“በእንተ ጦማረ ሐሰት”

ግንቦት 13፣ 2003 ዓ.ም

በሐሰት የተሠራጨውን ሰነድ በተመለከተ ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ

እምነትና ሥርዓቷ ጸንቶ የቆየውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕልውናዋን ለማሳጣት እና ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ለማደናቀፍ ቀን ከሌሊት የሚተጉ አካላት የጥፋት ሤራቸውን ከመጎንጎን እና የተቻላቸውን ሁሉ ከመፈጸም ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡ ቅድስት ቤተክርቲያን ሕግና ደንብ አውጥታ በመዋቅሯ አቅፋ እንዲያገለግል አደራና ሓላፊነት የሰጠችው ማኅበረ ቅዱሳንም የጥቃታቸው አንዱ አላማ ነው፡፡ የማኅበሩን ቀና አገልግሎት ለማስቆም ብዙ ጥረዋል፡፡
 
በእግዚአብሔር ፈቃድና ቸርነት የተመሠረተ እንደመሆኑ የቅድስት ቤተክርቲያንን መመሪያ ጠብቆ በአባቶች ምክርና ጸሎት እየታገዘ አገልገሎቱን ከመፈጸም ወደኋላ አይልም፡፡ እነዚህ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚፈታተኑ አካላት የማኅበረ ቅዱሳንን ስም በማጥፋት እንደደከሙት ሁሉ፤ ሰሞኑን የማኅበሩን ማኅተም በተጭበረበረ ሁኔታ / ፎርጅድ/ በመጠቀም፣ "የማኅበሩ የሃያ አምስት ዓመት እቅድ" ነው በማለት የሐሰት ሰነድ አዘጋጅተው በኢንተርኔት ለማሠራጨት እና ለተወሰኑ ብፁዓን አባቶች እንዲደርስ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱ ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ ባሳለፋቸው አሥራ ዘጠኝ የአገልግሎት ዓመታት እቅድና አፈጻጸሙ በየደረጃው ለሚገኙ የቤተክርስቲያን አካላት እና አባቶች እንዲሁም ለማኅበሩ ማእከላትና አባላት በየወቅቱ በሪፖርት የሚገለጽ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን በዚሁ ሁኔታ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ ይህ የማኅበሩ አሠራር በተገቢው ሁኔታ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ሰሞኑን የተሠራጨውን የሐሰት ጽሑፍ በተመለከተ የማኅበሩን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ሰሞኑን “ድንግል ማርያም” በተባለ የፌስ ቡክ አድራሻ(face book Account) “የማኅበረ ቅዱሳን የረዥም ጊዜ እቅድ” በሚል የተበተነ የሐሰት ጽሑፍ እንዲወጣ (Post) መደረጉ ታውቋል፡፡ ይህ ጽሑፍ በመጨረሻው ላይ የማኅበረ ቅዱሳን የሃያ አምስት ዓመት እቅድ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ለመሆኑ ይህ “ጦማረ ሐሰት” ምንጩ ከየት ነው? ጽሑፉ እንዳመለከተው በውኑ የማኅበረ ቅዱሳን እቅድ ነውን? ይዘቱና ዓላማውስ ምንድን ነው? ማኅበረ ቅዱሳንስ በዚህ ጽሑፍ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?

ምንጩ ከየት ነው?
ጽሑፉ በራሱ ሥልጣን እየተጣጣረም ቢሆን ለመናገር የሚሞክረው "የማኅበረ ቅዱሳን ነኝ" እያለ ነው፡፡ ነገር ግን በመናገር እና በመሆን መካከል ያለውን ርቀት እንዳይፈራገጥ ባስገነዘው ጣእረ ሞት እንደያዘው የሚይዘውን የሚጨብጠውን ያጣ ወረቀት ነው፡፡ ለዚህም ጽሑፉ ሳያውቀው ምንጩን ሲናገር እናገኘዋለን፡፡ ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ምንጩ ማኅበረ ቅዱሳን ሊሆን ይችላልን?

የሚለውን መመልከቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እቅድ እያቀደ የእግዚአብሔርን አጋዥነት እየለመነ አገልግሎትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ እቅድ ማቀድ በማኅበሩ ዘንድ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በጥቂቱ የሃያ ዓመት ልምድም ያለው ማኅበር ነው፡፡ አባላቱም ከመንፈሳዊው አገልግሎት ባሻገር በየተሠማሩበት የሙያ ዘርፍ እቅድ እያቀዱ ራሳቸውን በዘመናዊው አሠራር ያበለጸጉ ከመሆናቸው አንጻር መሠረታዊ የእቅድ አዘገጃጀት እውቀት ያላቸው መሆኑን ልንጠራጠር አንችልም፡፡ የተበተነው ጽሑፍ ያውም ሁለት ከወገብ በታች /ግማሽ ገጽ/ የሆኑ ወረቀቶች ላይ ማኅበሩ የሃያ አምስት ዓመት እቅድ ተብሎ ተዘርዝሯል፡፡ እንዲህ አይነቱ የሃያ አምስት ዓመት እቅድ ማቀድ   በአዘጋጆቹ ዘንድ የተለመደ ይሆናል እንጂ በማኅበረ ቅዱሳን ዘንድ የለም፡፡ የማኅበሩ የአራት ዓመት ስልታዊ እቅድ እንኳን የተዘጋጀው በሃምሳ አምስት ገፆች ነው፡፡

ስልታዊ እቅድ እንደመሆኑ መጠን በዘመናዊው አሠራር የራሱ ቅርጽ (format) አለው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መግቢያ፣ የማኅበሩን ማንነት፣ የማኅበሩ ዓላማ፣ ርእይ፣ ተልእኮ፣ እሴት፣ የባለድርሻ አካላት ትንተና፣ ውጫዊ አካባቢ ትንታኔ፣ እንዲሁም አስፈላጊነቱ ሌሎች ትንታኔዎች ምቹ እና ፈታኝ ሁኔታዎች፣ የምቹ እና ፈታኝ ሁኔታዎች ምዘና፣ ወሳኝ ጉዳዮች፣ ስልታዊ እቅድ ዓላማ፣ ግብና ስልት፣ ዝርዝር የአፈጻጸም መርሐ ግብር እንዲሁም የክትትልና የግምገማ ሥርአት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡

በዚህ ቅርጽ መሠረት የማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ /ስትራቴጂክ/ እቅዱን አዘጋጅቶ  ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት በማቅረብ በእቅዱ መሠረት አገልግሎቱን በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አሠራሩ ያልተመቻቸው አካላት የጐንዮሽ እቅድ በማቀድ የራሳቸውን የፈጠራ ሥራ አቅርበዋል፡፡ማኅበረ ቅዱሳንን ለመወንጀል ታስቦ የሐሰት ሰነድ (forged document) ተዘጋጅቶ የተበተነበትም ምክንያት ያንን እቅድ አባቶች እንደማያውቁት በማስመሰል ነው፡፡

የፖለቲካ አጠቃቀም
ማኅበሩ በመዋቅሩ ሥር ያሉትን አካላት በራሱ መጥራት የተሳነው አስመስለው ቀርጸውታል፡፡ ለማሳያ የሚሆነውም በዝርዝር እቅዱ ውስጥ በአንድ ላይ "በየንዑሳን ቅርንጫፍ በኩል" የሚል ሐረግ ይገኛል፡፡ ሲጀምር ማኅበሩ ቅርንጫፍ የሚባል ምንም ዓይነት መዋቅር የለውም፡፡  
 
