‹‹በላይ ያለውን ሹ›› (ቈላ. ፫፥፩)

ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

መልአከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፈንታሁን

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንደተናገረው ‹‹ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ በአለበት በላይ ያለውን ሹ፡፡ የላይኛውን አስቡ፤ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና፡፡ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ ያን ጊዜም ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ፡፡›› (ቈላ. ፫፥፩-፬)

ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር በዕለተ ዐርብ ሞቶ በሰንበተ እሑድ የተነሣ ማንም የለም፡፡ እርሱም ዐርጎ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጧልና እኛንም አምላክ በቀኙ ያኖረን ዘንድ በላይ ያለውን (ጌታችንን) እንድንሻ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ነግሮናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ እንደሚገለጥ፣ ያንጊዜም እኛ በታላቅ ክብር ከእርሱ ጋር በቀኝ እንደምንቀመጥ አስረድቶናል፡፡ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሣ ሰዎች ደግሞ ከኃጢአትና ከክሕደት ሲመለሱ በትንሣኤ ልቡና ተነሡ ይባላል፤ በኃጢአት የሚኖር ሰው የሞተ፣ ንስሓ የገባ ሰው ግን የተነሣ ነውና፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋል›› ብሎ እንዳስተማረው ኃጢአተኛ ሰው እንደሞተ ሰው በመሆኑ ከሞት ወደ ሕይወት ለመሸጋገር በምድር ላይ እስካለን ድረስ በንስሓ መመለስ ይገባል፡፡  ከሞትን በኋላ የሚጠብቀን ፍርድ እንጂ ሌላ ዕድል ፈንታ የለምና፡፡ በሥጋ ከሞትን በኋላ ማስነሣት የሚቻለው ደግሞ አምላካችን ሲሆን ያም ለፍርድ በትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፤ በኃጢአት ከወደቀበትና ከሞትንበት መነሣት ግን የእኛ ድርሻ ነው፡፡

የቈላስይስ ሰዎች ከአሕዛብ ይኖሩ ነበሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ወንጌል የቅዱስ ጳውሎስ አገልጋይ የሆነው ኤጳፍራስ ካስተማራቸውም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከሰማይ ወርዶ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በተወለደ በ፴ ዓመቱ ተጠምቆ የዕዳ ደብዳቤያችንን እንደቀደደልን፣ ከዚያም ወንጌልን አስተምሮ በመጨረሻም ዓለምን ለማዳን በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ፣ ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ እንደተነሣ አምነው ተቀበሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በመልካም ሥራ መንፈሳዊ ፍሬ አፍርተው ወደ እግዚአብሔርም በክብር ይሄዱ ዘንድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያውቁና እንዲፈጽሙ በኤጵፍርስ እጅ በላከላቸው መልእክቱ መከራቸው፡፡ (ቈላ. ፩፥፱-፲)

ከዚህ ጋር አንድ ታሪክ እንደ ምሳሌ እናንሣ፤ በአንድ ወቅት አንድ ሰው ወደ መነኩሴው አባ መቃርስ በመሄድ ለመዳንናና የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ ምን ማድረግ እንዳለበት ሲጠይቀው አባ መቃርስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ‹‹ወደ መቃብር ቦታ ሂድና ሙታንን (የተቀበሩትን ሰዎች) ስዳበቸው›› እርሱም እንደተባለው ወደ መቃብር ቦታ በመሄድ የሞቱተን ሰዎች ሲሳደብ ውሎ እና ድንጋይ ወርውሮባቸው ምንም ምላሽ ስላላገኘ ወደ መነኩሴው ተመለሰ፤ ከዚያም መነኩሴው አባ መቃርስ ‹‹ምን አሉህ?›› ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ምንም አላሉኝም፤›› አባ መቃርስ  መልሰው፤ ‹‹ነገ ተመልሰህ ሂድና አመስግናቸው›› አሉት፤ እርሱም ወደ መቃብር ቦታ በመሄድ ‹‹እናንተ ሐዋርያት፣ ቅዱሳንና ጻድቃን ሰዎች ናችሁ›› እያለ ሲያመሰግናቸው ውሎ በተመሳሳይ ሁኔታ ምላሽ በማጣቱ ወደ አባ መቃርስ ተመልሰ፤ አባ መቃርስም ‹‹ምንም አልመለሱልህም?›› ብሎ ሲጠይቀው እርሱም ‹‹አልመለሱልኝም፤›› ብሎ መለሰላቸው፤ አባ መቃርስ መልሰው ‹‹ ሙታንን እንደሰደብካቸውና ምንም እንዳልመለሱልህ፣ እንደገናም ስታመሰግናቸው ምንም ነገር እንዳልተናገሩህ አይተሃል፤ አንተም ልትድን ከፈለክ እንዲሁ ማድረግና የሞትህ መሆን አለብህ፤ ልክ እንደ ሙታን የሰዎችን ነቀፌታቸውንም ሆነ ምስጋናቸውን ከቁም ነገር አትቁጠረው፤ ቦታም አትስጠው፤ እንዲህ ብታደርግ ትድናለህ›› ብለው መከሩት፡፡ (ከበርሐውያን ሕይወትና አንደበት ገጽ.፩፵፱)

