“በምንም አትጨነቁ” (ፊል.፬፥፮)

ታኅሣሥ ፲፫፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ጨለማውን አስወግዶ ብርሃንን የገለጠው፣ ሰውን ለአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ከነበረበት የኃጢአት ባርነት ያወጣው እንዲሁም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሰላምና ነጻነትን ያወጀልን የዓለም መድኃኒት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ስለምንም ነገር መጨነቅ የለብንም፡፡

“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፣ ለሥጋችሁም በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከምግብ አትበልጥምን? ሥጋስ ከልብስ አይበልጥምን? የማይዘሩና የማያጭዱ በጐተራም የማይሰበስቡ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ ሰማያዊ አባታችሁም ይመግባቸዋል፡፡ እናንተ ከእነርሱ እጅግ ትበልጡ የለምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?

ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የምድረ በዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እዩ፤ አይደክሙም፤  አይፈትሉም። ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን፥ ነገም ወደ እሳት ምድጃ የሚጣለውን የምድረ በዳ ሣር እነሆ፥ እንደዚህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተን ሃይማኖት የጎደላችሁ፥ እናንተማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይሹታልና፤ ለእናንተ ግን ሰማያዊ አባታችሁ ይህን ሁሉ እንድትሹ ያውቃል፡፡ እናንተስ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት፣ ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም  ሁሉ ይጨመርላችኋል። ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ ነገ ለራስዋ ታስባለችና፤ ለቀኒቱ ክፋቱ ይበቃታል” እንዲል፤(ማቴ.፮፥፳፭-፴፬)

እንግዲህ ጌታችን ከተናገረው ቃል በመነሣት ጭንቀት ማለት ከመጠን በላይ ማሰብ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ስለኑራችን በምንም ጉዳይ እንዳንጨነቅ ስላስተማረን ስለመብልም ሆነ ስለአልበሳት እንዲሁም መጠላያ ስለመቸገር መጨነቅ ከንቱ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰማይ አባታችን እንኳን በአርአያውና በአምሳሉ ለፈጠረን ለእኛ በሰማይም ይሁን በየብስ ላይ፣ በመሬትም ሆነ በባሕር ውስጥ እንዲሁም በከተማም ወይም በዱር ለሚኖሩ ግዙፋን እንስሳትም ሆነ ለጥቃቅን ነፍሳት ምግብን ያዘጋጃል፤ በጥላ ከለላውም ያኖራቸዋል፡፡

በምድራዊ ሕይወታችን ለሚገጥመን ማንኛውም ችግር ከእግዚአብሔር ዘንድ መፍትሔ ይኖረዋል፡፡ በእርሱ አምነንና ታምነን እስከኖርን ድረስ ከመከራና ከሥቃይ ያወጣናል፡፡ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት በሕይወታቸው ውስጥ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ የሚረዳቸው ቤተሰብም ሆነ ዘመድ ከሌላቸው ደግሞ ችግራቸውን ስለሚያባብሰው ወደከፋ መከራ ውስጥ ሲገቡ ሰምተንም ሆነ ተመልክተን ይሆናል፡፡ ነገር ግን አምላካችን እግዚአብሔር ሰውን የሚፈትነው ለበጎ እንደሆነ በማወቅና በመረዳት የነገን ተስፋ አድርጎ መኖር ይኖርብናል እንጂ ተስፋ መቁርጥ ወይም ማማረር አይገባም፡፡ በተቻለው መጠን ለኑሯችን ተሯሩጠን የዕለት ጉርሻችን መሙላት እንዲሁም ወደ ተሻለ ሕይወት መትጋት ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” ብሎናል፡፡ (፪ተሰ.፫፥፲)

