድብ መልካም ነገርን ያወጣል፡፡ ስድብ ተሳዳቢውን ያረክሳል፡፡ ተሳዳቢውን የሚያሳፍርበትና የሚያዋርድበት ደረጃ ግን እንደ ተሰዳቢው አቀባበል ይወሰናል፡፡ ስድብን ራስን እንደ መመልከቻ መስተዋት፣ ውስጥን እንደ መመርመሪያ መሳሪያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይኸውም ሊሆን የሚችለው በጎ ኅሊና ቀና አስተሳሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ፈጣሪውን በብዙ መንገድ እንዳስደሰተ ሁሉ በፈጸማቸውም ክፉ ነገሮች እግዚአብሔርን አሳዝኖታል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በፈጸማቸው ስሕተቶች ንስሓ ለመግባት የንስሓ ዕንባን ለፈጣሪው መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ እጅግ ፈጣን ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ነቢዩ ዳዊት በንግሥና ዙፋን በነበረበት ጊዜ ሳሚ የሚባለው ሰው  ‹‹ሂድ አንተ የደም ሰው ምናምንቴ›› እያለ እየደጋገመ ይረግመው ጀመር፡፡ በዚህም ሳያቆም በሕዝቡና በኃያላኑ ፊት ድንጋይንም ይወረወርበት ነበር፡፡  አናንተ በዳዊት ቦታ ብትሆኑ ምን ታደርጉ ነበር? ሰው በተሰበሰበበት እንዲህ ብትሰደቡ ምን ይሰማችሁ ነበር? ነቢዩ ዳዊት ይህን ሁሉ ርግማን እንዴት አድርጎ በመልካም እንደቀየረው የምንረዳው የጽሩያ ልጆች  ለእርሱ በመቆርቆር ‹‹ይህ የሞተ ውሻ (ሳሚ) ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሂድና ራሱን ልቁረጠው›› ባለ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ጠቢብ ሰው ከስድብ መልካም ምክርን ሊያወጣ መቻሉን በተግባር ተርጉሞ የጽሩያ ልጅ ‹‹እናንተ የጽሩያ ልጆች እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር ዳዊትን ስደበው ብሎ አዞታልና ይርገመኝ››  ማለቱን ስንመለከት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ነገሩን በትዕግሥት ባያልፈውና የተቆረቆረሉትንም ሰዎች አነሣሥቶ ‹‹ሂዱ ቁረጡት ፍለጡት›› ቢል ኖሮ ምን ዓይነት ደም መፋሰስና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ይከሠት እንደነበር መገመት አዳጋች አይሆንም፡፡ ዳዊት ይህን እንዴት አደረገ? ብንል መልሱ ‹‹የበጎ ኅሊናና የቅን ልቡና ውጤት ነው›› የሚል ነው፡፡ (፪ሳሙ.፲፮፥፭)

ዛሬ በከተማችን የሞሉ የትርጉምና ሀገር በቀል መጻሕፍት የምናነብ ሰዎች ከመጻሕፍቱ በሸመደድናቸው  ልብ የሚነኩ ሐረጋትና ቃላት ‹‹ብልህ ሰው የሚወረወርበትን ድንጋይ ለቅሞ ቤት ይሠራበታል፤ ሞኝ ሰው መልሶ ይወራወርበታል፡፡›› እንዲሁም ‹‹ታላቅ ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይታየዋል፣ በውድቀት ጊዜ መነሣትን ተስፋ ያደርጋል፤ በሕመሙ ጊዜ ጤናን ተስፋ ያደርጋል፤ በማጣትም መካከል በእጁ ያሉ ነገር ግን ደግሞ የማይስተዋሉ ሀብቶቹን ይመለከታል›› ብንልም በተግባር ስንፈተንባቸው ግን የለንባቸውም፡፡ ነቢዩ ዳዊት ግን ሁሉን በተግባር ተርጉሞ አሳየን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከአባቶቻችን አኗኗር  ፈልገን የምናጣው አንዳችም መልካም ነገርና ጥበብ የለም የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ እስቲ እናስተውል! ቅኑ ሰው ዳዊት ክፉን ነገር በመልካም ኅሊና በቅን ልቡና እንተርጉም ካልን እስከምን መድረስ እንደምንችልና በዚህም ክፉና አጥፊ  ውጤቶችን ማስቀረት እንደሚቻል ሊያስተምረን እንጂ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ሳሚን ‹‹ሂድና ዳዊትን ስደብ›› ብሎ ያዝዛልን? ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በሳሚ ስድብ ውስጥ ራሱን ተመለከተ፡፡ ርግማኑና ድንጋይ ውርወራው ተሳዳቢውና ድንጋይ ወርዋሪውን ሳሚን ቢያረክሰውም ዳዊት ግን እግዚአብሔርን የበደለውን በድል አስቦ ‹‹እንዲህ መባል ይገባኛል›› በሚል ድምፀት ‹‹ተዉት ይስደበኝ›› በማለት ስሕተቱን ተመልክቶ የነገር እሳቱን አበረደበት፡፡ ለኃጢአቱም እንደ ቀኖና አድርጎ ቆጠረው፡፡  ፈጣሪህ ብቻ ሊፈርድብህ እንደሚቻለውና እንደሚገባው ብታውቅም በስውርም ይሁን በግልጽ በፈጸምከውና አንተ ብቻ በምታውቀው በደልህ ኃጢአትህና ክፉ ሥራህ ያን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሰዎች ያን ክፉ ተግባር አንሥተው ቢናገሩህ ‹‹ንጹሕ ነኝና አትንኩኝ›› ትላለህ ወይስ ‹‹እግዚአብሔር ባወቀ ስለ ክፉ ሥራዬ ንስሓ እንድገባ እየገሠጸኝ ነው›› ብለህ ራስህን ትመለከታለህ?

