weyenute

በንብና ነብር የምትጠበቀው ሥዕለ ማርያም “ወይኑት”

 ኅዳር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በእንዳለ ደምስስ

 

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ገዳማት መካከከል በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙት የመርጡለ ማርያም እና ደብረ ወርቅ ገዳማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ገዳማት ጥንት መሥዋዕተ ኦሪት ይከናወንባቸው የነበረና ታላላቅ ታሪካዊ ቅርሶችንም ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትልቁን ድርሻ ከያዙት ቅዱሳት መካናት መካከል ይመደባሉ፡፡

 

መስከረም 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ ጥሪ መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚመራና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት የልዑካን ቡድን መርጡለ ማርያም ገዳም አዲስ ለሚሠራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ለማኖር፤ እንዲሁም በደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም የተገነባውን መንበረ ጵጵስና ለመመረቅና ለዘመናዊ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ለማኖር ከሄደው ልዑክ ጋር ተጉዣለሁ፡፡

በመርጡለ ማርያም ገዳም የነበረን ቆይታ አጭር በመሆኑ መረጃዎችን ለማሰባበሰብ የጊዜ እጥረት ስላጋጠመኝ አልተሳካልኝም፡፡ በደብረ ወርቅ ገዳም ቆይታዬ ከቋጠርኳቸው መረጃዎች መካከል ቅዱስ ሉቃስ ከሣላቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ቅዱሳት ሥዕላት መካከል በንብና ነብር የምትጠበቀው ሥዕለ ማርያም /ምስለ ፍቁር ወልዳ/ “ወይኑት” ስለተሰኘችው ሥዕል ጥቂት ላካፍላችሁ፡፡ ደብረ ወርቅ ማርያም ገዳምን ላስቀድም፡፡

 

ደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም

ደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በእናርጅና እናውጋ ወረዳ ከአዲስ አበባ 290 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የኦሪት መሥዋዕት ሲሰዋባቸው ከቆዩት ቅዱሳት መካናት አንዷ ናት፡፡ በተለይም ከ250-351 ዓ.ም. መሥዋዕተ ኦሪት ሲሰዋባት እንደቆየች የጽሑፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

የጎጃም አፈ ጉባኤ በነበረው ምሑረ ኦሪት ያዕቆብ አማካይነት መሥዋዕተ ኦሪት ሲሰዋባት የቆየ መሆኑን በገዳሟ የሚገኙ የኦሪት ሥርዓት ማከናወኛ የነበሩ እንደ መቅረዝ፤ ስንና ብርት የመሳሰሉ ቅርሶች ከመመስከራቸውም በላይ በገዳሟ ውስጥ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ መዝገብ ያስረዳል፡፡

 

weyenuteእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ስትሰደድ ካረፈችባቸው ቅዱሳት መካናት መካከል አንዷ ደብረ ወርቅ መሆኗንም በድርሳነ ኡራኤል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የነገሡት ወንድማማቾቹ አብርሃና አጽብሃ ክርስትናን እያስፋፉ ከቦታ ቦታ ይዘዋወሩ በነበረበት ወቅት መርጡለ ማርያምን አቅንተው ክርስትናን መሥርተው ወደ ደብረ ወርቅ በመምጣት ከምሁረ ኦሪት ያዕቆብ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ያዕቆብን ክርስትናን አስተምረው የአዲስ ኪዳን ሥርዓትን በመመሥረት “ያዕቆብ ኤጲስ ቆጶስ ዘኢየሩሳሌም ደብረ ወርቅ” ብለው ሾመውታል፡፡

 

አብርሃና አጽብሃ ደብረ ወርቅ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሳይሠሩ ዐረፍተ ሞት ስለገታቸው በእግራቸው የተተካው ዐፄ አስፍሐ ያልዝ በ351 ዓ.ም. ወደ ደብረ ወርቅ በመምጣት ቤተ ክርስቲያኗን አሰርቷል፡፡ የደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም በዮዲት ጉዲት በመቃጠሏ በ1372 ዓ.ም. በዐፄ ዳዊት የገንዘብ ድጋፍ አባ ሰርፀ ጴጥሮስ በተባሉ አባት አማካይነት በድጋሚ ተሠርታለች፡፡ ከጊዜ በኋላም ቤተ መቅደሷን ዐፄ ገላውዴዎስ በኖራና ድንጋይ ሲያሠሯት፤ ቅኔ ማኅሌቷ ደግሞ በስክ እንጨት ካለምንም ምሥማር በዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ተሠርታለች፤ በ1963 ዓ.ም. ዐፄ ኃይለ ሥላሴም አሳድሰዋታል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ 44 ቆመብዕሴ/አምድ/፤ የውጪና የውስጥ 11 በሮች፤ 36 መስኮቶች ሲኖሯት የግድግዳ ላይ ሥዕሎቹ ዐፄ ዮስጦስ /1704 ዓ.ም./፤ 1873 ዓ.ም. የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ልጅ የሆኑት ራስ ኃይሉ አስለውታል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ በርካታ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችም ይገኛሉ፡፡

