በአገልግሎታችን የሚከሰቱ ፈተናዎችን የምናልፋቸው በእግዚአብሔር ኃይል ነው

 ኅዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም.

ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠናከር በርካታ ተግባራትን እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ ሲፈጽም የቆየ የአገልግሎት ማኅበር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን ማኅበሩ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመንፈሳዊ ዓላማ የተቋቋመ ቢሆንም መልካም ነገርን የማይወደው ጥንተ ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስ የተለያዩ ፈተናዎችን ሲጋርጥበት ኖሯል፡፡ ማኅበሩም የሚደርሱበትን ፈተናዎች ከምእመናን፣ ከካህናትና ከብፁዓን አባቶች ጋር በመሆን በትዕግሥትና በጸሎት ሲያልፋቸው ቆይቷል፡፡

 

አንዱን ሲያልፍ ሌላው እየተተካም ከዚህ ደርሷል፡፡ ምንም እንኳን በየጊዜው ፈተናው መልኩን እየቀየረ ቢመጣም ማኅበሩ ከኃይለ እግዚአብሔርና ከአባቶች የኖላዊነት ተግባር ውጭ የሚመካበት ነገር የለውምና ይህንኑ አጋዥ አድርጎ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋትን ያህል ባይሆንም “ጋን በጠጠር ይደገፋል” እንዲሉ የተቻለውን አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በየጊዜው ከተነሡት ፈተናዎች መካከል አንዱ በቅርቡ የተከሰተውና ማኅበሩን ቅድሚያ በማኮላሸትና በመምታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት የሸመቀው የአፅራረ ቤተ ክርስቶያንና የተሐድሷውያኑ ዘመቻ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ በመመዝበር የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት በሚጥሩ ኃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ እንቅሰቃሴ ነው፡፡ እነዚህ አካላት በተደጋጋሚ እያቀዱ የጀመሩት አልሳካ ሲል «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባንሔድ፣ ከፈቃዱም ተቃራኒ ብንሆን ነው» ብለው ራሳቸውን ከመመርመር ይልቅ ውስጥ ለውስጥ ሥራቸውን ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ በዚህ በያዝነው ዘመን መስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ በስውር ሲያደርጉት የነበረውን ፈተና በስም ማጥፋት መልኩ ወደ ዐደባባይ ማውጣት ጀመሩ፡፡

 

የቤተ ክርስቲያኒቱን አምልኮተ እግዚአብሔር ወደ ተሐድሶ መናፍቅነት ለመቀየርና የግል ጥቅማቸውን ለማካበት የሚፈልጉት እነዚህ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን “ለእንቅስቃሴያችን ማኅበሩ እንቅፋት ነው፤ ማኅበሩ ካለ ያሰብነውን ማሳካት አንችልም” የሚል የጥፋት አቅጣጫ ይዘው በመነሣት ከተለያዩ አካላት ጋር ሊያጋጩት ሞከሩ፡፡ የውሸት ክስ ጸንሰውም በዐደባባይ ማኅበሩን ወቀሱት፡፡ አንደበታቸው ባቀበላቸው ልክ የስድብ ናዳ አወረዱበት፡፡ በሠሩት ጎዳና እንደ ልባቸው ለመመላለስ እንዲረዳቸውም ያሸማቀቅንና ያስፈራራን መስሏቸው አገልጋይ ምእመናንንና ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆሩ ብፁዓን አባቶችን አሻቅበው ተሣደቡ፡፡

በጣም የሚደንቀውና የሚገርመው እነዚህ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓመት አንድ ጊዜ የምትጠራውን የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ዓለማዊ በሆነ ጥበብ መጠቀሚያ ለማድረግና ውጤቱም በቀጣዩ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተፅፅኖ እንዲፈጥር በማሰብ በስብሰባው ውስጥና በማይጠበቅ ቦታ የማይጠበቅ ተግባር የፈጸሙ መሆኑ ነው፡፡