እጅግ ከለመድናቸውና እንደቀልድ ከምንናገራቸው ንግግሮች ‹‹መልካም ኅሊና ምቹ ትራስ ነው›› የሚለው እጅግ ልናስተውለው የሚገባ መልካም ሐሳብ ነው፡፡ ቅን ኅሊናን ገንዘብ ያደረገ ሰው ጉዳዮችን ከቅንነት ተነሥቶ ስለሚመዝናቸው እንቅልፍ አያጣም፡፡ ቃየል የገዛ ወንድሙን አቤልን ስለምን ገደለው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ የሚሆነው በጎ ኅሊናን ማጣቱ ነው፡፡ ቃየል ኅሊናውን ከመነሻውም በክፋትና አፍራሽ በሆኑ ሐሳቦች ስላጠረው እግዚአብሔር ይሆንለታል ብሎ የሰጠውን ስጦታ ከመናቁም በላይ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን እንዲያቀርብ በታዘዘ ጊዜ እንኳን ‹‹እግዚአብሔር አይበላው›› በማለት አሰስ ገሰሱንና እንክርዳድ የተቀላቀለበትን መሥዋዕት በግዴለሽነት አቀረበ፡፡ መሥዋዕቱም ሆነ መሥዋዕቱን ያቀረበበት ልቡናው የተጣመመ ኅሊናውም የቆሸሸ በመሆኑ ምክንያት እግዚአብሔር መሥዋዕቱን ባልተመለከተ ጊዜ እንኳን ከወንድሙ ተምሮ ከስሕተቱ ተመልሶ ንስሓ በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቅ ሲገባው መሥዋዕቱ ተቀባይነት ባገኘለት በወንድሙ አቤል በክፋት ተነሣስቶ ገደለው፡፡ ቃየል በአቤል እንዲነሣበትና እንዲገድለው ያደረገው መነሻ ክፉ ኅሊና ነው፡፡ ክፉ ኅሊና (አሉታዊ አስተሳሰብ) ሲሠለጥን ከሌሎች ጋር የሚኖረንን ማኅበራዊ ኑሮ፣ ትዳራችንን፣ ሥራችንን፣ ጓደኝነትን ሁሉ ያበላሻል፡፡ (ዘፍ.፬፥፩-፲)

በጎ ኅሊናን እንዴት ማሳደግ ይቻላል?

