በዓለ ጥምቀት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ጥር ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ! ልጆች! የጌታችንን የልደት በዓልን እንዴት አሳለፋችሁ? በሰላም እንዳሳለፋችሁ ተስፋችን ነው፤ ትምህርትስ እንዴት ነው? የግማሽ መንፈቀ ዓመት ፈተናም እየደረሰ ነውና በርትታችሁ አጥኑ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ዛሬ ደግሞ ስለ ጥምቀት በዓል እንማማራለን፡፡ ጥምቀት ማለት ‹‹አጥመቀ- አጠመቀ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ‹‹መነከር፣ መድፈቅ፣ በተባረከው ውኃ ጸበል ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ›› ማለት ነው፤ እንግዲህ በዛሬ ትምህርታችን ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት እንመለከታለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ እያጠመቀ ሳለ ጌታችን ኢየሱስም በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ወደ እርሱ ሄደ፤ በዚህን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እኔ በአንተ ልጠመቅ እሻለሁ፤ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን›› አለ፤ ጌታችንም ‹‹ጽድቅን ሁሉ እንፈጽም ዘንድ ይገባል›› በማለት ለእኛ አርአያ ለመሆን ሲል በትሕትና ወደ አገልጋዩ ዮሐንስ ዘንድ በመሄድ ተጠመቀ፤ ከዚያም ተጠምቆ ሲወጣ የባሕርይ አባቱ አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› በማለት መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ (ማቴ.፫፥፲፬-፲፯)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን በምን ምክንያት የተጠመቀ መሰላችሁ? እኛ ሰዎች በተወለድን ወንዶች በዐርባ እና ሴቶች በሰማንያ ቀናችን ስንጠመቅ የእግዚአብሔርን ልጅነት ለማግኘት ነው፤ ጌታችን ግን መጠመቁ ለእኛ ሲል ነው፤ ለምን መሰላችሁ? አንደኛው ምክንያት ጠላታችን ዲያቢሎስ አዳምንና ሔዋንን በባርነት የሚገዛበት የዕዳ ደብዳቤ በዮርዳኖስ ወንዝ ነበረ፡፡

ልጆች ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከባለጋራችን የተነሳ በትዕዛዝ የተጻፈውን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን..›› በማለት እንዳስተማረን ጌታችን ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ገብቶ ሲጠመቅ ያንን በእብነ በረድ ተጽፎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን ደመሰሰልን፤ (ቈላ. ምዕራፍ ፪፥፲፬) ሌላው የጌታችን መጠመቅ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም እንዲሁም ደግሞ አንድነቱና ሦስትነቱ በኋላ ይገለጽ ዘንድ ነው፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ታላቅ በዓል ሁል ጊዜ ጥር ዐሥራ አንድ ቀን በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ታከብረዋለች፤ በዚህ ዕለት ጠላታችን ዲያብሎስ ያፈረበት የደስታ የነጻነታችን በዓል ነው፤ የከተራ ዕለት (በዋዜማው) ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በመነሣት አባቶች ሊቃውንት እየዘመሩ ምእመናን እያጨበጨቡና እልል እያሉ ታቦታቱን አጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሄዳሉ፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን በኅብረት ሆነው ብርሃነ ጥምቀቱን የሚያወሳ የጌታችንን ውለታ የሚያዘክሩ ዝማሬያትን በመዘመር በደስታ ታቦታቱን አጅበው ይሄዳሉ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው (ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው) ወደ ጥምቀተ ባሕሩ የመሄዳቸው ምሳሌነቱ ምን መሰላችሁ? ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ በትሕትና ቅዱስ ዮሐንስ ወዳለበት ዘንድ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ መሄዱን ለማዘከር ነው፡፡ በጥምቀተ ባሕሩም ሊቃውት ፈጣሪን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴም ይፈጸማል፤ እንዲህ በምስጋና ሌሊቱ ካለፈ በኋላ በዓሉን አስመልክቶ ዝማሬው ቀርቦና ትምህርት ተሰጥቶ እንደገና ታቦታቱ በዝማሬ በእልልታ ታጅበው ወደ መንበረ ክብራቸው (ወደ የአብያተ ክርስቲያናቱ) ይመለሳሉ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ከጥምቀት በዓል ማግስት በዐሥራ ሁለት የሚከበር የቃና ዘገሊላ በዓል አለ፤ ይህ በዓል ጌታችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ በተባለ ቦታ ድንቅ ተአምር ያደረገበት ዕለት መታሰቢያ ነው፤ ልጆች  ምን ሆነ መሰላችሁ? በገሊላ አውራጃ ሠርግ ተደረገና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ሠርግ ቤት ተጠሩ፡፡ ከዚያም በጣም ብዙ ሰው ስለነበር ደጋሾቹ ለእንግዶች የሚያቀርቡት ወይን ጠጅ አለቀባቸው፤