በዚህ ድርጊት ያዘነው ሕዝበ ክርስቲያን ግን ፈተናዎቹ ዐዲስ ባይሆኑበትም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ዐሥራት በኩራታቸውን በሚያዋጡ ምእመናን ገንዘብ የሚኖሩ አገልጋይ ነን ብለው ራሳቸውን በሚያሞካሹ የተወሰኑ ግለሰቦች እንደዚህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር መፈጸሙ እንደ መንፈሳዊነቱ የሚያሳዝን ቢሆንም ለእውነት የቀና ልቡናን ስጣቸው ብሎ ወደ ፈጣሪ ከመጸለይ ውጭ የሚለው የለም፡፡ እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሐ የሚሰጥና ሁሉን የሚፈጽምበት የራሱ ጊዜ አለው፤ እስከዚያው ድረስ ግን ውሸት የሕዝበ ክርስቲያኑን ኃዘን ግምት ውስጥ ሳታስገባና ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይገሥጸኛል ሳትል በዐደባባይ ፈረስ መጋለቧን በመቀጠሏ የቤተ ክርስቲያን ልዕልና እየተነካ፣ በቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ሰዎች መስለው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች መልካም ስም ላላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላሸት የሚቀባ እየሆነ መጣ፡፡

 

የራሷን ችግር በራሷ መፍታት የምትችለው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሥርዓት አልባዎች ሥርዓት የሌላት እስከመምሰል ደረሰች፡፡ ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስፋፋት ውሳኔ እንደሚሰጥና ችግሮችን ሁሉ እንደሚፈታ ያምናልና በመንፈስ ቅዱስ ለሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ፍትሕ ያገኝ ዘንድ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ ጥያቄውን አቀረበ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ወሳኝ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስም ሁኔታውን አጥንቶና አጣርቶ በምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ ሰጠ፡፡ ይህም በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን የሆኑ አካላት ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡

ማኅበሩም በተፈጸመበት የስም ማጥፋት ድርጊት እጅግ ያዘነ ቢሆንም፣ ከንቱ የሆነውን ውንጀላ እንደ ፈተናነቱ ከመቀበል ውጭ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ያላደረገውን አደረገ፤ የሠራውን አልሠራም እየተባለ ፍጹም አሳዛኝ የሆኑ የስም ማጥፋት ጾሮች የተወረወሩበት ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት፣ ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሐ የሚሰጥበት ቀን አለው ብሎ ስለሚያምን እግዚአብሔር እንደፈቀደ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ምእመናን በጸሎትና በዕንባ፣ በየበረሃውና በየገዳማቱ ያሉ መነኮሳት በምኅላ፣ የማኅበሩ አገልጋዮች በትዕግሥት፣ ብፁዓን አበው በውሳኔያቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያልሆነውን መንፈስ ገሠጹት፡፡

ይህንን ከቅዱስ መንፈስ ያልሆነ ትጋት ቅዱስ ሲኖዶስ መርምሮ እንዲቆምና እንዲታረም አቅጣጫ ባይሰጥበት ኖሮ የቤተ ክርስቲያኒቱን ንጹሕ አገልግሎት አዳክሞና ጥላሸት ቀብቶ የሚያልፍ ነበር፡፡ ይህም አፅራረ ቤተ ክርስቲያን መረባቸውን ከላይ እስከ ታች የዘረጉት የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞችና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረት የግል ሀብታቸውን ማካበት የለመዱት አማሳኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና ተደፋፍረው እንዳልሆነች ለማድረግ በመቀናጀት የተንቀሳቀሱበት ነው፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ የተደበቀውን መርምሮ፣ የራቀውን አቅርቦ ለጥፋት የተነሣሣውን መንፈስ ገሥጾታል፡፡

