ሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት

በሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ጉዳይ ውይይት ተደረገ

በዳዊት ደስታ

መጋቢት 9 ቀን 2005 ዓ.ም.

ሰማዕቱ የአቡነ  ጴጥሮስ ሐውልት

 

የሰማዕቱ የአቡነ  ጴጥሮስ ሐውልት የቴክኒክ ጥናት ኮሚቴ ሐውልቱ ያለምንም ጉዳት እንዴት መነሣት እዳለበት ከባለ ድርሻ  አካላት ጋር ውይይት አደረገ፡፡

 

የቴከኒክ ጥናት ኮሚቴው የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስብሰባ አዳራሽ ለግማሽ ቀን ባካሔደው ውይይት ሐውልቱ ተነሥቶ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ በስፋት መክሯል፡፡

 

ሐውልቱ ከቦታው ተነሥቶ የመንገድ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ እንዴት ወደ ነበረበት መመለስ እነዳለበት ኮሚቴው ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የቴክኒክ  ጥናት ኮሚቴው የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ስንታየሁ አስታውቀዋል፡፡

 

የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት በጊዜያዊነት የሚነሣበት ምክንያት በዐደባባይ ላይ የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ስለሚካሔድ ጉዳት እንዳይደርስበት በሚል እንደሆነ በሐውልቱ  አነሣስ የቴክክ ጥናት ኮሚቴ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ስንታየሁ ስለ አዲስ አበባ ባቡር ፕሮጀክት አሠራር አጠቃላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

 

በውይይቱ መርሐ ግብሩ ላይም ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያው “የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ታሪካዊ ዳራና ሐውልቱ የሚገኝበት ሁኔታ” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ኃይሉ ዘለቀ ናቸው፡፡

 

እንዲሁም የቴክኒክ ጥናት ኮሚቴው ሰብሳቢና ከፍተኛ የማይንቀሳቀስ ቅርስ ጥገና ባለሙያ አቶ በየነ ደሜ “ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አነሣሥ” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

 

በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቲች ከተሳታፊዎቹ የቀረበ ሲሆን ፤ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው የተገኙት መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል “ እስካሁን ተነሥቶ ያልተመለሰ ሐውልት ስላለ ማነው የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልትን በባለቤትነት የሚያስመልሰው ፤ ቤተ ክርስቲያን ለእኒህ ቅዱስ አባት የመጨረሻ ክብር ሰጥታ አክብራለችና ሐውልቱ ሲመለስ እንደቀድሞ ስለመከበሩ ምን ዋስትና አለው ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጠዋል፡፡

 

ሌላው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ጥናት  ምርምር መምህር ዶክተር ሐሰን ሰይድ “ ወደፊት የባቡር ንቅናቄ ስለሚኖር በሐውልቱ ላይ የሚያመጣውን አደጋ ከወዲሁ አብሮ ማጤን ያስፈልጋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

ለተነሡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከጥናት አቅራቢዎቹ  በቂ ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቶባቸዋል፡፡

 

በጊዜያዊነት የሚነሣው የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት የባቡር ሀዲዱ ዝርጋታ ተጠናቆአስኪያልቅ ድረስ በብሔራዊ ሙዚየም እንደሚቀመጥ ተጠቁሟል፡፡ሐውልቱ መቼ እንደሚመለስ ፣ የአወሳሰዱ ሒደትና የሚያስፈልጉ ግብአቶችን እንዲሁም ወጪዎችን በሚመለከት የቅርስ ባለአደራ ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ አስተዳደር እንደሚፈራረሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

በውይይቱ መርሐ ግብር ላይ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት ፣ የቤተ ክርስቲያንና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ተወካዮች፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ተጋባዥ  እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ምንጭ፡-  ስምዐ ጽድቅ  ፳ኛ ዓመት ቁጥር ፲፪  ከመጋቢት ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.