 

“ወይኑት” ቅዱስ ሉቃስ የሣላት ሥዕለ ማርያም

ዐፄ ዳዊት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል ጋር ወደ ኢትዮጵያ ካመጧቸው የቅዱስ ሉቃስ ሥዕላት መካከል “ወይኑት” የተሠነችው ሥዕል አንዷ ስትሆን ዐፄ ዘርዓweyenute 2 ያዕቆብ ለደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም አበርክተዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም ተጠብቃ ትገኛለች፡፡ በ1660ዎቹ ዓ.ም. በዐፄ አእላፍ ሰገድ /ፃድቁ ዮሐንስ/ ለወይኑት ማስቀመጫ እቃ ቤት ይሆን ዘንድ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ በድንጋይና በኖራ በማስገንባት ጣሪያውን የሣር ክዳን በማልበስ አሠርተውላታል፡፡ ፎቁ ላይ ትናንሽ 8 መስኮቶችም ይገኛሉ፡፡

 

ሥዕለ ሉቃስ “ወይኑት”ን የሚጠብቁ ነጫጭ ንቦች የሚገኙ ሲሆን ጥቋቁር ንቦቹ ደግሞ ከመስኮቶቹ እየወጡና እየገቡ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ንቦቹ ከሕንፃው መሠራት ጋር እንደገቡ የሚነገር ሲሆን ማሩ እስካሁንም ተቆርጦ አያውቅም፡፡ ወይኑት በዓመት ለሦስት ጊዜያት ሕዝቡን ለመባረክ ወደ ቤተ መቅደስ ትወሰዳለች፡፡ መስከረም 21፤ ጥር 21 እና ነሐሴ 16፡፡ ሥዕሏ ወደ ቤተ መቅደስ ሥትወሰድ ንቦቹ አጅበዋት የሚሄዱ ሲሆን ስትመለስም አብረዋት ይመለሳሉ፡፡ ንቦቹ ሕዝቡን የማይተናኮሉ እንደመሆናቸው በተንኮል ወይም ለሥርቆት የመጣ ሰው ካለ ግን እየነደፉ እንደሚያባርሩ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ገቢረ ተዓምራት በመነሳት ይገለጻል፡፡

 

ወይኑትን የሚጠብቁ ከንቦቹ በተጨማሪ ነብሮችም በሕንፃው ጣሪያ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀን እዚያው ተኝተው የሚውሉ ሲሆን ምሽት ላይ ምግብ ፍለጋ እንደሚወጡ ይነገራል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ በጎች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ከገቡ ከነብሮቹ ጋር እንደሚጫወቱና እንደማይተናኮሏቸው የዓይን እማኞች ያስረዳሉ፡፡

 

የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ወታደር ሥዕለ ሉቃስ /ወይኑትን/ ለመሥረቅ ሞክሮ ንቦቹ ነድፈው እንዳባረሩት፤ እንዲሁም ዐፄ ዮሐንስ ከደርቡሽ ጋር ባደረጉት ጦርነት ሥዕለ ማርያምን /ወይኑት/ ይዘው ለመዝመት ባደረጉት ጥረት ንቦቹ ወታደሮቻቸውን- በመንደፍ አስጥለዋታል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ የተረዱት ዐፄ ዮሐንስ ሥዕሏን ወደነበረችበት መልሰው እንደዘመቱ የቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ መዝገብ ያስረዳል፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የደብረ ወርቅ ማርያም ገዳምን ለመዝረፍ ዕቃ ቤቱን ሰብረው ለመግባት ያደረጉት ጥረት እንዳይሳካ በማድረግ ጠባቂ ንቦቹ ወታደሮቹን በመንደፍ እንዳባረሯቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

 

ይቆየን