hawassakidusgebriel.jpg

በሐዋሳ ያለው ችግር እንደ ቀጠለ ነው፡፡

ሰኞ፣ የካቲት 14/2003 ዓ.ም                                                                    በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
 
hawassakidusgebriel.jpgትናንት እሑድ የካቲት 13/2003 ዓ.ም በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከቅዳሴ በኋላ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሊሰጥ የነበረው ትምህርተ ወንጌል በተወሰኑ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች አመጽ ተስተጓጉሏል፡፡ ከሥፍራው የደረሰንን ሪፖርት እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
 
ብፁዕነታቸው ጸሎተ ቅዳሴውን ከመሩ በኋላ ለማስተማር ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥተው ከካህናቱ ጋር ተቀመጡ፡፡ ወጣቶቹም የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለብሰው ዝማሬ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ በተለምዶ ሁለት መዝሙር ቀርቦ ስብከተ ወንጌል የሚጀመር ቢሆንም ትናንት ግን “እመቤቴ ማርያም እለምንሻለሁ” እና “የኢቲሳ አንበሳ ተክልዬ ተነሳ” የሚሉ መዝሙሮች ከተዘመሩ በኋላም ዝማሬው አልቆመም፡፡ 
 
ወጣቶቹ ከኪሳቸው ይዘውት የነበረውን ጥቁር ጨርቅ አውጥተው እያውለበለቡ “መዘመራቸውን” ቀጠሉ፡፡ ይህንን የተመለከቱት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ትምህርት መስጠቱን ትተው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት ቅድስቱ ላይ በመሆን የማሰናበቻ ጸሎቱን አድርሰዋል፡፡

ከጸሎቱ በኋላ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “ጥቂት ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን ሰላም አያደፈርሱም፣ …. የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ተከብሮ ይኖራል፣ … ከአሁን በኋላ እንድንጨክን እያደረጋችሁን ነው…” በማለት ጠንከር ያለ ወቀሳና ተግሣጽ አስተላልፈዋል፡፡ ምእመናን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም እንዲጸልዩም በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡ ለምነዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ይህንን መልእክት ሲያስተላልፉ ወጣቶቹ በከፍተኛ ድምፅ እየዘመሩና ከበሮ እየመቱ እንዳይሰሙ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡

እነዚሁ ወጣቶች እና ሌሎች ከ60 – 100 ያህል የሚሆኑ “ምእመናን” ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከቅዳሴ በኋላ ወደሚወጡበት የቤተ ክርስቲያኑ የምሥራቅ በር ጥቁር ጨርቃቸውን እያውለበለቡና “አንፈራም አንሰጋም…” እያሉ እየዘመሩ በመሄዳቸው በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ የነበሩት ምእመናን ግልብጥ ብለው ወደዚያው በመሄድ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን አጅበው እስከ መንበረ ጵጵስናቸው /መኖሪያቸው/ አድርሰዋቸዋል፡፡ ሰዎቹ ለምን ዓላማ ጥቁር ጨርቅ እያውለበለቡና እንደዚያ እያሉ እየዘመሩ ወደ ብፁዕነታቸው እንደሄዱ ግልጽ ባይሆንም በኋላ ተመልሰው ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ገብተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን አጅበው ወደ ቤታቸው ያደረሱት ምእመናን “አይዝዎት አባታችን፣  ሰላማችንን እያጠፋውና እየበጠበጠን ያለው ዲያብሎስ በመሆኑ ልንታገሥ ይገባል፣ እኛም ከጎንዎት ነን…” በማለት ብፁዕነታቸውን አጽናንተዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም ለዚህ ሁሉ ዋናው መፍትሔ ጸሎት በመሆኑ ሁሉም ስለቤተ ክርስቲያን ሰላም በመጸለይ እንዲተጋ በድጋሚ በማሳሰብ ሕዝቡን በቡራኬ አሰናብተዋል፡፡

ትናንት ይህንን ሁከት ያደረሱት ወጣቶች በቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት በተፈጸመው ቃለ ዐዋዲውን ያልጠበቀ ምርጫ በተመረጠው የሰንበት ትምህርት ቤት አመራር የሚመሩ ሲሆኑ፣ ይህ ሁኔታ ከመፈጸሙ ከአንድ ቀን በፊትም /ቅዳሜ የካቲት 12/2003 ዓ.ም/  በሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽ ተገኝተው እንደተወያዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ በፊት ብፁዕነታቸው ወደ ሀገረ ስብከቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሄዱ በተመሳሳይ መልኩ ጥቁር ጨርቅ እያውለበለቡ እንደተቀበሏቸውም ይታወሳል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውንና የታቀደና የተቀናጀ የሚመስለውን እንቅስቃሴ በማየት፥ እነዚህ አካላት ሆን ብለው የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ የማጉደፍና አገልግሎቷን የማደናቀፍ ብሎም ምእመናንን አስመርሮ ከቤተ  ክርስቲያን የማስወጣት ሥውር ተልእኮ ባላቸው የውስጥ አርበኞች የሚነዱ እንዳይሆኑ ስጋት እንዳላቸው የሚገልጹ ምዕመናንንም ቁጥር በርካታ ነው፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ሁከት መፈጠር እንደሌለበትና ተቃውሞም ቢኖር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ መቅረብ እንዳለበት ያሳሰቡ መሆኑ ይታወሳል፡፡