በዚህ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት መጠናከር አኩሪ በሆነው መንፈሳዊ ውሳኔ ምእመናን፣ አገልጋይ ካህናትና የገዳማት አባቶች ከእሱ ፈቃድ ውጭ ምንም ማድረግ የማይቻልበትን እግዚአብሔርን በማመስገን፤ እንደ ቀድሞው ሁሉ ተስፋቸውን በዚሁ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በኋላም ቢሆን እንኳን ለእኛ ለደካሞቹ፣ ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያልተኛው ጠላት ዲያብሎስ የተቃናውን ለማጣመም፣ የቀረበውን ለማራቅና የተሰበሰበውን ለመበተን ጦሩን ወደ ሰገባው አይመልስምና ባንዱ ሲሸነፍ በሌላ አቅጣጫ እየመጣ የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት ለማደናቀፍ ጉድጓድ መቆፈሩ ስለማይቀር እንደነዚህና መሰል ችግሮች ከዚህ በኋላም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እንደ ሰሞኑ ሁሉ ወደ ፊት የሚመጣውን የሰይጣን ፈተና ኃይለ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ እንዲገሠጽ፤ ከላይ እስከ ታች በየተዋረዱ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን ፈተናውን በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ለማለፍ በጸሎትና በአገልግሎት ሊተጉ ይገባል፡፡

ክርስቲያን ኃይሉ እግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን በጸሎት በመጠየቅ እያንዳንዱ ነገር ሲከሰት ምን ይዞ እንደመጣ፣ የተቀነባበረበትን ዓላማ በመረዳትና በመገንዘብ ለቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግሎት «እንደ ርግብ የዋኆች እንደ እባብ ልባሞች ሁኑ» ማቴ. 10÷16 ተብሎ የተጻፈውን አምላካዊ ቃል መፈጸም ይሆናል፡፡ የችግሩን ምንጭ ከሥር መሠረቱ ከተረዱ በኋላም ለቤተ ክርስቲያን በመናገርና ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው ውሳኔና አቅጣጫ መሠረት ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ የተጠናከረ ሆና ትቀጥል ዘንድ በአገልግሎትና በጸሎት መትጋት ያስፈልጋል፡፡

ምእምናን፣ በየተዋረዱ ያሉ አገልጋይ ካህናት እንዲሁም ብፁዓን አባቶች ለቤተ ክርስቲያን በሚያደርጉት መንፈሳዊ ጽናትና ትጋት የሰይጣን ቀስት እየወደቀ፣ አቅሙ እየደከመ፣ ተስፋ እየቆረጠ ይሔዳል፡፡ በዚህም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከመቼውም በላይ የተፋጠነ ሆኖ፤ ክብሯ ሳይነካ፣ ማንነቷ ሳይበረዝ ሥርዓቷና ትውፊቷ እንደተጠበቀ ከትውልድ ወደ ትውልድ ትቀጥላለች፡፡

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቀናው ማኅበረ ቅዱሳን የፈተናዎቹ ጥንስስና ዝግጅት በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማይጠበቅ በመሆኑ ቢያዝንም በአባላቱ ፅናት፣ በምእመናን ድጋፍና በብፁዓን አባቶች ውሳኔ ሥውሩ ደባ ስለተገለጠ፤ በጨለማ ወይም በግንብ ውስጥ ወይም ማንም አላየኝ በሚል በስውር ሆኖ ማንም ቢሠራ ከእሱ ሊሠወር የማይችለው እግዚአብሔር፣ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን ያስታግሥልን፤ አገልግሎታችንን ይባርክልን፤ አባቶቻችንን ይጠብቅልን ከማለት ውጭ የሚለው ነገር የለም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ፅኑ ዓላማው ኃይለ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመልካም ጎዳና ላይ እንድትራመድ ሲሆን፤ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ የሚያዝነው ደግሞ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መገፋትና የነገረ ሃይማኖት መፋለስ ሲደርስ ነው፡፡

 

