በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በተከሰተው ችግር ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ!

 

                                                               እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል /ሮሜ  1419/

         በሀገራችን በኢትዮጵያ የሚካሔደውን የመንግሥት የአሠራር ለውጥ ተከትሎ ላለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በግጭቶችም ከሀብት ውድመት እስከ ክቡሩ የሰው ሕይወት ኅልፈት ድረስ መከሰቱ እና በዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማዘኑና ለመፍትሔውም በሚችለው ሁሉ መረባረቡ የሚታወቅ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት በሶማሌ ክልል የተከሰተው ግን በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በተለየ ሁኔታ አደጋ ውስጥ መክተቱ ደግሞ የበለጠ አሳዝኖናል፡፡ ይልቁንም ደግሞ ግጭቱ ሆነ ተብሎ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ሰፊ ጥፋት ለመቀስቀስ የታሰበ መምሰሉ በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ ሆኖም ክርስቲያኖችም ሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮች ነገሩን በጥንቃቄና ኃላፊነት በሚሰማው ሁኔታ እንደሚይዙት እምነታችን ታላቅ ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና አማኞች ላይ ልዩ ትኩረት አድረገው ግድያ መፈጸማቸው፣ አብያተ ክርስቲያንን ማቃጠላቸው እና የአማኞቹን ሀብት ንብረት መዝረፋቸውና ማቃጠላቸውም ቢሆን ለሟቹቹ የሰማዕትነትን ክብር ከማቀዳጀቱና ለቤተ ክርስቲያንም ጸጋና ኃይል ከማጎናጸፍ ያለፈ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያኖች “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” /ዮሐ 16፥33 / በሚለው የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል አምነውና ታምነው የሚኖሩ የሰላም ሰዎች ናቸውና፡፡ ሰማዕትነቱም ቢሆን ለሟቾቹ ብቻ ሳይሆን መከራውን፣ ስቃዩንና ጭንቀቱ ሁሉ ለደረሰባቸው ሁሉ ነውና ሥርየተ ኃጢአትንና ጸጋ እግዚአብሔርን ያበዛላቸዋል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፋት አይችልም፡፡ እንዲያውም በዘመነ ሰማዕታት እንደሆነው በሌላ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ለሰማዕትነት የሚያበቃ በዚያ ጉዳት የደረሰባቸውንም በመርዳት፤ አብያተ ክርስቲያኑንም የበለጠ አድርጎ በመሥራት የሰማዕትነቱ ተካፋይ የመሆን እድል ይሰጣቸዋል፡፡ በፍትሐ ነገሥታችን አንቀጸ ሰማዕታት ላይ እንደተገለጸውም በዚያ የተጎደቱን ለመርዳት የሚረባረቡ ሁሉ ቁጥራቸው ከሰማዕታት ስለሆነ በመንፈሳዊ ዐይን ለሚያዩት ሁሉ ጥቅም እንጂ ጉዳቱ እምብዛም ነው፡፡

ለክርስቲያኖች እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ጠቀሜታ ቢኖረውም የሰው ሕይወት ክቡር ከመሆኑ የተነሣ ደግሞ በማናቸውም የሰው ልጆች ላይ ያለአግባብ የሚደርሰው ጥፋት በእጅጉ ያሳዝነናል፤ ያሳስበናልም፡፡ ስለዚህም ከመንግሥት ጀምሮ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ ይህን የመሰለ ችግር እየሰፋና እየተበራከተ እንዳይሔድ ቅድመ ጥፋት የጥንቃቄና የሰዎችን ሁሉ የደኅንነት ዋስትና የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ዐይነት ድርጊት የተሳተፉ አካላትንም ለሕግ በማቅረብ ለሰዎች ዋስተናን ለአጥፊዎችም ትምህርትን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ጥፋት አድራሾቹ “የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም” /ሮሜ 3፥17-18 / ተብሎ በቅዱሱ ሐዋርያ የተነገረላቸው መሆናቸውን ለመረዳት አይቸግርም፡፡ ስለዚህም እነዚህ አካላት የየትኛውንም ሃይማኖት የማይወክሉና የራሳቸውን ሰላም አጥተው የሌሎቻችንም ለመውሰድ የተነሡ መሆናቸውን ተረድቶ የእነርሱ ጠባይን ላለመውሰድና ለበቀልና ለመሳሰሉት ተጨማሪ አደጋ አምጭ ነገሮች ተጋላጭ እንዳሆን መጠበቅም ክርስቲያናዊ ብቻ ሳይሆን የመልካም ዜግነት ግዴታችን መሆኑንም ለማስታወስ እንወድዳለን፡፡  በዚህ አጋጣሚ ጥፋቱ ከደረሰው በላይ እንዳይሆን ስትከላከሉና የመልካም ዜግነት ግዴታችሁን ስትወጡ ለነበራችሁ ክቡር የሱማሌ ክልል ህዝብ ከፍ ያለ አክብሮታችንን እናቀርብላችሀለን፡፡ አሁንም በየመጠለያውና በየቦታው ያሉ የጉዳት ሰለባዎችን በመደገፍና ከወደቁበት በማንሳት አርአያነታችሁን እንድምታሳዩንእናምናለን፡፡