ከዋናው ማእከል ቀጥሎ ያሉት ማእከላት ይባላሉ እንጂ ንዑሳን አይባሉም፡፡ ይህም አጠቃቀሙ ሌላ አካል መሆኑን ያሳያል፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ የተበተነው ወረቀት አንድ ተማሪ ክፍል ውስጥ ገብቶ ሲማር ከሚይዘው ማስታወሻ እንኳ ያነሰ፤ እቅድ መባል ካለበት እንኳ የጨነገፈ እቅድ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ሊያወጣው አይችልም፡፡ በዚህ መስፈርት እንኳን ቢታይ እቅዱ በምንም መለኪያ የማኅበረ ቅዱሳን አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ራሱን ሲጠራ ”ማህበረ ቅዱሳን” ብሎ አያውቅም። "እቅድ" የሚለውን ቃል አቅድ የሚለውን ተክቶ ለጥቅም እንዲውል አድርጐም አያውቅም፡፡ እነዚህን የተጠቀመው ጽሑፍ ራሱን እርቃኑን አቁሞ የማኅበረ ቅዱሳን አለመ ሆኑን የገለጠበት ዘርፍ ነው፡፡ ወረቀቱ ስለ እቅድ የሚናገር ከሆነ የተግባራዊነት ዘመኑ ከመቼ እስከ መቼ እንደሆነ እንኳ አለመገለጹ ድንገቴ እንደ ወራጅ ውኃ የፈሰሰ የጥቂቶች አሳብ እንጂ እቅድ አለመሆኑን ያሳብቅበታል፡፡ የስሕተት ሙሻዙር የጠመዘዛቸው አዘጋጆች እንደመሰላቸው እነርሱ ያስቀመጧቸውን በወንጀል ደረጃ የሚፈረጁ አደገኛ አሳቦች በማኅተም አትሞ በቲተር እና በፊርማ አስደግፎ ራሱን ለአደጋ አጋልጦ የሚያስቀምጥ ተቋም በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ይገኛል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው፡፡

በተሠራጨው እቅድ ላይ የተቀመጡት አሳቦች አሉታዊ እና አፍራሽ አስተሳሰቦች እንደመሆናቸው መጠን ማኅበሩ የቱንም ያክል ክፉ ነው ተብሎ ቢታሰብ እንኳ እንዲህ ያለ እቅድ በዚህ መልክ አዘጋጅቶ እና አንድ ቦታ አጠራቅሞ ይገኛል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ያንን ያክል ክፋት ማርገዝ የቻለ እኩይ ሕሊና ቢኖር እንኳ አካሔዱን እና አቀማመጡን አይጠበብበትም ነበር የሚለው ለአንባቢ የሚተው ውሳኔ ይሆናል፡፡ እነዚህን አካሔዶች ጠቅልለን ስንመለከታቸው ምንጩ ለጊዜው የማኅበረ ቅዱሳንን በመጨረሻም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጥፋት ሌት ተቀን ከሚለማመኑ አካላት የተቀዳ ለመሆኑ ከቶውኑ ማን ይመራመራል? መጽሐፍ “በክፋታቸው እየባሱ ይሔዳሉ” እንዳለው የማኅበረ ቅዱሳን መኖር የእግር እሳት ስለሆነባቸው በምን መንገገድ ስሙን ቢያጠፉ ተቀባይነት ሊያገኙ እንደሚችሉ ሁልጊዜ ወጥመድ ያጠምዳሉ፡፡ እስካሁን ድረስ የእግዚአብሔር ቸርነት ከልክሏቸው አልተሳካላቸውም እንጂ የወገባቸው የሐሰት ዝናር ሲያልቅባቸው በማኅበሩ ወንበር ተቀምጠው የሚናገሩ በማስመሰል ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ተልእኮ እንዳለው አድርገው ሊያቅዱለት ፈለጉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ካባ ለብሰው ያቀዱለት እቅድ ግን ከተለመደው ክሳቸው የወጣ አለመሆኑ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ ማኅበሩን ለምን ትቃወማላችሁ ሲባሉ ይሰጡት የነበረውን መልስ እቅድ ነው ብለው አቀረቡት እንጂ ምንም አዲስ ነገር አላመጡም፡፡ ስለሆነም በዚህ በጻፉት እቅዳቸው ምክንያት ማንም ሊደነግጥላቸው አይችልም፡፡ በተቻላቸው መጠን የመጨረሻዋን ጥይት ለመተኮስ ሲጥሩ መልሶ ራሳቸውን ወጋቸው፡፡ በተጉበትም መጠን በመጐዳታቸው አሟሟታቸውን ለማሳመር የሐሰት እና የጥፋት እቅድ ለማኅበሩ አወጡለት፡፡ የሚጠባበቁት ውጤት በእነዚያ ወንጀሎች ምክንያት ያቀዱለት አካል እለቱኑ ታንቆ እለቱኑ ሲሞት ለማየት በጉጉት ኮርቻ ላይ ተቀመጡ፤ የፈለጉት ማኅበሩ እነርሱ ጐን ቆሞ ቤተክርስቲያንን አንዲያጠፋላቸው ነበር፡፡