በመሆኑም በእውነት በማኅበሩ የተፈጸመው የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት ከእውነታው ውጭ በሆነ መንገድ በዐደባባይ ሲሰደብና ሲከሰስ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ አዝኗል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሲሰጥ ደግሞ ውሳኔው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ስለሚበጅ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባው ብሏል፡፡ ለዚህም የምእመናን ኀዘን፣ በየተዋረዱ ያሉ የአገልጋይ ካህናትና ብፁዓን አባቶች ጥረትና ትጋት እግዚአብሔር ከሰጣቸው ሓላፊነት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከውንጀላዎቹ በስተጀርባ ከተዘጋጀው ዕቅድ አንፃር የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አባቶች የኖላዊነት ተግባር ሁላችንም እንድናይ አድርጎናል፡፡

ምንም እንኳን እግዚአብሔር አምላክ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለሚገፉና በእውነት ወደ እርሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ዋጋ የሚከፍል ቢሆንም፤ በሰው ሰውኛው ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቆጩና የሚያዝኑ ምእመናንንና ደፋ ቀና የሚሉ አባቶችን የአገልግሎት ዘመን ይባርክልን ልንልበት ይገባል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ምድራዊ ያልሆነ ሰማያዊ ዋጋ ለማግኘት ስለሆነ የሚገፋውና የሚተቸው በዚህ ምክንያት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ካለው ቁርጠኛ አቋም የተነሳ ነው፡፡ ዓላማው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ነውና ይህንን ዓላማውን እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ፣ በብፁዓን አበው ፈቃድ ተመርቶና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እናት አድርጎ እንደ ባለቤቱ ፈቃድ ይቀጥላል፡፡ ክርስትናና ፈተና እስከመጨረሻው ትግል እየገጠሙ የሚኖሩ እንደ መሆናቸው መጠን የቱንም ያህል ለማገልገል በሚያደርገው ሩጫ ስሕተት ከታየበትም በአባቶች ለመታረምና ለመታዘዝ ዝግጁ ሆኖ አገልግሎቱን ይፈጽማል፡፡ ጠላት ቢነሣበትና ስለ ቤተ ክርስቲያን ግፍ ቢደርስበት እግዚአብሔርን እስከ ያዘ ድረስ ከዓላማው ወደ ኋላ አይልም፡፡

በመሆኑም በየወቅቱ ለሚከሰቱ ፈተናዎች ኃይለ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የምድራዊቷን ሳይሆን የሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም ወራሽ ለመሆን በጸሎት ከመትጋት ውጭ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ጠላት ዲያብሎስን የሚያሳፍርበት መንገድ የለውምና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በየጊዜው ለሚከሰቱ ችግሮችና በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ለሚነሱ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለሚሸረሽሩ ፀረ ኦርቶዶክሳዊ አቋሞች ሕዝበ ክርስቲያኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ውሳኔ መስጠታቸውን በፅናት የተከታተለበት ሁኔታ ምንጊዜም ከአንድ ሕዝበ ክርስቲያን የሚጠበቅ ነው፡፡

ፈተናው በቤተ ክርስቲያን ላይ እንጂ በማኅበሩ ላይ ብቻ የመጣ ስላልሆነ እያንዳንዳችንም ለምድራዊ ሕይወታችን ስንተጋ ቤተ ክርስቲያንን ስለረሳንና እግዚአብሔር ስለሚወደን ፈተናው ለተግሣፅ፣ ለአመክሮና ለተዘክሮ የመጣ ነው ብለን ማመን አለብን፡፡ በመሆኑም ከቤተ ክርስቲያን የራቅን ቀርበን፤ ራሳችንን በቅዱስ ቃሉ በማነፅ፤ በሰበካ መንፈሳዊ አገልግሎት በትጋት በመሳተፍ፤ ዐሥራት በኩራታችንን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመስጠት፤ ልጆቻችንን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በሰንበት ትምህርት ቤት ተኮትኩተው እንዲያድጉና ተተኪ እንዲሆኑ በማድረግ፤ ሩቅ ሆነን ይህ ጎደለ በሚል ብቻ ጣት ቀሳሪዎች ሳንሆን፤ ባለቤቶችና ችግር ፈቺ እንዲሁም የጎደለ ሞይ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንና የአባቶች ተላላኪና አጋዥ መሆን እንደሚጠበቅብን ልንገነዘብ ይገባል፡፡

