‹‹በቸልተኝነት እና በግዴለሽነት ፈጣሪን አትርሱ!›› ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ

እግዚአብሔር አምላክ ሰዎችን በአምሳሉ መፍጠሩ እርሱን በመዋዕለ ዘመናቸው እንዲፈልጉት፣ እንዲያውቁትና እንዲወዱት ለማድረግ ነው፡፡ እርሱም ስለሚወዳቸው እነርሱን ይፈልጋቸዋል፤ ሁልጊዜም ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጠራቸዋል፡፡ ‹‹በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል›› እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፥፫)

በእግዚአብሔር መንገድ ስንጓዝም ሁሉም ነገር በምክንያት እንደሆነ በማመንና በመረዳት በየትኛውም ጊዜ ቸል ከማለት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሀልዎተ እግዚአብሔር ፈጣሪያችንን እንድናውቅ የሚረዳን በመሆኑ ስለ ባሕርዩ ማወቅና አለብን፡፡ አለበለዚያ ግን ከሕይወት እና ከእውነተኛው መንገድ እንወጣለን፡፡ እግዚአብሔር የጊዜን ስጦታ ለሰዎች በሙሉ የሰጠን እንድንጸልይ፣ እንድንጾም እንዲሁም በጎ ምግባር እንድንፈጽም ነው፡፡ እነዚህን ሠናይ ተግባራት ከመፈጸም ቸል ካልን ከአምላካችን እግዚአብሔር ከመራቃችን በተጨማሪም በመጥፊያው ጎዳና የመጓዛችን ምልክት ነው፡፡

ሰው በተፈጥሮው ደስታን ለማግኘት ይጥራል፤ ያንንም በየትኛው መንገድ ሊያገኝ እንደሚችል ያምናል፡፡ ሆኖም ግን ደስታ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ በመጽሐፋቸው ስለዚህ ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹ሰው እውነትና ደስታውን ሊያገኝ የሚችለው ወደ እግዚአብሔር በመድረስ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሰው ለሕይወቱ የሚያስፈልገው ሁሉ እንደሚሟላለት ያምናል፡፡ ስለሆነም በሙሉ ልቡናውና ሕሊናው እርሱ የሚገኝበትን መንገድ ይመራመራል፡፡›› (የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም)

ከአምላካችን ጋር ለመኖር ክርስቲያናዊ ምግባርን መፈጸም ይጠበቅብናል፤ ሆኖም ግድ የለሽ ሆነን ወይንም ለመንፈሳዊ ፍላጎት ካለመነሣሣት የተነሣ ለጥፋትና ኃጢአት ተጋላጭ ስለምንሆን በችግርና መከራ ጊዜም ሆነ ፈተና ሲበዛብን መቋቋም እና ማለፍ አይቻለንም፡፡ ከዚያም ባሻገር እኩይ ተግባራትን በመልመድ፣ በትዕቢትና በትምክህተኝነት በመጠመድ ሙሉ ለሙሉ ሃይማኖታችንን ትተን ለባዕድ መገዛት እንጀምራለን፡፡

ስለዚህም ‹‹ሰው የግል ነፃነቱን በትክክል በአግባቡ ባለመጠቀሙ የተነሣና በሌሎችም ችግሮችና ተጽእኖ ምክንያት እግዚአብሔርን ከመፈለግ ሊቆጠብ ይችላል፤ ከቸልተኝነቱና ከግዴለሽነቱ ብዛት የተነሣ ፈጣሪውን ወደ መርሳት ይደርሳል፡፡ እንዲያውም ፈጽሞ አምላኩን የዘነጋበትና የተወበት ጊዜም እንዳለ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ዛሬም በትውልዳችን በሰፊው የምናየው ሐቅ ነው›› ሲሉ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ አስረድተዋል፡፡

ቸልተኝነትና ግዴለሽነት በዚህ ትውልድ ከመንጸባረቁም ባሻገር ሰዎች ፈጣሪን ረስተውና ሃይማታቸውን ትተው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎችም የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰሙም ሆነ ምንባባትን ሲያነቡ በግዴለሽነትና ቸል ብሎ በማለፍ ሌሎች ነገሮች ላይ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ምድራዊ ሕይወታቸው ላይ ብቻ በማተኮር ለጥቅም በመገዛትና ጊዜያዊ ደስታን ለማግኘት ሲሉም መንፈሳዊነትን ንቀው ዓለማዊ ሕይወት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የመጠበቅ ቸልተኝነት