ግን ምን ያደርጋል? እነርሱም ታወቁ ሕልማቸውም መከነ፡፡ ራሱን በራሱ ሲቃረን አንድ  ተቋም ራሱን ሲገልጽ ‘እኛ” በሚል ባለቤት ሊናገር እንደ ሚችል የተረዳ ነገር ነው፡፡ በጽሑፉ ላይ ግን አባቶችን አባላት በማድረግና ”ስብሰባቸው ላይ” የሚል አባባል ተጠቅመዋል፡፡ ስለራሱ እቅድ የሚናገር ሰው ”በስብሰባችን ላይ” ይላል እንጂ ”ስብሰባቸው ላይ” እንዴት ሊል ይችላል? በተጨማሪም ”በራሱ ጠቅላላ ጉባኤ መምራት” በማለት ማኅበሩ ራሱን ”እርሱ” እያለ እንዲጠራ አድርገው ጽፈዋል፡፡ እንዲሁም ”ካህናቱን ለድርጅቱ ሠራተኞች አድርጐ መቅጠር” በሚለው እቅዳቸው ላይ ”እርሱ” ብሎ ራሱን እንዲጠራ አድርገውታል፡፡

ከእነዚህ አገላለጾች የምንረዳው የሆነ አካል ራሱን አስገድዶ የማኅበሩ አካል አድርጐ በመቁጠር ስለማኅበሩ ሆኖ እንዲጽፍ እንደተጨነቀ ያሳያል፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል አልተቻለውም፡፡ ራሱን ጠፍሮ በማሠር ስለማኅበሩ እንዲናገር አሰቃየው እንጂ ስለሌላ ማኅበር እንደሚናገር ተገልጦበታል፡፡ ጸሐፊው ያለ እርሻው የበቀለ ከሌላ ዘር የመጣ ነውና የራሴ ነው ያለውን ማኅበር ”እነርሱ” ”እርሱ” እና ”እኛ” እያለ ጠራው፡፡ ያልሠለጠነ ውሸታም በመሆኑ እንዲጽፍላቸው የቀጠሩትን ሰዎች አጋለጣቸው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወዴት መሸሸግ ይቻላል? የጨለማው መጋረጃ ተቀደደባቸው፣ ከእነ ተንኮላቸው እጅ ከፈንጅ ተያዙ፡፡ ወዲህና ወዲያ እንዳይሉ በራሳቸው ገመድ ተጠፍንገው ታሠሩ፡፡ እግዚአብሔር ይፍታችሁ ከማለት ውጭ ምን እንላለን?

ማኅበሩ ማኅበሩን ሲቃወም በዕቅዳቸው ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን የሚያሳትማቸውን ኅትመቶች ያለ ኤዲቶሪያል ቦርድ ኅትመት አከናውኖ ማሠራጨት የሚል የተጠላለፈ አሳብ አስቀምጧል፡፡ በመሠረቱ ማኅበረ ቅዱሳን በመዋቅሩ እንዳመለከተው ማንኛውንም ኅትመት ኤዲቶሪያል ቦርዱ ዓይቶት ሲፈቅደው ይታተማል፡፡ ታዲያ እንዴት አንድ ማኅበር የራሱን መዋቅር የጣሰ ለመሥራት ያቅዳል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ቦርዱን ማፍረስ ሲችል እንዴት ስለመጣስ ያስባል። እንዲህ ያለ ዕቅድ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅምና ዕቅድ አውጪዎቹ በጣም የተራቀቁ መሆን አለባቸው፡፡ ዕቅዳቸውን ለራሳቸው ጥብቅና ሲያቆሙት ቅድስቲቱን እምነት ለመበረዝ የተነሡ የተሐድሶ ኦርቶዶክስ ዓላማ አራማጆች ስውር ተልኮአቸው በአሁኑ ወቅት ስለተነቃባቸው ከገቡበት አዙሪት ለመውጣት ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ፡፡