እግዚአብሔር አምላክ ለወፎችንና ለምድር አራዊት መብል ቢያዘጋጅላቸውም እንኳን ምግብ የሚሆናቸውን ነገር ፈልጎ ለማግኘት ሁሉም የየድርሻውን እንደሚወጣ ሁሉ ሰውም መትከል፣ ማረስ፣ መቆፈር፣ ማጨድና፣ መገንባት እንዲሁም መነገድ አለበት፡፡ እነዚህ ሥራዎች በፈጣሪያችን ዘንድ የተፈቀዱ በመሆናቸው ልንተገብራቸው ይገባል፡፡ ሥራችንም እንዲባረክልን በጸሎት መጠየቅ እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ “በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ፤ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ” በማለት ተናግሯል፡፡ (ፊል.፬፥፮)

በሐሳብ መጨነቅ የማይገባን እንደሆነ ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡ ሆኖም ግን ሰዎች ለምድራዊ ሕይወታቸው በተጨነቁ ቁጥር የነፍሳቸውን ዋጋ እንደሚያጡ ጌታችን አስተማሮናል፡፡ በዚህም መሠረት የሥጋችንን ፍላጎት መግታት እንዳለብን ከቅዱስ ቃሉ እንረዳለን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ሕይወትን የሚሰጥ ነው። የምድራዊ ሕይወታችን የተሟላ እንኳን ቢሆን የጎደለንን የነፍስ ስንቅ ዐውቆ የነፍስ ምግብ ሊመግበንና የሕይወት ጽዋ ሊያጠጣን ስለሚሻ ከኃጢአታችን ነጽተን በንስሓ በመመለስ ለሥጋ ወደሙ እንድንበቃ ይፈትነናል፡፡ እዚህ ላይ የጻድቁ ኢዮብን ታሪክ ማንሣት ይገባል፡፡ ኢዮብ ባለጸጋና የእግዚአብሔር ሰው ስለነበር ሰይጣን ቀንቶ ባመጣበት መከራና ሥቃይ አምላክ ፈተነው፡፡

በአንዲት ቀን የኢዮብ ገንዘብ ሁሉ ጠፋ፤ ሥጋው በደዌ ሥጋ ከራሱ ጠጉሩ እስከ እግሩ ጥፍሩ ድረስ ተመታ:: በዚህም በአስጨናቂ ደዌ ውስጥ ኖረ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም በአንድ ጊዜ አጣ፤ ሆኖም ግን ኢዮብ እግዚአብሔርን አመሰገነ እንጂ አንዲት ቃልን እንኳ በፈጠረው እግዚአብሔር ላይ አላጕረመረመም፤ ……::›› (ኢዮብ ፫፥፩)

የነበሩት ከብቶቹ፣ ገንዘቡ፣ ሀብትና ንብረቱ ሁሉ በጠፋ ጊዜ “እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን አለ እንጂ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ (ኢዮብ ፩፥፳፩)

ይህን ሁሉ ፈተና ካለፈ በኋላ ግን እግዚአብሔር በደመና ውስጥ ኢዮብን ተናገረው:: ከዚያ በኋላ ከደዌ ሁሉ ፈወሰው፤ ሀብቱንም ሁሉ ባርኮ ከቀድሞ እጥፍ አደረገለት፤ የተባረኩ ልጆችም ሌሎች ወንዶችና ሴቶችም ሰጠው:: ከደዌ ከተፈወሰ በኋላ በሰላምና ፍቅር ከቤተሰቦቹ ጋር ለመቶ አርባ ስምንት ዓመት በበጎ ሽምግልና ኖሮ እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፤ መንግሥተ ሰማያትንም ወረሰ፡፡ (ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት ፪)

