በተሰደብክ ጊዜ

ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

ቅዱስ ዳዊት በወታደሮቹ ተከብቦ ብራቂም ወደ ተባለ ስፍራ በመጣ ጊዜ፤ ከእርሱ አስቀድሞ ንጉሥ የነበረው የሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው በታላቅ ቁጣ ወደ እርሱ መጣ፡፡ በንጉሡ ሠራዊትና በዚህ እንግዳ ሰው መካከል ታላቅ ወንዝ ነበረ፡፡

ይህ ሳሚ የተባለ ሰው ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ድንጋይ ይወረውርና ትቢያ ይበትን ነበር፡፡ ይህንን ተቃውሞ በሚያሰማበት ወቅት አንደበቱ አላረፈም ነበር፡፡ ይህ ሳሚ በቤተ ክርስቲያናችን የጸሎት መጻሕፍት ላይ በበርካታ ስፍራዎች በተራጋሚነቱ የሚወሳ ሲሆን በቅኔም ተሳዳቢ ሰውን ወክሎ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሠራዊት ተከብቦ ያለውን ንጉሥ ዳዊትን ከፍ ዝቅ አድርጎ እየተሳደበና እየተራገመ ነበር፡፡ ‹‹ውጣ! አንተ የደም ሰው ምናምንቴ ሂድ! በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ እነሆም አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል!›› እያለ የስድብ ናዳ አወረደበት፡፡

እርግጥ ነው ዳዊት በሳኦል ፈንታ ነግሧል፤ ይሁንና የነገሠው ተራጋሚው ሰው እንደሚለው በጉልበቱና በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ተመርጦ ነው፡፡ በዚያም ላይ ሳኦልን ሊገድል የሚችልበትን አጋጣሚ ‹እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣም› ብሎ አሳለፈው እንጂ በሳኦል ቤት ላይ ደመኛ የሚያሰኝ በደልን አልፈጸመም ነበር፡፡ ከብዙ የሕይወት ውጣ ውረዱ ላይ የገዛ ልጁ አቤሴሎም ባመፀበትና ቀን ጎድሎበት በተከፋበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ስድብና ንቀት ከአንድ ተራ ሰው መቀበል ለንጉሡ ለዳዊት በእርግጥ መራራ ነበር፡፡ ይሁንና ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፤ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው፡፡ ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች›› ብሎ እንደዘመረው ታግሦ ዝም አለ፡፡ (መዝ.88÷22) ስለተሰደበው ስድብም ክፉም በጎም መልስ አልመለሰም፡፡

 

የንጉሣቸው በአንድ ተራ ሰው መሰደብና መንቋሸሽ ያንገበገባቸው ወታደሮቹ ግን ዝም ሊሉ አልቻሉም፡፡ ከወታደሮቹ መካከል የጺሩያ ልጅ አቢሳ በቁጣ ‹‹ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሻገርና ራሱን ልቊረጠው›› ብሎ በቁጭት ጠየቀ፡፡ ይህን የሎሌውን ለጌታው መቅናት ያየው ንጉሥ ዳዊት ይህንን ወታደር እሺ ብሎ አላሰናበተውም ወይም ስለ ተቆርቋሪነቱ አላመሰገነውም፤ ተቆጣው እንጂ፡፡ ‹‹እናንተ የጺሩያ ልጆች፤ ከእናንተ ጋር ምን (ጠብ) አለኝ? እግዚአብሔር “ዳዊትን ስደበው!” ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ፤ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ የሚለው ማን ነው?›› አለ፡፡

 

በቅዱስ መጽሐፍ ስድብ ፈጽሞ የተከለከለ የአንደበት ኃጢአት ነው፡፡ የሚሳደብም ሰው ንስሓ እስካልገባ ድረስ ጽኑዕ ፍርድ እንደሚጠብቀው በግልጥ ተነግሯል፡፡ ታዲያ ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር “ዳዊትን ስደበው!” ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ›› ሲል ምን ማለቱ ነው? ተሳዳቢ ይልካልን? የሚል ጥያቄ መነሣቱ የግድ ነው፡፡ ስድብን የሚቃወምና በተሳዳቢዎች ላይ የሚፈርድ እግዚአብሔር አንድ ሰው ሌላውን እንዲሳደብ ፈልጎ ‹እገሌን ስደበው› ብሎ አይልክም፡፡ በእርግጥም እንዲህ ከሆነ ይህ ሰው ምንም አላጠፋም፤ እንዲያውም የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ ቅዱስ ዳዊት ‹ዳዊትን ስደበው ብሎ እግዚአብሔር አዝዞታል› ሲል ምን ማለቱ ነው?

