‹‹በወንድማማችነትም ፍቅርን ጨምሩ›› (፪ ጴጥ. ፩፥፯)

የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ፍቅር ልባዊ መዋደድ ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ፍቅር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ፍቅር ያስታግሣል፤ ፍቅር ያስተሳዝናል፤ ፍቅር አያቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር ልቡናን አያስታብይም፡፡ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም፤ ክፉ ነገርንም አያሳስብም፡፡ ጽድቅን በመሥራት ደስ ያሰኛል እንጂ፥ ግፍን በመሥራት ደስ አያሰኝም፡፡ በሁሉ ያቻችላል፤ በሁሉ ያስተማምናል፤ በሁሉም ተስፋ ያስደርጋል፥ በሁሉም ያስታግሣል፤ ፍቅር ለዘወትር አይጥልም፡፡›› (፩ ቆሮ. ፲፫፥፬-፰)

ሰዎች በማኅበራዊ ግንኑነታችን በፍቅር እንድንኖር አንዱ ለሌላው መልካም ነገርን ያደርግ ዘንድ ይገባል፡፡ ዕለት ከዕለትም በፍቅር ለመኖር በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ግንኑኝነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ ይህም በኀዘንም ሆነ በደስታ ጊዜ የሰዎችን ስሜት መጋራት ማለት ነው፡፡ ካዘኑት ጋር ስናዝንም ሆነ ከተሰደሰቱት ጋር ስንደሰት ፍቅር በመካከላችን ይኖራል፤ ሰዎችን እንደ ራስ በመውደድ፣ በመከራቸውና በችግራቸው ጊዜ በማጽናናት እንዲሁም በመርዳትም ፍቅር ይገለጻል፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰዎች ድኅነት ሲል ከሰማያት ወርዶ፣ በመከራና በሥቃይ ተንገላቶ በመስቀሉም ላይ ተሠውቶ ፍቅሩን ገልጾልናል፡፡ እኛም ይህን አርአያ እያደረግን መስቀሉን በመሸከም በክርስቶስ ክርስቲያኖች እንባል ዘንድ ለፈጣሪያችን በፍቅር እንገዛለን፡፡

እግዚአብሔር አባታችን እንደሆነ ሁሉ የእርሱ ልጆች በመሆናችን ወንድማማቾች ነን፡፡ ከምድራዊ አባትና እናቶቻችን መወለዳችን ብቻ ወንድማማች አያስብለንም፤ ወንድማማችነት ከዚያ ያለፈ ትርጒም አለው፡፡ ከቤተሰባዊነት ባሻገር በዝምድናም ሆነ በቀረቤታ ወንድማማችነት ይገኛልና፤ የሰው ዘር በሙሉ በወንድማማችነት ፍቅር ሊኖር እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔርን በማምለክ ወንድማማችነትን፥ በወንድማማችነትም ፍቅርን ጨምሩ›› በማለት ያስተምረናል፤ (፪ ጴጥ. ፩፥፯)

ሰዎች የአንድ ጎሳ ወይም ብሔር አባላት ቢሆኑ እንኳን የወንድማችነት ፍቅር በመካከላቸው የሚኖረው እግዚአብሔር አምላካቸውን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው እና በፍጹም ኃይላቸው ሲወዱ ነው፤ ከዚያም ለቤተሰቦቻቸው ያላቸውን ፍቅር ያህል ሌሎች ሰዎችን መውደድ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ›› እንዲል፤ (ዘሌ. ፲፱፥ ፲፰)

ያለ ሰው ፍቅር የእግዚአብሔር ፍቅር የማይቻል ነው፤ ‹‹ወንድሞቻችን ሆይ፥ እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን፥ እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል›› እንደተባለውም የወንድማማችነት ፍቅር ሰዎችን እንደ ራስ በመውደድ በአንድነት መኖር ነው፤ ራስ ወዳድነትንም ሆነ ሌሎች እኩይ ጠባያትን ከውስጣችንን አፅድተን ለሰዎች በጎ በማድረግ መኖር አለብን፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም ያማረ ነው›› በማለት ተናግሯል፤ ይህም የነቢዩ ቃል የሚያመለክተው የወንድማማችነት ፍቅር ከልብ በመነጨ መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ መተዛዘን እና የልብ አንድነት መሆኑን ነው፡፡ (፩ ዮሐ. ፬፥፲፩፣ መዝ. ፻፴፪፥፩)

በወንድማማችነት ፍቅር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የተራቆቱትን በማልበስ፣ የታመሙትን በማስታመም፣ የታሠሩትን በመጠየቅ፣ ያዘኑትን በማጽናናት እንዲሁም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉትን በመርዳት ይገለጻል፡፡  ‹‹በእኔ ካመኑ ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁትን ሁሉ ለእኔ አደረጋችሁት›› እንደተባለው ለአምላካችን ያለንን ፍቅርም ለሌሎች በጎ በማድረግ በመግለጽም በፍቅር መኖር ይቻለናል፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፵)

