በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስም የተገነባው ዘመናዊ ሕንጻ ተመረቀ፡፡

ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በደመላሽ ኃይለ ማርያም

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በከላላ ወረዳ ቤተ ክህነት በ፳፻፫ ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ መሠረቱ የተቀመጠው፣ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስም የተገነባው ባለ ሦስት ፎቅ ኹለገብ ዘመናዊ ሕንጻ ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ተመረቀ፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይም ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሊቃውንት ጉባኤ ሓላፊ፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝና ሌሎችም የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የዞኑ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ማኅበሩ ከሚሠራቸው ፻፳ወ፮ (126) ፕሮጀክቶች መካከል ይህ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ፕሮጀክት አንዱ መኾኑን ገልጸው፣ ከመሠረቱ መቀመጥ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የየመምሪያ ሓላፊዎች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህ ዘመናዊ ሕንጻ በከተማው ካሉት አራት ሕንጻዎች መካከል አንዱ ሲኾን፣ በውስጡም ለእንግዳ ማረፊያ አገልግሎት የሚውሉ ዐሥራ ስምንት ክፍሎች፣ የባንክ ወይም የምግብ አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል፣ ለንግድ ሥራ የሚኾኑ ሱቆች እና ሌላም ሥራ ሊሠራባቸው የሚችሉ ክፍሎችን የያዘ ሲኾን፣ ከዚህ ኹሉ አገልግሎት የሚገኘው ገንዘብ ተሰብስቦ ለደብረ ባሕርይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና አባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም አገልግሎት ማጠናከሪያነት እንደሚውል የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር የኾኑት ዲ/ን አእምሮ ይሄይስ አስረድተዋል፡፡

ዲ/ን አእምሮ አያይዘውም የአባ ጊዮርስ ዘጋሥጫ ዘመናዊ ሕንጻ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የበላይ ሓላፊነት በሚዋቀረው ኰሚቴ እንደሚመራ ገልጸው፣ በዚህም የማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ የሚቀጥል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስና ሌሎች የክብር እንግዶች ሕንጻውን ከጐበኙ በኋላ በአባቶች ጸሎት እና ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾኗል፡፡