 

እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ እምነታቸውንም ለመፈተን ሲል በርካታ መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ የተናጋሪዎቹን ነጻ ፈቃድ ሳይነካ እንደገዛ ፈቃዳቸው የሚናገሩትን ኃይለ ቃል በመጠቀም በመልካም ሰዎች ብቻ ሳይሆን፤ በክፉ ሰዎችም ንግግር ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ ንጉሥ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን አታለልሁ ብሎ ‹‹ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ ባገኛችሁትም ጊዜ መጥቼ እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ›› ብሎ ነበር፡፡ ይሁንና እግዚአብሔር ይህንን የሄሮድስ የሸፍጥ ንግግር የሰብአ ሰገልን እምነት ለማጽናት ተጠቅሞበታል፡፡ ምክንያቱም ሰብአ ሰገል ‹ልስገድለት› ማለቱን ሲሰሙ ለካ የሀገሩም ንጉሥ ያምንበታል ብለው እምነታቸው ጸንቶአልና ነው፡፡ የጌራ ልጅ ሳሚንም እግዚአብሔር ሒድ ተሳደብ ብሎ ባይልከውም እንደ ዳዊት ላለ መንፈሳዊ ሰው ግን ራሱን እንዲመረምር የተላከለት  ስጦታ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሳሚን የግልፍተኛነት ደካማ ጎን ተጠቅሞ ባሪያው ዳዊትን ገስጾታል፡፡

 

ንጉሥ ዳዊት በወታደሮች እና በሕዝብ ተከብቦ ያለ ኃያል ንጉሥ ሆኖ ሳለ የዚህን ተራ ሰው ስድብ ታግሦ ከመቀበልም ባሻገር ለሌላ ዓላማ ተጠቀመበት፡፡ ስድቦቹና እርግማኖቹንም እንደፍቱን መድኃኒት የኃጢአት ቍስሉን የሚሽሩ እንዲሆኑለትና ከእግዚአብሔር ምሕረት መቀበያ እንዲሆኑለት ተመኘ፡፡ ‹‹ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል›› ብሎ በተስፋ ተናገረ፡፡

ይህን ደገኛ ንጉሥ ስድብን እንዲታገስ ምክንያት የሆኑት ነገሮችም አሉ፡፡ እርግጥ በሳኦል ቤት ላይ ተሳዳቢው ሳሚ እንዳለው ያለ ግፍ አልፈጸመም ይሁንና ሚስቱን ቀምቶ በግፍ ያስገደለው የኦርዮ ደም በእጁ አለ፡፡ ስለዚህ የሳሚን እርግማን ምክንያታዊ ባይሆንም ‹የደም ሰው› አስብሎ የሚያስጠራ በደል ሠርቶ ያውቃልና ለዚያ በደሉ ሥርየት እንዲሆነው እግዚአብሔር ይህንን ቅጣት እንዲያደርግለት በአኮቴት ተቀበለ፡፡

 