ከዚህም መንገድ አንዱ ተሐድሶ የሚባል የለም የሚል መፈክራቸውን ማስተጋባት ነው፡፡ ዕቅድ ተብየውም ይህንኑ የተከተለ ሳያውቀው በስውር ዓላማቸው የተቃኘ የተነረተ የበሽታ ሆድ ሆኖባቸዋል፡፡ ስለሆነም ከዕቅዱ መካከል በአንዱ ላይ ታላላቅ የቤተክርስቲያን መሪዎችና ተሐድሶዎች /ፖለቲከኞች/ ናቸው በማለት ከምዕመኑ ሰላማዊ ቅብብል እንዳይኖራቸው የሚል ይገኛል /ቃላቱ እነርሱ እንዳስቀመጧቸው የተቀመጡ ናቸው/። በዚህ ዕቅድ ላይ ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን ማስተዋል እንችላለን፡፡አንደኛው ተሐድሶን ፖለቲከኛነት ጋር ለመቀላቀል መታሰቡ ሲሆን ሁለተኛው ግን ታላላቅ የቤተክርስቲያን መሪዎች ያሏቸውን የሚመለከት ነው፡፡ ተሐድሶ ማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲየንን ሙሉ በሙሉ ወደ ፕሮቴስታንት ጐራ ለመክተት አቅዶ የሚሠራ ሲሆን ፖለቲካኛ ደግሞ ሌላ ለዕቅድ አዘጋጆች ግን ተሐድሶና ፖለቲካ ተቀላቅሎባቸዋል፡፡ እውን  ተቀላቅሎባቸው ይሆንን? መልሱ ለአንባቢው የሚተው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ታላላቅ የቤተክርስቲያኗ መሪዎችን ማኅበረ ቅዱሳን ስማቸውን እንደሚያጠፋ ያመላክታል፡፡ ታላላቆችማ ታላላቆች ናቸው፡፡እነርሱን የሚቃወም ማንነቱ ግልጽ ነው፡፡ ስም ማጥፋትም ወንጀል ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ግን ተሐድሶ የሆኑትን ተሐድሶ ናችሁ ከማለት አስያፈገፍግም፡፡ ይህንን ሲያደርግ በማስረጃ እንጂ በተራ አሉቧልታ አይደለም፡፡ ነገር ግን ታላላቆችን አባቶች የሚነኩትን ማኅበሩም ዝም  አይላቸውም ተልኳቸው ይታወቃልና፡፡ ይሁን እንጂ ሊያስተላልፉ የፈለጉት ተሐድሶ የለም የሚለውን የዘወትር የጨለማ መጋረጃቸውን ለመሆኑ ማን ሁለት ጊዜ ያስባል? ድንጋይ ይቧጥጣሉ እንጂ መጋለጣቸው አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ የሐሰት ደበሎ ይገለጣል፡

የጽንሰ ሐሳብ ችግር

ከዝርዝር ዕቅዳቸው አንዱ ባልተጠኑ ትምህርቶች የቤተርክስቲያኗን ምዕመናን ደጋፊ ማድረግ ይላል። አንድ ጤናማና የሚያስብ አእምሮ ያለው ሰው ይህንን አባባል እንዴት ይረዳዋል? ብሎ መገመት እጅግ ቀላል ይሆናል፡፡ ዕቅድ እያቀደ ያለ አንድ አካል እንዴት ባልተጠና ትምህርት ሌላውን ሊያሳምን ይችላል? ዕቅዱን ያቀዱት ሰዎች የሰለቻቸው ይመስላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት /የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተማሪዎችን/ የሚያስተምረው በተጠና ሥርዐተ ትምህርት መሆኑን ያወቁ እንዴት ይህን ሊሉ ቻሉ? በርግጥም ደክሟቸው መሆን አለበት፡፡

