በእንተ ልደቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት

ዮሐንስ ተመስገን

ታኅሣሥ ፳፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የዳሞት አውራጃ ገዚ ሞተለሚ በነበረበት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ በኢቲሳ መንደር ካህኑ ጸጋዘአብና እግዚኀረያ በትዳር ተወስነው ይኖሩ ነበር። ጸጋ ዘአብ በክህነቱ እግዚኀረያ በደግነቷና በምጽዋት ጸንተው በመኖራቸው በሕጉና በሥርዓቱ ለሚኖሩት ቀናዒ በመሆኑ እግዚአብሔር አምላክ ጎበኛቸው። ሃይማኖታቸውን የሚረከብ፣ እንዳባቱ ጸጋዘአብ የሚባርክ የአብራካቸውን ክፋይ ሊሰጣቸው ወደደ።

ነገር ግን የአውራጃ ገዢ ሞተሎሚ ጽኑ መከራን አደረሰባቸው። መልከ መልካሟን እግዚኀረያ ተመኝቶ ካህኑ ጸጋዘአብን ሊገድለው ፈለገ። ከተቀደሰው ትዳራቸውም ለይቶ ማሳደዱን ያዘ። እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ ከሞት ጠበቀው። እግዚኀረያ ደም ግባቷ ያማረ ነበረችና አረማዊው ንጉሥ ለትድምርት (ጋብቻ) ተመኛት። ንጉሡ እና ሠራዊቱ እየተከተሉ ቢያሳድዷትም የልብን ዐይቶ ከሰይጣን ወጥመድ የሚጠብቅ ጌታ በቅዱስ ሚካኤል በኩል እየተከተለ፣ በመንገድ እየመራ ባሕሩን ምቹ መሸሸጊያ እያደረገ ከአረማዊ ጋብቻ አስጠብቋታል።

ጸጋ ዘአብ በስደት ሆኖ እንኳን የተመረጠበትን የክህነት አገልግሎት አልዘነጋም ነበር። በደረሰበት ቦታ ሁሉ ባለች ቤተ ክርስቲያን ያገለግል ነበር። ከብዙ ድካምና ስደት በኋላ እርሱ ወደ ሚያገለግልባት ቤተ ክርስቲያን እግዚኀረያ በስውር መልአኩ ሚካኤል እየመራት ደረሰች። በአጸዱ ቁማ ስብሐተ እግዚአብሔር ስታቀርብ ካህኑ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ዙሪያውን እየባረክ፣ እያጠነ ነበር። እግዚኀረያ ዐይኗ ብቻ እስኪቀር ተካናንባ ነበርና ማንነቷን አላወቀም። እርሷ ግን ለየችው ካህኑ ጸጋዘአብ ነበር።

ተለያይተው የነበሩትን እግዚአብሔር በማይመረመር ጥበቡ አገናኛቸው። ለማሕፀኗ ፍሬ ይሰጣት ዘንዱ እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ሆነ፤ መጋቢት ፳፬ ቀንም ፀነች። በታኅሣሥ ፳፬ ቀን ቤታቸው በብዙ ተአምራትና በረከት ተሞልቶ  ወንድ ሕፃን ተወለደ። ሕፃኑንም ፍስሐ ጽዮን አሉት። ይህ ሕፃን አባቱ ጸጋዘአብን እየተከተለ አደገ። ካህኑ አባቱም ለዲቁና የሚያበቃውን ትምህርት እያስተማሩ በጥበብ አሳደጉት። ቅዱሳት መጻሕፍትን በተለይም ብሉይና ሐዲስ ኪዳንን አስተምረውታል። ዲቁናም በዘመኑ ከነበሩት የእስክንድርያው አቡነ ቄርሎስ ተቀብሏል።

ፍስሐ ጽዮን ጎን ለጎን በሥጋዊ ሥራው ብርቱ አዳኝ ነበር። አንድ ቀን ለአደን ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ ድምጽ ተሰማ። ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ነበር። አብረውትም አእላፍ መላእክት ነበሩ። ለአገልግሎት እንደእርሱ ፈቃድ የሚጠራ አምላክ ይህን ብላቴናም ይጠራው ዘንድ በዚህ ስፍራ ተገለጠለት። ለመረጣቸው ሥራ ከማሕፀን ጀምሮ የሚጠራ አምላክ ከደገኛ ወላጆቹ የተገኘውን ሐዋርያ የሚጠራበት ጊዜ ደርሶ ነበር።