በጎነት እየታጣ ባለበት በዚህ ዘመን በጎ ኅሊናን መያዝና ማሳደግ ብርቱ ተጋድሎን ይጠይቃል፡፡ የበጎ ኅሊና በረከትና ይዞ የሚመጣውም መልካም ነገር እጅግ ብዙ ስለሆነ እንተጋለት ዘንድ መጻሕፍት በስፋት ያስተምሩናል፡፡ በክርስትና ትምህርት እንደምንረዳው ክርስትና በየዕለቱ እያደጉ የሚሄዱበትና በሂደትም መልካም ፍሬን የሚያፈሩበት ጉዞ ስለሆነ በአንድ ጀምበር በአስተሳሰባችን ላይ ተአምራዊ ለውጥ ካላመጣን ብለን መጨነቅ ተገቢ አይሆንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ‹‹ስለዚህ ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ በበጎነትም እውቀትን ጨምሩ በእውቀትም ራስን መግዛት÷ ራስንም በመግዛት መጽናትን÷ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል÷ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ÷ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ›› በማለት መናገሩም የክርስትና መንፈሳዊ ሕይወት ቀስ በቀስ እያደጉና መልካም ነገር እየጨመሩ ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚጓዙበት መንገድ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዳስቀመጠልንም በጎነት (በጎ ኅሊና – አዎንታዊ አስተሳሰብ) የመልካም ነገር ሁሉ መሠረት ነው፡፡ እግዚአብሔርን በማመን ላይ የተመሠረተ መልካምነትና በጎነት ወደሚፈለገው ታላቅ ሰብእና ያደርሳል፡፡ ክርስቲያን በጎ ማሰብ መልካም ማድረግ የሚገባው ‹‹ፍርድና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖረም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም›› በሚል መልካም በሚመስል ነገር ግን ደግሞ እጅግ አደገኛ መርሕ ተመሥርቶ ሊሆን አይገባውም፡፡ ደግነት በማናቸውም ሚዛን ቢሆን ከክፋት ጋር የሚመዛዘንበት አንዳች ነገር ባይኖርም  የፍርድና የኩነኔ ጉዳይ (ምጸአተ ክርስቶስ) ግን ‹‹ሊኖርም ላይኖርም ይችላል›› የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ እንግዲህ ቅዱሳት መጻሕፍት በጎነትን ማሳደግ ይገባል ካሉን እንዴት እናሳድገው የሚለውን ጥያቄ አንሥቶ ጥቂት ነጥቦችን መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ (፪ጴጥ.፩፥፭-፱)

. በጎ ኅሊና – አዎንታዊ አስተሳሰብ መልካም ነገር እንደሚስብና እንደሚያመጣ ማወቅ ማመንም  

በማናቸውም ሁኔታ በጎ ማሰብ ማለት የተከሠተን ክፉ ነገር እንዳልተፈጠረ አድርጎ ማሰብ  ወይም ደግሞ ችግሮች ተፈጥረው ሳለ ችግሮቹን መሸምጠጥ ማለት ሳይሆን በኑሯችን የሚገጥሙን እነዚህ ክፉ ነገሮች እግዚአብሔር በቸርነቱ ‹‹ከእኔ ጥቂት ጥረት ጋር ወደ መልካም ይለውጣቸዋል›› ብሎ ተስፋ ማድረግ ነው፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የገዛ ወንድሙን አቤልን በግፍ የገደለ ቃየል በክፉ አሳቡ መነሻነት ፊቱ በጠቆረ ጊዜ ‹‹ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው÷ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት›› በማለት የተናገረውም ቃል በጎ ኅሊናና (አዎንታዊ አስተሳሰብ) ውጤቱ የሆነው መልካምነት ብሩህ ሕይወት፣ ደስታና የኅሊና ሰላም እንደሚያሸልም ያስገነዝበናል፡፡ መልካምነት ወጪ ሳይኖረው የሚያተርፉበት መልካም ንግድ ነውና፡፡ (ዘፍ.፬፥፮)

. ለፈቃደ እግዚአብሔር በመገዛት መትጋት

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ኅሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ›› (የሐዋ 24፡16) ብሎ እንተናገረው በጎነት እየጎደለውና እየጠፋበት ባለ ዓለም  በጎ ኅሊና ያለ ትጋት አይገኝም፡፡ ‹‹ጠማማ ልብ ያለውም ሰው መልካምን አያገኝም›› እንደተባለውም በጠማማ ኅሊና፣ በአሉታዊና አፍራሽ አስተሳሰብ እየተመላለስን መልካም የሆነ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን እንዴት ማግኘት እንችላለን? (ናሆ.፩፥፯፣ ምሳ.፲፯፥፳)

ስለሆነም በሥጋዊ ኑሯችን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልናሳካቸው ስለምንፈልጋቸው ነገሮች ፈጣሪያችንን በጾም በጸሎት በስግደት እንደምንማጸነው ጉጉታችን እጅግ ከፍ ሲልም ‹‹ይህን ብታደርግልኝ ይህን አመጣልሃለሁ›› ብለን በስእለት እንደምንማጸነው የመልካም ነገር ሁሉ መሠረት የሆነውን በጎ ኅሊናና ቅን አስተሳሰብ እንዲያድለንም በጾምም በጸሎትም በመውደቅ በመነሣትም በስእለትም ጭምር ደጅ ልንጠና ይገባናል፡፡ አምላካችን እንደተናገረው ‹‹የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው፤ ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና፡፡›› (ምሳ.፰፥፴፬)

ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲሆንልን ለፈቃዱ ለመገዛት እንትጋ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ሲያስተምር ‹‹እግዚአብሔርን ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን›› በማለት ይናገራል፡፡ (ሮሜ ፰፥፳፰)

፫. ጠበል መጠመቅ፣ ቅብዐ ቅዱስ መቀባትና በአባቶች ጸሎት መታገዝ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማንኛውም ሰው በሥነ ልቡና ችግሮች እንዳይሠቃይ፣ ሳንወድ በሐሳባችን በሚመላለሱ ክፉ ኅሊናት (አሉታዊ አስተሳሰቦች) እስረኛም እንዳንሆን የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት መሠረት ያደረጉ በጎና መልካም ክርስቲያናዊ ሥርዓቶችን አስቀምጣልናለች፡፡ ከነዚህም አንዱ ንዕማን ከለምፅ የተፈወሰበት፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደረቅ ግንባር ዐይን ሥሎ ዐይኑን ያበራለት ሰው በምሕረት በተጎበኘበት በቅዱስ ውሃ (ጠበል) መጠመቅ አንዱ መንገድ ነው፡፡ (፪ነገ.፭፥፩-፲፭፣ዮሐ.፱፥፩-፱)

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን በተባረከው ጠበል ስንጠመቅ የታወከ አእምሮአችን ይረጋጋል፣ ክፉውን የሚያመላልስ አእምሮአችን አደብ ይገዛል፡፡ ከዚህም ጋር ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ቀሳውስት ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም ዘይት (ቅብዐ ቅዱስ) ቀብተው ይጸልዩለት፡፡ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል›› በማለት እንዳስተማረው በተቀደሰው ውኃ ሥልጣነ ክህነቱ ባላቸው አባቶች እየተጠመቁ ቅዱስ ቅብዐት መቀባቱም ከአእምሮ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ አሉታዊ አስተሳሰቦች ፈውስ ይሆናል፡፡ (ያዕ.፭፥፲፫-፲፭)

. ቃለ እግዚአብሔርን መማር መንፈሳዊ መዝሙራትን ማዳመጥ

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ‹‹በውኑ ቃሌ እንደ እሳት ድንጋይንም እንደሚያደቅ መዶሻ አይደለምን?›› በማለት እንደተናገረው ሐዋርያትም ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና የሚሠራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው÷ ነፍስንና መንፈስን ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል÷ የልብን ስሜትና አሳብ ይመረምራል›› ብለው እንዳስተማሩን ወደ እግዚአብሔር ቤት መጥተን ቃሉን በእምነት የምንሰማ ከሆነ ቅዱስ ቃሉ በውስጣችን የሚመላለሰውን ክፉና አሉታዊ አስተሳሰብ እንደ ሰናዖር ግምብ ይደረምስልና እንደ ኢያሪኮ ቅጥርም ያፈርስልናል፡፡ (ኤር.፳፫፥፳፱፣ዕብ.፬፥፲፪)

ሐዋርያው ‹‹በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና÷ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ሁሉ እናፈርሳለን›› ብሎ መናገሩም ለዚሁ ነው፡፡ ስለሆነም የበጎ ኅሊና ባለቤቶች ለመሆን ቃለ እግዚአብሔርን መስማት አንዱ መልካም መንገድ ነው፡፡ ከቃለ እግዚአብሔር በተጨማሪም መንፈስን የሚያረጋጉና ውስጥ ዘልቀው የሚገቡ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የተዘጋጁ መንፈሳዊ መዝሙራትንም ማዳመጥ ከክፉ ኅሊና (ከአሉታዊ አስተሳሰብ) ያወጣሉ፡፡ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳዖል በክፉ አሳብ እየተንገላታ ውስጡ ሲጨነቅ ነቢዩ ዳዊት እየመጣ በገና እየደረደረ በሚዘምርለት ጊዜ ከዚያ ክፉ አሳብ ይገላገል እንደነበር ተጽፎልናል፡፡ ስለሆነም እርባና ከሌለው የሰነፎች ዜማ እየራቅን ቃለ እግዚአብሔርን መሠረት ያደረጉ መዝሙራትን ማዳመጥ የዘወትር ሥራችን ይሁን፡፡ (፪ቆሮ.፲፥፪-፭፣፩ሳሙ.፲፮፥፲፬)

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ለሁላችን በጎ ኅሊናን ያድለን!!!