የእግዚአብሔር ቃል በማንኛውም ቦታ የወንድማማችነት ፍቅር እንድናሳይ ይመክረናል፡፡ ፈጣሪያችንን የምንወድ ከሆነ የእርሱ የሆኑትን እንወዳለን፤ አምላካችንም ሰውን ሁሉ ለመልካም እንደፈጠረ ሁሉ ሰዎች በሙሉ ተዋደን ልንኖር ይገባል፡፡ አንድ አምላክ እግዚአብሔር እንዳለን በማወቅና ለእርሱ በመገዛት በምድር የመኖራችንም ምክንያትም ለድኅነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እርስ በእርሳችንም ተዋደን በሃይማኖትም ጸንተን ስንኖር እያንዳንዳችን ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ እንቀርባለን፤ ይህ ወንድማማችነት እውነተኛ ፍቅር እና አንድነት ነው፤ የሁላችንም እረኛ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመራንም ሁላችንም በአንድነት ወደ ሰማያዊት እየሩሳሌም እንጓዛለን፡፡

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በብዛት ራስ ወዳድ ከመሆናችን የተነሣ ለራሳችን እንጂ ለሌላው የማናስብ ሆነናል፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ክርስቲያናዊ ሕይወትን መኖር ስንጀምር ግን የራስ ወዳድነት መንፈሳችን እየጠፋ ይሄዳል።

የትምህርት፣ የአቋም፣ የባሕርይ፣ የችሎታ፣ የብሔረሰብ ወይም የዘር ልዩነቶች የወንድማማችነት ፍቅራችንን እንዳያደናቅፉት መጠንቀቅ አለብን። በመካከላችን የአስተሳሰብ ልዩነቶች ከመኖራቸው የተነሣ አለመግባባት ቢኖር እንኳን እውነቱን በመረዳት መግባባት መቻል ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ይህ መሆን ሲገባው እርስ በርሳችን የምንጣላ እና የምንቀያየም ከሆነ ግን በመካከላችን ያለው የወንድማማችነት ፍቅር ትልቅ እንቅፋት ላይ ይወድቃል፡፡ ተሳስተንም ከሆነ ስሕተታችንን አምነን በመቀበል ካስፈለገም ይቅርታ በመጠየቅ መስማማት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የሃይማኖት አባቶችንም ማማከር ይቻላል፤ የእነርሱ ምክርና ተግሣጽ እኛን ከጥፋት ይመልሰናል፤ ከጥልም መልሶ በፍቅር እንድንኖር ያደርገናል፡፡

ስዚህ ሁልጊዜም በወንድማማችነት ፍቅር መኖር አለብን። ሰዎች በሕይወተ ሥጋ እስካለን ድረስ ወንድማማቾች ተብለን እንድንኖር ልባችን ከክፋት፣ ከጥላቻ፣ ከቂም፣ ከበቀል የፀዳ እንዲሆንና እውነተኛ ፍቅር እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ሰዎች ለሌሎቸ ፍቅር አለን በማለት ሊናገሩ ይችላል፤ ነገር ግን መምሰል እና መሆን ይለያያልና ሆነን መገኘት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ለሌሎች እንዲኖረን እውነተኛ ሰዎች መሆን አለብን፡፡

ከዚህም ባሻገር ለሰዎችም ልባዊ ወይንም እውነተኛ ፍቅር ሲኖረን ለቤተ ክርስቲያን እና በውስጧ ላሉት አገልጋዮች እንደዚሁም ለምእመናን በሙሉ  ፍቅር ይኖረናል፤ ብዙዎች ይህን ፍቅር ለማዳበር መሞከር እንዳለብን እና በእርግጥም አስፈላጊ ነገር መሆኑን ይስማማሉ፤ ነገር ግን ይተገብሩታል ማለት አይደለም።

ወንድሞቻችንን እንደራሳችን መውደዳችን ከሞት ወደ ሕይወት እንደሚያሻግረን ማወቅ አለብን፡፡ ምክንያቱም ፍቅር እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንንና የመዳናችንም ማረጋገጫ ነው፡፡ ‹‹እርስ በርስ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ›› (ዮሐ. ፲፫፥፴፭)

ለፈጣሪያችን ያለን ፍጹም ፍቅር ጠንካራ ከሆነም ለወንድሞቻችንም የሚኖረን ፍቅርም ጠንካራ ይሆናል፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥም ያለው ማንኛውም በጎ ምግባር ከእምነት እና ከፍቅር የመነጨ ይሆናል። ፍቅር መሠረቱም  ፍፃሜው  እምነት ነውና፡፡  ፍቅር ርኅራኄ፣ ትሕትናን፣ ራስን መግዛትንና ትዕግሥትን ያስተምራልና፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር በሁሉም ልጆቹ ውስጥ ፍቅር እንዲኖር ፍቃዱ ስለሆነ ልባችንን ለፍቅር የተገባ እናድርገው፤ ለፈጣሪያችን በፍቅር እንገዛ፤ ወንድሞቻንን ከልብ እንውደድ፡፡