ከጻድቁ ኢዮብ በትዕግሥትና በሃይማኖት ጽናት መከራና ችግርን ማለፍ እንደምንችል እንማራለን፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ እጅግ አስከፊ በመሆኑ ከፊታችን የተጋረጠብን ሀገራዊ ችግር ለማለፍ ልንጸና ይገባል፡፡ አልባሌ በሆነ ሰበብ፣ ተራ ወሬና አሉባልታ እርስ በእርስ እንድንጨካከንና እንድንጣላ እንዲሁም እንድንጋደል የሚያደረገን ነገር በራሳችን ፍቃድ ለሥጋ ፍላጎታችን መገዛታችን ነው፡፡ በጥቅምና በገንዘብ ፍቅር ተነድፈን በባልንጀሮቻችን ላይ እንድንጨክንና ክፋትም እንድናደርግ ያደረገን ነገር ቢኖር ሥጋዊ ምኞታችንን ለማሳካት ያለን ብርቱ ስሜት እንደሆነ በግልጽ የተመለከትነው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ጊዜ በዘር፣ በባህልና በሃይማኖት የተከፋፈልንበት ምክንያት እንዲሁም ለዕለት እንጀራችን የሚሆኑን የምግበ ሥጋ አቅርቦቶች ዋጋ መናር “ምን ዓይነት አስከፊ ጊዜ ላይ ደረስን? እስክንል ያደረስንና ለጭንቀት የዳረገን እርስ በእርሳችን በመጨካከናችን ነው፡፡ በንግድ ሀብት ለማካበትም ሆነ በምድራዊ ሕይወት ለመክበር ሌት ከቀን የሚዳክሩ አንዳንድ እንስሳዊ ባሕርይ የተላበሱ ግለሰቦች ደግሞ ለግል ጥቅማቸው ሰዎችን እስከመግደል ይደርሳሉ፡፡ ወጥቶ መግባት እንኳን አስቸጋሪ የሆነበት ጊዜ ላይ የደረስነው በራሳችን ክፋትና ኃጢአት በመሆኑ እንዲህ ለመከራና ሥቃይ ስንዳረግ መልሰን አምላክን ማማረር ምን ይባላል?

መለስ ብለን ራሳችን መርምረንና ከስሕተት ጎዳና ተመልሰን ንስሓ ካልገባን መጨረሻችን የሚሆነው እንደ ምዕራባዊያኑ ሰይጣንን በግልጽ ማምለክ ነው፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃናት ላይ ሰዎች በተለይም ወጣቶች የአውሬው አምላኪዎች ወይም ተከታዮች እንደሆኑ በአንደበታቸው እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ካሉበትም የድኅነት አረንቋ ለመላቀቀም  የሰይጣናዊ አምልኮ ድርጅት በማቋቋምና ለአውሬው በመገበር ገንዘብ እየሰበሰቡና የግል ጥቅማቸውን እያሟሉ እንደሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃናት ላይ እየተገለጸ ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን መሰል ወሬዎች በምንሰማበት ጊዜ ስለ እምነታችንና ሃይማኖታችን እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወታችን መቃኘትና ስሕተታችንን ወይም ጥፋታችንን በማወቅ ለኃጢአታችን ሥርየትን እናገኝ ዘንድ አምላካችንን መለመን እንጂ ችግርና መከራ በገጠመን ቊጥር ፈጣሪን ከመጠን ባለፈ ጭንቀት ማማረር ለባሰ ጥፋትና ቅጣት ይዳርገናል፡፡ አምለካችንም መፍትሔ የሚሰጠን ከልብ ተጸጽተን ይቅርታና ምሕረትን ስንማጸን ነው፡፡ በብዙም ቢሆን በጥቂቱ እግዚአብሔርን እንዳስከፋነው በመረዳት ልንለምነው ይገባል፡፡ እርሱ እኛን የሚፈትነን እንድንመለስ በመሆኑ በዚህ በጭንቅ ጊዜ ወደ ፈጣሪያችን አብዝተን ልንለምንና ምሕረትን ልንጠይቅ ይገባናል፡፡ ለበጎ ሰዎች ይህ ጊዜ ሰማዕትነት ሲሆን ለኃጥአን ግን የንስሓ ጥሪ ነው፡፡ የማንሰማ ከሆነ ግን በመቅሠፍቱ ያጠፋናልና ለሆነው ላልሆነው ከመጨነቅ ይልቅ በአምላካችን እግዚአብሔር አምነንና ታምነን ይህን መከራ ጊዜ እንዲያሳልፈን፣ ጭንቀታችን እንዲያስወግድልንና ችግራችንን እንዲፈታልን ለእርሱ አሳልፈን በመስጠት መኖር ያስፈልጋል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱና በምሕረቱ ይጎብኘን፤ ይህን መከራ ጊዜ ያሳልፍልን፤ አሜን!