በሶማሌ ክልልና በሌሎችም ሆናችሁ ይህ አደጋ የደረሰባችሁ ክርስቲያኖችም ነቢዩ ኢሳይያስ “በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ” /ኢሳ 26 ፤ 3/ ሲል በተናገረው ቃለ መጽሐፍ ተማምናችሁ ብትጸኑ ለሰማዕትነት ክብር ከታጩት በቀር እግዚአብሔር እንደሚጠብቃችሁ የታመነ አምላክ ነውና አትረበሹ፡፡ ከዐለም የሆነው ሁሉ ስለመጥፋቱም አትጨነቁ፡፡ “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” /ማቴ 6 ፤ 25/ ሲል ያስተማረንን ጌታችንን አስታውሳችሁ እንድትጸኑ በፍጹም ፍቅርና ትሕትና ልናሳታውሳችሁ እንወድዳለን፡፡ እንደታዘዝነውም ለሚያሳድዷችሁና መከራውን ላመጡብን ሁሉ ከልብና ከእውነት እንጸልይላቸው፤ ጌታችንን አብነት አድረገንም በአንድነት አቤቱ  የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብለን በየዕለቱ እንጸልይላቸው፡፡ በየትም ዐለም ያለን ክርስቲያኖች ሁላችንም ከመቼዉም ጊዜ በላይ ስለቤተ ክርስቲያናችን፣ ስለሀገራችንና በስደትና በመከራ ላይ ስላሉት ሁሉ እግዚአብሔር በሃይማኖታቸው መጽናትን፤ በፍቅርም ይቅርታ ማድረግን በልቡናቸው ይጨምር ዘንድ በጥፋት ጎዳናም ያሉት ልቡና አግኝተው ይመለሱ ዘንድ ጊዜ ወስደን ሥራዬ ብለን ልንጸልይ ይገባናል፡፡ ከዚህም በሻገር ከሰማዕትነት ክብር እንካፈልና እኛንም ልንሸከመው ከማንችለው ፈተና እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘንድ የተፈናቀሉትን ለማቋቋም፣ የተቸገሩትን ለመርዳት፣ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያንን ለማሳነጽና የሰማዕታቱን ቤተ ሰቦች በዘላቂ ለመርዳት መነሣሣትና ኃላፊነታችንን በአግባቡ በፍጥነት ልንወጣ ይገባናል፡፡

ጉዳት በማድረስ ከምክር እስከ ገቢር የተሳተፋችሁትም በማወቅም ባለማወቅም ከፈጸማችሁት ጥፋት ትመለሱና የእግዚአብሔርንም ይቅርታ ተገኙ ዘንድ “ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም” /መዝ 34፥14/  በሚለው ቃለ መጽሐፍ እንለምናችኋለን፡፡ የማትመለሱ ከሆነ ግን እርሱ የቁጣ ፊቱን ወደ እናንተ ባዞረ ጊዜም ሊያድናችሁ የሚችል ኃይል የለም፡፡ በነቢዩ ዳዊት “እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም” /መዝ 50 ፤ 22/ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ስለዚህም ይህን አምላካዊ ማስጠንቀቂያ አስባችሁ እንድትመለሱና ሀገራችን የሰላምና የፍቅር ሀገር እንድናደርጋት በእውነት እንማጸናችኋለን። ሁላችንም ልንጠቀም የምንችለው በሰላም፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ብቻ ነውና በታላቁ ሐዋርያ በቅዱስ ጳውሎስ ቃል “እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል በማለት ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን /ሮሜ  14፥19/።

እግዚአብሔር አምላካችን ሀገራችንን ሕዝቦቿን ሁሉ በጽኑ ሰላም ይጠብቅልን፤ አሜን፡፡

 ማኅበረ ቅዱሳን