የተራገመውን ሰው ለመግደል ወታደሮቹ በተነሡ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት ማስተዋልና ብስለት በተሞላበት ንግግር ነበር የከለከላቸው፡፡ በሳሚ ስድብና እርግማን ሳይበሳጭ ልጁ አቤሴሎም አሳድዶት እንደወጣ አስቦ፡- ከወገቤ የወጣው ልጄ ነፍሴን ይሻል፤ ይልቁንስ ይህ የብንያም ልጅ እንዴት ነዋ?›› በማለት የአብራኩ ክፋይ ልጁ ሊገድለው ተነሥቶ እያለ የሌላ ሰው ልጅ ሰደበኝ ብሎ ሊቆጣ እንደማይገባው ተናገረ፡፡ ‹‹ተነሣሒት በመሆኗ የምትታወቅ ነፍስ ወዳለችው ወደ ዳዊት ተመልከቱ! እነዚያን ሁሉ መልካም ነገሮች ካደረገ በኋላ ከሀገሩ ከቤቱ ሌላው ቀርቶ ከሕይወቱ እንኳን ስደተኛ ሆኖ እያለ በመከራው ጊዜ የአንድን ተራ ሰው ስድብ ታገሠ፤ መልሶ አለመሳደብ ብቻ ሳይሆን ከወታደሮቹ አንዱ ሊበቀልለት ሲነሣ ከልክሎ “እግዚአብሔር አዝዞታልና ይርገመኝ” አለ፡፡›› በማለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህን የዳዊት ትዕግሥት ያደንቃል፡፡

 

ሰላም በሰፈነበት ወቅት በሚመስልህ በሚያክልህ አቻህ መነቀፍና መሰደብ ያን ያህል አይከብድህ ይሆናል፤ የሀገር መሪ ሆነህ በተራ ሰው በአደባባይ መሰደብ ግን ለመታገስ የሚከብድህ ነው፡፡ በተለይም በዙፋን ላይ ላለ ንጉሥ ከእርሱ ቀድሞ በነገሠው ንጉሥ ዘመዶች በአደባባይ መተቸት እጅግ የሚፈታተን ጉዳይ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ክፉ ቀን በገጠመው፣ የገዛ ልጁ ዐምፆበት በሚንከራተትበትና ሆድ በባሰው ሰዓት እንዲህ ዓይነቱን እርግማን መስማት የሚቋቋመው ጉዳይ አልነበረም፡፡

 

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ንጉሥ ዳዊት ተሳዳቢውን ሳሚን ቢገድለው ኖሮ ለተሳዳቢው የሚያዝንለትም ሆነ በንጉሡ ላይ የሚፈርድበት ሰው አይኖርም ነበር፡፡ ‹እንደተራ ሰው ከፍ ዝቅ ሲያደርገው አቧራ ሲበትንበት ምን ያድርግ፤ ቀድሞ ነገር ንጉሥን በሠራዊቱ ፊት እንዲህ መዳፈር ይገባ ነበር?› እያለ የየራሱን ማስተባበያ ይሰጣል እንጂ ማንም ንጉሡን አይኮንነውም ነበር፡፡ በዚያ ላይ እግዚአብሔር የቀባውን ንጉሥ ተሳደበ የተባለ ሰው ደግሞ ሞት ቢፈረድበት ሁሉም የሚስማማበት ዘመን ነበር፡፡ (1ነገ. 20÷13፤ 2ሳሙ 19÷21)፡፡

 

ንጉሥ ዳዊት ግን ይህንን ሁሉ ትቶ ስድቡን በደስታ ተቀበለ፤ የቀረበበትን ትችት ተገቢ አለመሆኑን ለሌሎች   ለማስረዳት አልሞከረም፡፡ እኔ ሳኦልን ማጥፋት ስችል ዝም አልኩ እንጂ መች አጠቃሁት?፤ የሳኦልን የልጅ ልጅ ሜምፊቦስቴን እንኳን በገበታዬ አቅርቤው አልነበረም? ብሎ ለመናገር አልፈለገም ‹‹እግዚአብሔር አዝዞታልና ይርገመኝ››አለ እንጂ፡፡