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ‹‹ነገር ግን ሁሉን በአግባቡና በሥርዓት አድርጉ›› በማለት ሁሉም በሥርዓት ይሆን ዘንድ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ አገልግሎቶች በሙሉ ወጥና አንድ ዓይነት በሆነ መልኩ እንዲፈጸሙ ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት መገለጫ ነው፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ቅዳሴ፣ ስግደት፣ ጥምቀት፣ ቁርባን፣ እና ሌሎች ክርስቲያዊ ምግባሮች በማመን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆኑ የአፈጻጸምና አተገባበር መንገድ (ሥርዓት) ያስፈልጋቸዋል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ዝርዝር አፈጻጸም በሥርዓት ውስጥ ይካተታል፡፡ በተጨማሪም የአፈጻጸሙ ሥርዓት ያለንን መሠረተ እምነት የምንገልጽበትና የምናንጸባርቅበት ነው፡፡ (፩ቆሮ. ፲፬፥፵)

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመሠረተ እምነት (ዶግማ) የምናምንባቸውን በተግባር የምንገልጽበትና ገቢራዊ የምናደርግበት መንገድ ስለሆነ ሥርዓቱ ሲሠራና ሲፈጸም ሃይማኖታዊ አንድምታና ነጸብራቅ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህም የሕይወታችን አካል መሆናቸውን ተረድተን ያለቸልታ ዘወትር ልንተገብራቸው ያስፈልጋል፡፡ (ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት)

የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የመጠበቅ ግዴለሽነት

ለማንኛውም ነገር ግድ ማጣት የፍላጎት ማነስን ወይንም ጨርሶ ፍላጎት ማጣትን ያመለክታል፡፡ ሰዎች በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ለመኖር እንዲሁም ክርስቲያናዊ ምግባርን ለመፈጸም ፍላጎት ካጡ ከእግዚአብሔር የራቁ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ለመጸለይ ወይንም ለመጾም፣ በበዓላት ወይንም በሰንበታት እና ሰርክ ጉባኤያት ላይ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በጸሎት፣ በቅዳሴና በዝማሬ ለመሳተፍ ፍላጎት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን ክርስቲያናዊ ምግባር በቸልታም ሆነ በግዴለሽነት መተግበር ካቆምን ወይንም አለማዘውተር ወደ ጥፋት ይመራልና እናስተውል! ሥራ ቢበዛብንም ሆነ ችግሮች ቢደራረቡብን እንኳን የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማትና ከማንበብ ልንገታ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ሥራችንን የሚባርክልንም ሆነ ችግራችንን የሚፈታልን አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ ከእርሱ ፈቃድ ውጪ የሆነ አንዳች ነገር የለምና ሁላችንም እርሱ የፈቀደውን ሕይወት ልንኖር ይገባል፡፡

ስለዚህም ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ እንዳሉት ‹‹እንግዲህ ክርስቲያኖች ሁሉ የምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ማለት የመዳን ጸጋ ትምህርት መሆኑን በእምነት ተቀብለው በክርስያናዊ ሕይወታቸው በተግባር መግለጽ ይኖርባቸዋል፡፡፡ አለበለዚያ ግን እንደ ንኡሰ ክርስቲያን ወይም ገና የክርስትናን ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ እንዳልተቀበሉ ወገኖች ይቆጠራሉ፡፡ ስለዚህ በአለማወቅ ሆነ በቸልተኝነት ወይንም በሌላ ምክንያት የሩቅ ተመልካች የሆኑትን ምእመናን በትምህርተ ወንጌል ማቅረብ፣ እምነታቸውንም ማጽናትና እንደ እግዚአብሔር ልጆች ሰማያዊ አባታቸው በምሥጢረ ጥበቡ ያዘጋጀላቸውን ጸጋ በምስጋና እንዲቀበሉ ማስተማርና መምከር የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡››

እግዚአብሔር አምላክ ቸልተኝነትና ግዴለሽነትን አስወግደን በትጋትና በጽናት መንፈሳዊ ሕይወትን እንድንኖር በቸርነቱ ይርዳን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም፤ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ፣ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት