በዓለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት

መምህር ሰሎሞን ጥጋቡ

ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

አምላካችን እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ “በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀን ሳትወጣ ቀድሸሃለሁ” በማለት እንደተናገረ የገናናው ጻድቅ የአባታችን ተክለ ሃይማኖት ዜና ሕይወቱን እንዘክራለን፡፡ (ኤር.፩፥፭)

ልደት 

ደጋጎቹ ካህኑ ጸጋ ዘአብና እግዚእኃረያ የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ፡፡ እነርሱም እንደሌሎች ቅዱሳን እናት እና አባቶቻቸው ልጅ  አተው ኖረዋል፡፡ እንደነ አብረሃም እና ሣራ፣ እንደ እነ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥ  ማለት ነው። እግዚኃርያም ሁል ጊዜም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ታመለክት ነበር። ከዕለታት አንዲት ቀን መላኩ ተግልጾ ልጅ እንደሚወልዱ ነገራቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመጋቢት ፳፬ ቀን ፲፻፪፻፮ ዓ.ም ተፀንሰው በሸዋ ክፍለ ሀገር በጽላለሽ ወይም በዞረሬ አካባቢ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው ከእግዚኃርያ በታኅሣሥ ፳፬ ቀን በታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፻፪፻፯ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ሲወለዱም ሥላሴን “ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ” ብለው አመስገነዋል። ጻድቁ በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጿል፤ ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

አባታችን ተክለ ሃይማኖት ክርስትና ወይም የሥላሴን ልጅነት ሲቀበሉ አባቱ ጸጋ ዘአብ  ሲቀድስ ያመሰግን ነበር፡፡ እናቱም ደግሞ “አንተ ልጅ አሁን ጡጥ ጥባ እንጂ” እያለች ትሞግተው ነበር። የካህን ልጅ ካህን እንዲሉ ገና ሲወለድ ጀምሮ “ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ”  በማለት ምስጋና ስለጀመረ አባት እና እናቱ እጅግ ተደሰቱ፡፡

 ዕድገት

ጻድቃኖች የቅዱሱ ወላጆች እግዚአብሔር ለሰጣቸው የተመረጠ ልጅ የመጀመሪያ ያወጡላቸው “ፍሥሃ ጽዮን” የሚል ስም ነው:: በዚህም ስያሜ አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይም ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያትና ሐዲሳትን) ተምረዋል:: ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::

መጠራት

ከዕለታት በአንዱ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በቅዱስ ሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

በመቀጠልም የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ፤ “ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከአሁን በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ” ብሎትም በግርማ ዐረገ:: ጻድቁ ተክለ ሃይማኖትም ጊዜ አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

አገልግሎት

ጻድቁ አባት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: አባታችን በኢትዮጵያ  በረሃዎች ወንዞች ሸንተረሮች እና  አውራጃዎች  እየተዘዋወሩ  በልዩ ልዩ አምልኮ የነበረውን ሕዝብ  የክርስቶስን ወንጌለ መንግሥት አስተምረው እና አጥምቀው የክርስቶስን መንግሥት እንዲወርሱ ያደረጉ ታልቅ ጻድቅ ናቸው። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ፲ ሽህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ ሁለት መልክ ነበራት::

አንደኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽእኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዶ እና በባዕድ አምልኮ ተጠምዶም ነበር::

ሁለተኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሀገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን እንዲሁመ መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::

አባታችን ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም ላይ ወንጌልን መሰረት አድርገው የሐዋርያትን ሥራ ፈለግ በመከተል ብዙ ተጋድላዋል። ለሀገራችን ለኢትዮጵያ በዚህ ዓለም ብዙ ደክመዋል።፡ ለዚህም ነው በአንድ ወቅት አባታችን “ወለእመ ጠፋአ ማሕቶት አልቦ ዘየሐቱ ሎቱ ዘእንበለ ዘይከድኖ ጽልመት፤ መብራት ቢጠፋፋ የሚያበራለት የለም፤ ጨለማ ከሚወርሰው በቀር።” ለአቃቤ ሥርያኒ መኑ ይፌውስ ለአመኢያመረ ፈውሰ ለእረሱ ከማሁ ኮነት ነፍስዬ በላዕሌየ ቀሰምኩ ባዕዳነ ወለሳህዩኩ ለልየ ሰረይኩ፤ አሕዛበ ወደወይኩ ለልየ አብራይኩ ለዓለም ወጸለምኩ ለእርስየ፤ ባለ መድኃኒትንስ ማንን ይፈውሰዋል፤ ከእራሱ የሚድንበት ካላወቀ ነፍሴ በእኔ ላይ እንዲሁ ሆነች፤ ሌሎችን ግን አጣፈጥኩ፤ ለእራሴ ግን አልጫ ሆንኩ፤ ሕሙማንን ፈወስኩ፤ ለእራሴ ግን ድውይ ሆንኩኝ፤ ለዓለም አበራሁ፤ ለእራሴ ግን ጨለምኩ” በማለት እንደተናገሩ ገድላቸው ይጠቅሳል። ይህ የሚያመለክተው አባታችን ተክለ ሃይማኖት ረኃቡን፣ ጥሙን፣ መካራ ሥቃዩን ታግሠው በጾም እና በጸሎት እንዲሁም በስግደት ተጋድሎ በማድረግ በየተራረው እየዞሩ በዚህች በመራረው ዓለም ጣፋጭ ወንጌልን በማስማር ኢትዮጵያን ያጣፈጡ እንደሆኑ ነው፡፡ ሥራቸውም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም እንዳበራ የተመሠከላቸው ነው፡፡

ገዳማዊ ሕይወት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል:፡ እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ፲፪ ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት፣ በአጠቃላይ ለ፳፮ ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ፳፪ ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል::

ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከፅንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ፣ በቤተ መቅደስ ብሥራቱን፣ በቤተ ልሔም ልደቱን ፣በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን ፣በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን ፣በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው:: በዚያም የብርሃን ዐይን ተቀብለው ስድስት ክንፍ አብቅለው፣ የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣ ከ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው ፣ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው -“ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ” ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

ተአምራት

የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው:: ሙት አንስተዋል፤ ድውያንን ፈውሰዋል፤ አጋንንትን አሳደዋል፤ እሳትን ጨብጠዋል፤ በክንፍ በረዋል፤
ደመናን ዙፋን አድርገዋል፤ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መስርተዋል፤ በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል፤ በዘመናቸው ሰይጣን ታስሯልና::

ዕረፍት

ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በ፺፱ ዓመት: ከስምንት ወር ከ አንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፻፫፻፮ ዓ.ም ዐርፈዋል:: ጌታችን፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል፤ ፲ ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

የጻደቁ አባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት