“በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ” (ትንቢተ ዮናስ ፪፥፫)

በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ይኖር የነበረው ነቢይ ዮናስ አምላኩን ሸሽቶ በመርከብ በተጓዘበት ጊዜ ማዕበል ሲናወጥ መርከበኞችን ወደ ባሕር እንዲጥሉት የጠየቃቸው ጥፋቱን ስላወቀ ነበር፡፡ ነቢዩም አንስተው ወደ ባሕር እንዲከቱት በነገራቸው ጊዜ ሰዎቹ ግራ ተጋቡ፡፡ እጣ ተጣጥለውም በደለኛ የሆነውን ሰው መለየት እንደሚችሉ ተስማሙ፡፡ ዕጣውም በነቢዩ ዮናስ ላይ ወደቀ፤ አንስተውም ባሕር ውስጥ ሲጥሉት ማዕበሉ ጸጥ አለ፡፡

ባሕር ውስጥ እግዚአብሔር ነበርና ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ዮናስም ባሕር ውስጥ ሲገባ ዓሣው ዋጠው፡፡ ነገር ግን አልሞተም፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጠ፤ ከእግዚአብሔር ውጪ አንዳች ነገር እንደሌለ በማወቅና በማመን እንዲህም ብሎ ጸለየ “በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽኩ፤ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ የጩኸቴን ድምፅ ሰማኝ÷ ቃሌንም አዳመጥህ፡፡ ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ÷ ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ፡፡ እኔም ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፤ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህም ደግሞ እመለከታለሁ አልሁ” (ትንቢተ ዮናስ ፪፥፫-፭)

ጩኸት የተባለው ጸሎት ነው፤ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን የኢያሪኮ ሰዎችን ድል ያደረጉት ግንባቸውንም ያፈረሱት በጩኸት ነው፡፡ ጩኸቱ ግን ኡኡታ አልነበረም፤ ጸሎት ነበረ፡፡ ሰዎች በዚህ ምድር ስንኖር ብዙ ችግርና መከራ ያጋጥመናል፡፡ ያን ጊዜ “ችግር ደረሰብን፤ ፈተናችንም በዛ” ብለን የምናማርር ከሆነ ሌላ መከራ እንዲመጣብን ሰበብ ይሆንብናል፡፡ ስለዚህ በመከራ ውስጥ ሆነን ወደ እርሱ ልንጮህ ይገባል፡፡ ዛሬ አምላካችን እኛን “ንስሓ ግቡ ይቅርታ ጠይቁ” እያለን ነው፤ ስለዚህ እኛም በዓለም ላይ የመጣው ይህ ወረርሽኝ ኮሮና በሽታ በኃጢአታችን ብዛት መሆኑን ማወቅና መጸጸት አለብን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ነቢዩ ዮናስን በአዘዘው መሠረት ወደ ነነዌ ሄዶ እንዲሰብክና እንዲያስተምር ቢነግረውም ትእዛዙን አልተቀበም፡፡ ሸሽቶም ወደ ኢዮጴ ቢሄድ በዙሪያ እግዚአብሔር ነበር፤ መርከቡ ውስጥ ቢገባ እግዚአብሔር አለ፤ በባሕርም ሲጣል እግዚአብሔር ባሕር ውስጥ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር አለ፤ አሜሪካ እግዚአብሔር አለ፤ ጃፓን እግዚአብሔር አለ፤ ደቡብ አፍሪካ እግዚአብሔር አለ፡ጥልቅ ውስጥ እግዚአብሔር አለ፤ በሰማይ እግዚአብሔር አለ፡፡ ረገጥናት በተባለችው በማርስ ላይ እግዚአብሔር አለ፤ በቬነስ እግዚአብሔር አለ፤ በፕሉቶ  እግዚአብሔር፡፡ ገና ዓለም ባልደረሰበት በነፍስ ዓለም እግዚአብሔር አለ፡፡ በእሳት ዓለም እግዚአብሔር አለ፡ከዚህ ምድር በታች ሌላ ዓለም አለ፡፡ በሁሉም ስፋራ እግዚአብሔር አለ፡፡

ሰው ኃጢአት በሚሠራ ጊዜ ሰውን እንጂ እግዚአብሔርን አይፈራም፤ ነቢዩ ዳዊት ሰውን ለማታለል በሞከረ ጊዜ እግዚአብሔርን ረሳ፤ ብዙ ሚስቶች እያሉትም የኦርዮንን ሚስት ቤርሳቤህ ጋር ወሰደ፡፡ ኦርዮንንም ጠርቶ “ወደ ቤትህ ሂድ÷ እግርህንም ታጠብ” አለው፤ ኦርዮን ግን ከበረንዳው ላይ ተኛ፤ ከዚያም ነገረ ሠሪዎች ወደ ዳዊት መጥተው ኦርዮን ወደ ቤቱ አልገባም ብለው ነገሩት፡፡ ንፉሥ ዳዊትም ስለምን ቤቱ ገብቶ እንዳልተኛ ሲጠይቀው “ታቦቱና እስራኤል ይሁዳም የጌታዬም ባሪያዎችም በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል፤ እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤት እሄዳለሁን? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን አላደርግም አለው፡፡”  ንጉሡም ከእርሱ ጋር እንዲተኛና ወቅቱ የጦርነት ስለነበር በጥዋት ወደ ጦር ሜዳ እንደሚልከው ነገረው፤ “በፊቱም በላና ጠጣ÷ አሰከረውም፤ ነገር ግን በመሸ ጊዜ ወጥቶ ከጌታው ኗሪያዎች ጋር በምንጣፍ ላይ ተኛ÷ወደ ቤቱም አልወረደም፡፡” (፪ኛ ሳሙኤል. ፲፩፥፲፩፤፲፫)

ዳዊትም ለጦር አዛዡ ደብዳቤ ጻፈ፤ እንዲህም ይል ነበር፤ ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ ኦርዮን አቁሙት፤ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ፤” በዚህም ምክንያት እናም ኦርዮን በጦር ሜዳ ተወግቶ ሞተ፡፡ ዛሬም በአንድ ቀን ውስጥ በሐሜት በብዙ ሰዎችን የሚገድሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ (፪ኛ ሳሙኤል. ፲፩፥ ፲፭)

ሁሉንም የሚያይ እግዚአብሔር ነቢዩ ናታንን ላከው፤ ወደ ንጉሥ ዳዊትም በደረሰ ጊዜ በዙፋኑ ላይ ምንም እንዳልሠራ ሰው ተቀምጦ አገኘው፡፡ ናታንም እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ በአንድ ከተማ ውስጥ አንድ ብዙ በጎች ያሉት ባለጸጋ ነበር፡፡ በዚሁ ከተማም ምስኪን ሰው ነበር፡፡ ከሚበላው እያበላ ከሚጠጣው እያጠጣ በብብቱ አቅፎ የሚያስተኛው አንድ በግም ነበረው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ወደ በባለጸጋው ቤት እንግዳ መጣ፤ እርሱም ከብዙ በጎቹ አንዱን አርዶ እንዳያበላው የበጎቹ ቊጥር ሊጎድልበት ስለሆነ ወደ ምስኪኑ ቤት በመሄድ ያለውን አንዲት በግ ነጠቀው፡፡ ቤቱ ወስዶም ለእንግዳውም አረደለት” ብሎ ናታን ለንጉሥ ዳዊት ነገረው፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ፤ እንዲህም አለ  “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ይኼ ሰው በእኔ ግዛት ውስጥ ካለ እርሱ በሰውነቱ ላይ አያድርም፤ ለእርሱ ሞት ይገባዋል” አለው፤ በሌላ ሰው ላይ መፍረድ ቀላል ነውና፡፡ (፪ኛ ሳሙኤል. ፲፪፥ ፩-፭)

ነቢዩ ናታን ግን ከእግዚአብሔር የተላከው ንጉሥ ዳዊትን እንዲገሥጸው ስለነበር የነገረው ታሪክም ስለራሱ ነው፡፡ “ኦ ንጉሥ ፈታሕከ በርእስከ፤ ንጉሥ ሆይ በራስህ ላይ ፈርደሀል፤ ያ ይሙት ያልከው ሰው አንተ ነህ፤ ባለጸጋውም አንተ ነህ፤ ብዙ በጎች የተባሉት በቤትህ ያሉት ብዙ ሚስቶችህ ናቸው፤ ሚስቶችህን አስቀምጠህ የምስኪኑን የኦርዮን ሚስት ቤርሳቤህን ነጠቅህ፡፡  ባሏንም በማስገደል ኃጢአት ሠርተሀል” አለው፡፡ (፪ኛ ሳሙኤል. ፲፪፥ ፯-፲፪)

ዝሙት የሚፈታተነን በሽምግልና ሳይሆን በወጣትነት ጊዜ እያስጨነቀ ወደ እሳት ውስጥ ሊከተን የሚፈልግ ጾር በመሆኑ ልንጠነቀቅ ይገባል፤ ራሳቸውን የሚገዙና ኅሊና ያላቸው ሰዎች ግን እንዲህ ባለው ፈተና አይወድቁም፤ እግዚአብሔርንም በመፍራታቸው ዝሙትን አይፈጽሙም፡፡ ንጉሥ ዳዊትም የነቢዩ ናታንን ቃል በሰማ ጊዜ አልቅሶ መሬት ላይ ወደቀ፤ “እግዚአብሔርን በድያለሁ?” አለው፡፡ ናታንም እግዚአብሔር አምላክ በሞት እንደማይቀጣው፤ ነገር ግን በሠራው ኃጢአት የተፀነሰው ልጅ እንደሚቀሠፍ ነገረው፤ ዳዊትም በጸሎትና በጾም ምሕረትን ተማጸነ፤  እግዚአብሔርም የደኅንነት አምላክ ነውና ይቅር አለው፡፡

በመጀመሪያ ራሳችን “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ኃጢአተኛ ነኝ፤” ብለን አምነን መጸጸት አለብን፤ ጸጸትም ወደ ንስሓ ይመራናል፡፡ እግዚአብሔር ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና ውስጣችንን ከክፋት ሳናነጻ በሐሰተኛ አንደበት በንጸልይና ምሕረትን ብንለመን ልመናችንን አይቀበለንም፤ ሁሌም እርሱን በመፍራት መኖር እንዳለብን ቃሉ ይገልጻል፤ “ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር” እንደተባለው እግዚአብሔርን አምላክን በንጹሕ ልቡና ልንማጸን ይገባል፡፡ (መጽሐፈ ምሳሌ ፳፫፥፲፯)