የጽሑፉ ዓላማ

 ማኅበረ ቅዱሳን ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ማኅበራትና ልጆች ጋር በመቀናጀት በአሁኑ ሰዓት ፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ማዕበሉ እያንጓለለ የለያቸው ያሉ የተደራጁ  የሃይማኖት ጠላቶች ማምለጫ እስኪያጡ ድረስ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ የተዋሕዶ ምዕመናንን እየሰለቿቸው መጥተዋል፡፡ በመሸማቀቅ በቁማቸው አልቀዋል፡፡ ከመጠን በላይ በመደንገጣቸው ምክንያት ሳያስቡት የመጣባቸውን እውነት ለመጋፈጥ የሚያስችል መንፈሳዊ ተክለ ሰውነት አጥተዋል፡፡  ስለሆነም አቋራጭ የመሰላቸው የጨነገፈ ስልት ነድፈዋል፡፡ በዋነኛነትም የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ አስበዋል፡፡

በዚህም መንገዳቸው አንዱ የማኅበሩን ስም በድብቅ ሆኖ ማጥፋት ነው፡፡ እውነተኞች ሰዎች ከሆኑ ማንነታቸውን ገልጠው ፊት ለፊት በያዙት መረጃ በታገሉ ነበር፡፡ ለዚህ ያልታደሉ የመልካም ዘር ፀሮች በመሆናቸው መደበቁን መርጠዋል፡፡ ተደብቆ ውጭ ማኅበረ ቅዱሳን ሊያስበው ከቶውኑ የማይፈልገውን ያስቡለታል፡ ፡ “አዛኝ ቅቤ አንጓች” እንደሚባለው ሆኖባቸው በዚህ ስልት ማኅበሩን ለማጥቃት ሞክረዋል ራሳቸው ጽፈው ሊሰሙን ይችላሉ ብለው ለሚያስቧቸው አካላት ጽሑፉን ለመበተን ሞክረዋል፤ ይህንን ማድረጋቸውም አንድም አባቶችን ንቀዋቸዋል አለበለዚያም ተዳፍረዋል፡፡

ይህንን ከደረጃ ወጥቶ ጊዜ ወስዶ የተንኮታኮተ ጽሑፍ ዕቅድ ብለው ይዘው መዞራቸው በትክክል ማንነታቸውን ይገልጥባቸዋል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ማኅበረ ቅዱሳንን የማይመስል ወዘና የሌለው ወረቀት ብቅ ማድረግ ማንነታቸውን ገልጠዋል፡፡ በዝምታ ሊታለፉ አይገባቸውም፡፡

ማጠቃለያ
ይህንን ጽሑፍ ያሰራጩት አካለት እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉ ማንም ሰው መገመት ይችላል፡፡ ከመገመትም አልፎ አገኘሁ ብሎ ማኅበሩን ለማጥላላት የሚጠቀምበት ሁሉ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ተቀባዮችም የሰጪዎችን ማንነት ያውቃሉ፡፡ እንዲያውም ከማብራሪያ ጋር እንደተቀበሉ ይታመናል ፡፡

ስለሆነም፡-

1. ይህ የሐሰት ጽሑፍ የደረሳቸው አካላት ሰዎችን በማጋለጥ ሊተባበሩ ይገባል፤
2. ማኅበሩ እነዚህን አካላት በሕግ መጠየቅ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ የእነዚህን ሰዎች ማንነት አጣርቶ ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥን እንፈልጋለን፤

3. ይህ ጽሑፍ የደረሳቸሁ ምዕመናን በሐሰት ሥራ እንዳትታለሉ እናሳስባለን። አስፈላጊ ሆኖ ካገኙትም ወደ ማኅበሩ ጽ/ቤት በመምጣት ተገቢውን ውይይት ማድረግ እንደሚችሉ እንጠቁማለን።