የአባቶቻችንን ምክርም ተግባራዊ በማድረግ በድኅነት መንገድ እንጓዝ ዘንድ ተገቢ መሆኑን ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡ ይህንን ዓለምም ንቀንና አጥቅተን መኖር ያስፈልጋልና፤ ሐዋርያው ቅዱሰ ጳውሎስም ‹‹በእኔ ዘንድ ዓለሙ  የሞተ ነው፤ እኔም በዓለሙ ዘንድ የሞትሁ ነኝ›› ብሎ እንደተናገረው ይህን ምድራዊ ዓለምን ንቀን በሰማይ ያለውን ማሰብ እንዳለብን አንገነዘባለን፡፡  ሐዋርያው ‹‹የላይኛውን አስቡ›› ማለቱ በሰማይ ያለውን የእግዚአብሔርን ግዛት እንድናስብ እንጂ በዓይናችን የምናያቸውን ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ ከክዋክብትን እንዲሁም ደመናንና በምድር ያሉትን እንድናስብ አይደለምና፡፡  (ገላ.፮፥፲፬)

ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ደግሞ ‹‹እናንተ ግን የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ፥ በሰማያት ወደ አላቸው ኢየሩሳሌም፥ ደስ ብሎአቸው ወደሚኖሩ አእላፍ መላእክትም ደርሳችኋል›› ብሎ እንደነገረው እኛም ይህን አላፊና ጠፊ ዓለም ትተን ዘለዓለም ተድላና ደስታ ወደሚገኝበት መንግሥተ ሰማያት መድረስ እንደሚቻል አስተምሮናል፡፡ (ዕብ. ፲፪፥፳፪)

በምድር ላይ ያለ ቤት በሙሉ በስሚንቶና በሌሎች የሚታዩ ቁሳቁሶች እንደሚሠራና ፈራሽ እንሆነ ነገረ ግን በሰማይ ያለችውን ዘለዓለማዊ ቤት ግን የሠራት እግዚአብሔር በመሆኑ ዘለዓለማዊ መኖሪያ እንደሆነች ሐዋርያው አስረድቷቸዋል፡፡ ስለዚህ እነርሱም ከመላእክት ጋር አንድ ይሆኑ ዘንድ ወደ እነርሱ መድረሳቸውን አስረዳቸው፡፡ እዚህ የሚያዩት ምድራዊ እንደሆነ በኋላ እንደሚጠፋ፣ የሰዎች ከተማም እንደሚፈርስና ሁሉም እንደሚያልፍ ነገራቸው፡፡ ነገር ግን ወደ ማታልፈው ሰማያዊት መንግሥት፣ ወደ ጽዮን ተራራ፣ ወደዚያች ከተማ፣ ሁሉንም ወደ ሚገዛው እግዚአብሔር እንደሚደርሱ አበሠራቸው፤ ስለዚህ ምድራዊውን ዓለም እንዳይፈልጉም መከራቸው፡፡

የምድራዊ ሕይወት ጊዜያዊ በመሆኑ በሥጋዊ ድሎት ተታለን ተልኮአችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ የክርስቲያን ዓላማው ሁከትና ብጥብጥ፣ ምድራዊ ድሎትና ምድራዊ ምቾት ሳይሆን በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጾ፣ በሃይማኖት ጸንቶ መኖር ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም በመሆኑ የምታስተምረንም ዘለዓለማዊ መንግሥትን እንጂ ይህንን ኃላፊውን ዓለም እንድንኖር አይደለም፡፡ የእኛም ዓላማ ሊሆን የሚገባው ሰማያዊ መንግሥትን ለመውረስ ለበጎ ምግባር በቁርጥ ኅሊና መነሣሣት ነው፤ በትንሣኤ ዘጉባኤም የምናገኘው  የሥራችንን ወጤት ነውና፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር በቀኙ ያቆመን ዘንድ ቸርነቱን ያብዛልን፤ አሜን፡፡