ቅዱሳን ስድብን ታግሠዋል

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሲሰድቡን እንመርቃለን ሲያሳድዱን እንታገሣለን ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጕድፍ ሆነናል›› ብሎ እንደተናገረ ስድብን በጸጋ መቀበል የክርስቲያኖች መታወቂያ ነው፡፡ (1ቆሮ. 4÷12) በብዙ ቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ያለአግባብ መሰደብ የተለመደና በደስታ የሚቀበሉት ተግሣጽ ነበር፡፡ ቅዱሳኑ ስድብን በደስታ ይቀበሉ የነበረው ለስድብ የሚያበቃ ጥፋት ስለ ሠሩ አልነበረም፡፡ ያለ ስሙ ስም፣ ያለ ግብሩ ግብር ተሰጥቶት በዕለተ ዓርብ በአደባባይ የተሰደበውና የተተፋበትን አምላካቸውን መድኃኔዓለምን በእምነት እያዩ ‹ከእኔ ትለፍ› ያላትን የመከራ ጽዋዕ በመቅመሳቸው ደስ እየተሰኙ ነበር፡፡ ከሸንጎ ፊት ሲወጡም ጮማ እንደቆረጡ፤ ጠጅ እንደጠጡ ሁሉ ፊታቸው በደስታ በርቶ የወጡት ‹‹ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ›› ነበር፡፡ (ሐዋ 6÷41)

 

በአበው መነኮሳት ታሪክ ስድብና እርግማንን ሳያስተባብሉ በአኮቴት መቀበልን የመረጡ ብዙ ቅዱሳንን እናገኛለን፡፡ በንጽሕናቸው መላእክትን መስለው ይኖሩ የነበሩት ቅዱሳን ከዝሙት ርቀው ሳለ ዘማውያን ሲሏቸው ታግሠዋል፡፡ አባ መቃርዮስ የተባለ አባት ከአንድ ጎልማሳ የጸነሰች ወጣት ከእርሱ ነው የጸነስኩት ብላ በከሰሰችው ጊዜ እኔ አይደለሁም ሳይል ‹‹እየሠራሁ ልርዳ›› ብሎ ተቀብሏል፡፡ እስክትወልድ ድረስ ሰሌን እየሸጠ ሲረዳት ከቆየ በኋላ በምጥዋ ጊዜ ጭንቋ ሲበዛ እውነቱን ተናግራለች፡፡ ቤተሰቦቿ ይቅር በለን ሊሉት በሔዱ ጊዜ በአቱን ለቅቆ ሔዷል፡፡ (ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 27)

 

እንደ አባ መቃርዮስ ያለ ስድብን የታገሠው አባ በጥል እና በጾታ ሴት ሆና ሳለ ሴት መሆኗን ሳያውቁ በሐሰት ድንግል ሴትን አስረግዘሻል ብለው ዕድሜዋን ሙሉ የነቀፏት ቅድስት ዕንባ መሪናም ባልሠሩት መነቀፍን መታገሥ እንደሚገባን የሚያስረዱ እንደ ደመና የከበቡን ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ እውነተኛ ትሑትም ሲሰድቡት የሚታገስ ነው እንጂ ስድብን የሚያስተባብል አይደለም (ማር ይስሐቅ 6)፡፡

ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ !

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና።›› በማለት እንደተናገረ ሲሰድቡት መልሶ መሳደብ የክርስቲያን ተግባር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን ያሰኘን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሲሰድቡት መልሶ    አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤›› እንጂ (1ጴጥ.2÷23 ፣3÷9)፡፡

 

በእውነቱ ክርስቲያኖች እንሰኝ እንጂ ተሰድቦ መታገስ ግን ለብዙዎቻችን የሚዋጥ አይደለም፡፡ ተሰድቦ ዝም ማለት በብዙዎቻችን ትርጓሜ ራስን ማስናቅ፣ ፊት መስጠት፣ ፈሪነት እንጂ ትዕግሥት ተብሎ አይጠራም፡፡ አንዳንድ ዝም ያልንባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም እንኳን በትሕትና ታግሠን አለመሆኑና የዝምታችን ምክንያት ሌላ መሆኑ የመታገሣችንን ደረጃ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ተሰድበን ዝም የምንልባቸው ብዙ ምክንያቶችም አሉ፡-

•    ለተሳዳቢው ቦታ ካለመስጠት ንግግሩን ‹‹እንደ ዘፈን ቆጥሮ›› ‹ያሻውን ይለፍልፍ፣ ምን ያመጣል?› ከሚል ንቀት፤

•    ተሳዳቢው አካል በቀላሉ ልንጋፋው የማንችለው የበላያችን ሆኖ መልስ ብንሰጥ የሚመጣብንን በመፍራት፣

•    በአንደበት መልስ ከመስጠት ይልቅ ሌላ መበቀያ ምቹ መንገድ ለመፈለግ፣

•    በቃል በሚደረግ እሰጥ አገባ የተነሣ በሌሎች ሰዎች ዐይን ትዝብት ውስጥ ላለመውደቅ

በመሳሰሉ ተርታ ምክንያቶች ተሰድበን ልንታገስ እንችላለን፡፡ ይህ ግን ትዕግሥት ሆኖ ዋጋን የሚያሰጥ አይደለም፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ጊዜ ታግሠን ከቆየን በኋላ በአንድ አጋጣሚ ስንጋጭ ታግሠን ያሳለፍናቸውን ስድቦች ሁሉ ካጠራቀምንበት ልባችን አውጥተን ‹‹ታግሼ ነው እንጂ፤ ለእግዚአብሔር ሰጥቼ ነው እንጂ እንዲህ እንዲህ ብለኸኝ/ ብለሽኝ ነበር›› ብለን እናስታውሳቸዋለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት ግን በተግባር ያስተማረን ስድብን መታገስ ብቻ ሳይሆን ይገባኛል ብሎ ማመንንና ከእግዚአብሔር እንደተላከ ተግሣጽ መቀበልን ነው፡፡

 

ውድ ክርስቲያኖች! የጌራ ልጅ ሳሚ ቅዱስ ዳዊትን የሰደበው ስድብ ተገቢ አልነበረም፡፡ እኛን ግን ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚሰድቡንና የማንታገሠው ስድብ አንዳች እውነታንም ያዘለ ነው፡፡ ያለ አንዳች ምክንያትም የሚሰድበን የለም፡፡ ይሁንና ሌላው ቀርቶ ስማችንን የመጥራት ያህል ለእኛ በሚመጥን (በሚገባን) ክፉ ስም ሰዎች ሲጠሩን እንኳን ይበሉኝ ብለን ከመታገስ ይልቅ ለጠብ እንቸኩላለን፡፡ ልሳነ ወርቅ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አንድ ሰው “አንተ አመንዝራ” ብሎ ሲሰድብህ ለምን ትቆጣለህ? በሐሳብህም እንኳን ቢሆን አመንዝረህ አታውቅም? ወይም ደግሞ በክፉ የጎልማስነት ምኞት ዝለህ አታውቅም? ስለዚህ ይህንንም ስድብ ለክፉ ሐሳቦችህ እንደ ቅጣት አድርገህ ልትቆጥረው ይገባሃል፡፡››

 

‹ብልህ ሰው ከስድብ ይማራል› የሚሉት ብሂልም በእርግጥ እዚህ ላይ ሊነገር ይችላል፡፡ ‹ወንበዴ ቀማኛ› ከሚለው ስድብ ጀርባ ‹አትስረቅ› የሚል ምክር አለ፣ ‹ዘማዊ አመንዝራ› ከሚለው ነቀፋ ጀርባ ‹አታመንዝር› የሚለው ተግሣጽ አለና በምን ነቀፈው ነቀፋ መነፅርነት ራሳችንን መመልከት ይገባናል፡፡ ከስድብ ጀርባ ምክርና ተግሣጽ አለ ሲባል ግን ስድቡን ከሚሰማው ሰው አንጻር ነው እንጂ ምክርን ያዘለ ነው እያሉ ሰውን መሳደብ ይገባል ማለት እንዳልሆነ ግልጥ ነው፡፡ ላሳዝነው ብሎ ሥር ገብቶ ቤት መርምሮ ዘር ቆጥሮ መሳደብ በእግዚአብሔር ዘንድ   የሚያስፈርድ ነው፡፡ ‹‹ወዘይፀርፍሂ ላዕለ እኁሁ ፀረፈኬ ላዕለ እግዚአብሔር ልዑል፤ ወንድሙን የሚሰድብ ልዑል እግዚአብሔርን ተሳደበ›› ተብሎ እንደተነገረ ሕንፃን መንቀፍ ሐናፂውን መንቀፍ፣ ሥዕልን መንቀፍ ሠዓሊውን መንቀፍ እንደሆነ ሁሉ፤ ፍጡርን መንቀፍም ፈጣሪን መንቀፍ ነው፡፡ ፈጣሪን መንቀፍ ነው የተባለውም ሰውን የሠራ እግዚአብሔር ስለሆነ አንድም ደግሞ ሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ስለተፈጠረ ነው (ተግሣጽ ቀዳማዊ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡

 

ቅዱስ ዳዊት ‹እግዚአብሔር አዝዞታልና ይርገመኝ!› እንዳለ ሰዎች በክፉ ቃል በተናገሩን ጊዜ ቀንቶብኝ ነው፣ ተመቅኝቶኝ ነው እያሉ ራስን ከመካብ ይልቅ ‹አምላክ በዚህ ሰው አንደበት አድሮ ኃጢአቴን ሊያመለክተኝ ነው› ብሎ በትሕትና ማሰብ ይገባል፡፡ ትሕትና ማለትም ‹‹ራስን መሳደብ ሳይሆን ሌሎች ሲሰድቡን መታገሥ ነው›› ብሏል ቅዱስ ዮሐንስ በተግሣጹ፡፡

 

ተሳዳቢው ሰው የቱንም ያህል ክፉ ቢሆን፣ የምንሰደበው እኛም የቱንም ያህል ንጹሐን ብንሆን መልሶ መሳደብ አይገባም፡፡ ንጉሥ ዳዊት ስለ በደለው በደል ንስሓ የገባ ጻድቅ ቢሆንም፤ የጌራ ልጅ ሳሚም መናገር የማይገባውን የተናገረው ቢሆንም ታግሦታል፡፡ እኛም የሚሰድቡን ሰዎች ምንም ቢከፉ እኛም የቱን ያህል ብንቀደስ ለስድብ አጸፋ መመለስ አይገባንም፡፡ ከላይ ከተነሣንበት ታሪክ አንጻር ሙሉ በሙሉ ሊተረጎም አይገባም እንጂ አሁን ላነሣነው ሐሳብ የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ታሪክ ምሳሌ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ይህ ታላቅ መልአክ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ዲያቢሎስ የድፍረት ቃልን በተናገረው ጊዜ ‹‹እግዚአብሔር ይጣልህ!›› አለው እንጂ የስድብን ቃል ሊናገረው አልደፈረም፡፡ (ዘካ 3÷2፤ ይሁ 1÷9) ከመላእክት ወገን ከቅዱስ ሚካኤል በላይ የከበረ ከዲያብሎስም በላይ የተዋረደ የለም፤ ከነሠራዊቱ ተዋግቶ የጣለውን ውዱቅ መልአክ እንደ ሰው ቢሆን የጥንቱን አንሥቶ ሊያዋርደው ይቻለው ነበር፤ ይሁንና የከበረው ሚካኤል ለተዋረደው ዲያብሎስ እንኳን ክፉ ሊመልስለት አልወደደም፡፡

 

እኛም ምንም ብንከብር የቅዱስ ሚካኤልን ያህል አንከብርም፤ የሚሰድቡን ሰዎችም ምንም ቢከፉ የዲያብሎስን ያህል አይከፉምና ለመሳደብ በመቸኮል ለአንደበታችን አርነት አንስጥ! የሚገባንን ስድብ ስንሰደብ ራሳችንን በስድቡ ውስጥ እንገሥጽ፣ ያለ ጥፋታችን ስንሰደብ ደግሞ ያለ ጥፋቱ የተሰደበ አምላክ ባሪያዎች መሆናችንን እያሰብን ከቅዱስ ዳዊት ጋር ‹‹ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ›› ‹‹የሚሰድቡህ ስድብ በላዬ ወደቀ›› ብለን እናመስግን! (መዝ 88÷9)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡ሐመር ኅዳር 2003 ዓ.ም