 

ይህ ክስተት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን የዋጀች ሆና አገልግሎቷን በሰፊው ለማድረስ ከሚጠበቅባት አንፃር ያለችበትን ሁኔታ እንድናውቅ ያደረገበት አጋጣሚ ስለሆነ፤ ከምንጊዜውም በላይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁላችንም እንደየአቅማችንና ተሰጥዎአችን ድርሻችንን ልንወጣ ያስፈልጋል፡፡ አላወቅንም እንዳንል በምንወደው ድራማ በሚመስል እውነተኛ ታሪክ የተገለጸልን መልእክት ገና ያልበረታን መሆናችንን እግዚአብሔር በማየቱ ለማስተማር ነውና፤ ዋጋ በመስጠት «የሰው ልጅ ሕይወቱንና ዘለዓለማዊ ቤቱን አጥቶ ዓለሙን ቢያተርፍ ምን ይበጀዋል» ተብሎ እንደተጻፈ ማቴ 16÷26 ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከቀድሞው ይልቅ ልንተጋ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ባለማወቅ የእርሱን መለኮታዊ ኃይል በመገዳደር እና በድፍረት ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያሳድዱ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን ልቦናቸውን መልሶ፤ ማስተዋልን ያድልልን፤ ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ደፋ ቀና የሚሉትን ምእመናንን፣ ካህናትንና ብፁዓን አባቶችን ይጠብቅልን፤ ያበርታልን፡፡

በአጠቃላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፈተናዋ ብዙ እየሆነ በመምጣቱ ልጆቼ! በማለት በምትጣራበት በዚህ ዘመን ልትልከውና በትክክለኛ አቅጣጫ ልትመራው የሚቻላትን ልጇን፣ እንደ ባዕድ ሰው ቆጥሮ ይህን ያህል ዘመቻ ለማድረግ የተሄደበት ሁኔታ ላላየው ሰው መታመን የማይችል ቢሆንም በመንፈሳዊ ዐይን ከተመለከትነው፡- ፈተናዎቹ የምንማርባቸውና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ስም ያስነሱ ከመሆናቸው በቀር በግለሰብ ደረጃ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ የሌለባቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ዙሪያ እያንዳንዳችን የቆየንባቸውን መንገዶች አግባብነት በጥበብ ሰማያዊ ደግመን ደጋግመን በመመርመር ለሰማያዊ እንጂ፣ የዚህ ዓለም ለሆነው ከንቱ ነገር እልህ ሳይዘን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማጠናከር የሚያስችሉ ነገሮችን በመተጋገዝና በፍቅር ልንሠራ ይገባል፡፡

 

ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የቆመው ማኅበረ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር በቀር ፍጹም የሆነ ማንም እንደሌለ በማመን፣ ካጠፋ ምንጊዜም ለመታረም ዝግጁ፣ በአባቶች ሲታዘዝም የተቻለውን ለመፈጸም የቀና፣ ለሕግና ለሥርዓት ተገዥ ሆኖ የሚሠራ መሆኑን እያረጋገጠ፤ ቀሪ የሆኑት ምድራዊ ሀብቶች እያንዳንዳችንን ጠልፈው ሳይጥሉን፣ የእግዚአብሔርን ኃያልነትና ቻይነት ሳንዘነጋ ራሳችንን እየመረመርን በታሪክ ተወቃሽ፣ በእግዚአብሔርም ተጠያቂ ላለመሆን በሰጠን ጸጋ ለመልካም ነገርና ለተቀደሰው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቢያንስ እንቅፋት ላለመሆን ከበረታንም በመክሊታችን አትራፊ በመሆን፣ ምድራዊቷን ሳይሆን ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም ለመውረስና ሌሎችም እንዲወርሱ ምክንያት ለመሆን እንትጋ በማለት ማኅበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

ምንጭ፡- ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኅዳር 2007 ዓ.ም.