አስተውሉ ልጆች! እንግዳ ቤታችሁ ተጠርቶ አለቀብን ማለት በጣም ያስጨንቃል፤ የተጠራው ሰው ሳይደርሰው ወይኑ አለቀ፤ በዚህን ጊዜ ሰዎቹ ተጨነቁ፤ የሚያደርጉትም ጠፋቸው፤ እመቤታችን ማርያምም የሰዎችን መጨነቅ ተመለከተች፤ የርኅሩኅ ጌታ እናት ርኅሩይት ናትና ሳይነግሯት ወይኑ እንዳለቀባቸው አውቃ አዘነችላቸው፤ ጭንቀታቸውን ለማራቅ ያለቀባቸውን ጉድለታቸውን ልትሞላ ገመናቸውን ልትሸፍን ሁሉን ማድረግ ወደሚቻለው ልጇ ጌታችን አምላካችን ዘንድ ሄዳ ‹‹.ልጄ ሆይ የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል..›› ብላ ነገረችው፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሰዎቹም ሄዳ ልጄ የሚላችሁን አድርጉ አለቻቸው፤  ከዚያም ጌታችን ባዶ እንስራ (ጋን) እንዲያመጡ አዘዛቸው፤ እነርሱም አመጡ ውኃ ሙሉበት አላቸው፤ እነርሱም እመቤታችን እንደነገረቻቸው ጌታችን የነገራቸውን (ያዘዛቸውን) በባዶው እንስራ (ጋን ) ውኃ ሞሉበት፤ ከዚያም እንደ አምላክነቱ ያንን ውኃ የወይን ጠጅ እንዲሆን አደረገ፤ ባለሠርገኞቹ በጣም ተደሰቱ፤ የተጨነቁበት ነገር መፍትሔ ስላገኘ ያንን የወይን ጠጅ እየቀዱ ለመጡት እንግዶች ሰጡ፤ ጌታችን ከውኃነት ወደ ወይን ጠጅነት የቀየረው እነርሱ መጀመሪያ ከጠመቁት በጣም ይለይ ይጣፍጥ ነበር፡፡

እናም ልጆች! ጌታችን በሰርግ ቤት ተገኝቶ ይህን ድንቅ ተአምር ያደረገበትን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ በየዓመቱ ጥር ዐሥራ ሁለት ቀን ታከብረዋለች፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሠርገኞቹ በሠርግ ቤት ጌታችንንና እመቤታችንን እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያትን በመጥራታቸው ችግራቸው ተፈታ፤ ጉድለታቸው ሞላ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የሆነ ሁሉ ይሞላለታል፣ ያሰበው ይሳካለታል፤ እኛም በሕይወታችን ዘወትር እመቤታችንን በውዳሴ ማርያም ልንማጸናት፣ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል፤ ይህን የምናደርገ ከሆነ የምንማረው ትምህርት ይገለጥልናል፤ ማስተዋልና ጥበቡ ይሰጠናል፤ ዕቅዳችን ይሰምራል፣ ምግባራችን ለሁሉ ሰው ጣፋጭ (የተመቸ) ይሆንልናል፤ ስለዚህ ዘወትር በጸሎት፣ በዝማሬ መኖር ይገባናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ በጣም በጥቂቱ ስለ በዓለ ጥምቀትና ስለ ቃና ዘገሊላ በዓል ነገርናችሁ፤ ምሥጢሩ እና ትምህርቱ በጣም ሰፊ ቢሆንም እኛ ግን በሚረዳችሁና አጠር ባለ መልኩ ይህን አልናችሁ፤ ቸር ይግጠመን፡፡ መልካም በዓል!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!