ጌታችንም እንዲህ አለው ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት ይሁን። ከዚህ በኋላ እንስሳትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ሁል ጊዜም ካንተ ጋር ነኝ›› ብሎ በግርማ ዐረገ።  ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም የፈጣሪያቸውን ጥሪ ተቀብለው ጊዜ ሳያጠፉ ንብረታቸውን ለነዳያን መጽውተው በትር ብቻ ይዘው የቤታቸውን በር እንደከፈቱ እንደ አባቶቻቸው ለምናኔ ወጡ።

አባታችን ቅስና ተቀብለው ሸዋ ጽላልሽ አካባቢ ወደ አስርሺህ ነፍሳትን አሳምነው አጠመቁ። ይህ መጀመሪያቸው እንጂ የአገልግሎት መፈጸሚያቸው አልነበረምና በዮዲት ጉዲት ዘመን ክዶ የነበረውን የደቡቡን ክፍል ሊያስተምሩ ሐዋርያዊ ጉዞ አደረጉ። በዚህ አካባቢም ብዙዎችን አጥምቀዋል።

ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለሃይማኖት ጠንቋዮችን አጥፍተዋል፤ ድውይ ፈውሰዋል፤ እርኩስ መንፈስን ከበሽተኞች አውጥተዋል፤ ሃይማኖት ወደ ከበረ ሥፍራዋ መልሰዋል፤ ሙት አስነሥተዋል፤ እሳት ጨብጠዋል። ከመላእክት ጋር ጽና ይዘው አጥነዋል፤ ስድስት ክንፍ ተሰጥቷቸዋል።

ጻድቁ በኢትዮጵያ አላዊ ንጉሥ ተነሥቶ ከእስክንድርያ የመጡት ጳጳስ ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ ፕትርክና ከእግዚአብሔር ተቀብለው ሃይማኖት አቆይተዋል። ሀገር ሰላም ሁኖ ጳጳሱ ሲመለሱ በትሕትና ምእመናኑን አስረክበው እሳቸው ወደ ገዳም ተመልሰዋል።

ኢየሩሳሌም ተጉዘውም ሊሳለሙ ቢሔዱ፦ በቤተ መቅደስ ብሥራቱን፣ ቤተ ልሔም ልደቱን፣ በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣ በቤተ አልአዛር ተአምራቱን፣ በቀራንዮ ስቅለቱን በገሀድ አሳይቷቸዋል። ይህን ስቅለቱን አይተው ከዐይናቸው የፈሰሰው እንባ ቢያሳውራቸው በእመቤታችን ምልጃ ብርሃን ተቀብለው፣ ስድስት ክንፍ አብቅለው፣ የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣ ማእጠንተ ወርቅ ጨብጠው ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር መንበሩን አጥነዋል።

አባታችን በብዙ ተጋድሎና ጸሎት አምላካችንን አመስገነው፣ ሰይጣንን ድል አድርገው፣ ብዙ ገዳማትን መሥርተውና አቅንተው፣ ለሀገርና ለሃይማኖት ለረጅም ዘመናት እየጸለዩና እየተጋደሉ ይህን ከንቱ ዓለም በምናኔ አሳልፈዋል። ከትሕትናቸው የተነሣ የሚገባቸው ሁኖ ሳለ በረድእነት ለብዙ ዘመናት በተለያዩ ገዳማት አገልግለዋል። አንድ እግራቸው እስኪቆረጥ ድረስ በአንድ ቦታ ቁመው ለሃያ ሁለት ዘመናት፣ እግራቸው ከተሰበረ በኋላም በአንድ እግራቸው ለስድስት ዓመታት በአንድ በዓት ውስጥ ጸልየዋል።

እልፍ አእላፍ ፍሬ አፍርተው፣ ብዙ ደቀ መዛሙርትን ተክተው፣ ሃይማኖት አቅንተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመታቸው ዐርፈዋል።

ከበዓለ ልደታቸው ረድኤት በረከትን ይክፈለን፤ ቡራኬያቸው አይለየን።