ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጎቿን ይዛ እንድትዘልቅ …

ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.


በየዓመቱ በጥምቀት ወር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደርና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ላይ የሚመክረው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለሠላሳ አንደኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የእናት ቤተ ክርስቲያናቸውን የአገልግሎት ጥሪ የተቀበሉ ምሁራን ልጆቿ፤ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናት ጽሑፎቻቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ታላቅ ጉባኤ ላይ፤ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንታዊ አገልግሎት መቃናት የሚበጁ፣ በየሙያ ዘርፉ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ ምሁራን ልጆቿ የሚቀርቡ የጥናት ጽሑፎችና የሚካሄዱ ውይይቶች፤ እናት ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን ይዛ ዘመኑን እየዋጀች ጸንታ እንድትቀጥል በማድረግ ረገድ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡

 

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፎች የተቀላጠፈና ዘመናዊ የአስተዳደር መዋቅርና አሠራር እንዲኖር ማድረግ ወቅቱም ሆነ ትውልዱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ በሪፖርትና ትክክለኛ ክትትል ባልተለየው ግምገማ የተደገፈ፣ ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ማእከላዊ የፋይናንስ አስተዳ ደር ሥርዐት እንዲሰፍን ተጨባጭ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቷ ተጠናክሮ አስተዳደሯ፣ ሥርዐተ ከህነቷም ሆነ ሁለንተናዊ አገልግሎቷን የሚመለከቱ እንዲሁም የምእመናን መንፈሳዊ ጉዳ ዮች የሚዳኙበት አስተምህሮና ቀኖናዋን የጠበቀ መንፈሳዊ የፍትሕ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ችላ የሚባልበት ወቅት አይደለም፡፡

 

ከሐዋርያዊ ተልእኮዋ ባሻገር በማኅበራዊ አገልግሎቷም የበለጠ እንድትሠራ፤ በልማት ሥራ እንድትበለጽግ፣ ገዳማቷና አድባራቷ በገቢ ራሳቸውን ችለው ከልመና እንዲላቀቁ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅባታል፡፡ በእነዚህ ሁሉ መስኮች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሁራን ልጆቿን በማሳተፍ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ቀዳሚ ትኩረት መስጠት እንዲሁም ሁኔታዎችን ማመቻቸትና የበለጠ ጥረት ማድረግ አለባት፡፡

 

አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያለው ታላቅ መድረክ፤ በተራዘመ ሪፖርትና በተደጋገመ መልእክት የሚባክነው ጊዜ፤ በዓመት አንድ ጊዜ ከሚገኘው ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ አሳብ፣ ዕቅድና መፍትሔ የሚቀርብበትን ምቹ ሁኔታ በማሳጣት ያለጥቅም እንዲያልፍ ያደርጋል፡፡ ለተሻለ አሠራርና ለበለጠ ውጤት የሚያበቃ የውይይት መድረክ የሚሆንበትን ዕድል ይነፍጋል፡፡

 

ስለዚህ እንዲህ ዓይነቶቹን ክፍተቶች በመገንዘብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለን ተናዊ አገልግሎት የሚበጅ የጥናት ጽሑ ፎች እንዲቀርቡ ሐሳብ በመስጠት፣ ዕቅድ በማውጣት፣ ጊዜ፣ በጀትና የሰው ኀይል መድቦ ውይይቱ እንዲካሄድ የተደረገው ጥረትና የተከናወነው ሥራ የሚመሰገን ሲሆን ወደፊትም በተሻለ ሁኔታ ሊቀጥል የሚገባው ተግባር ነው፡፡

 

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብለው እውቀታቸውንና ሙያዊ ልምዳቸውን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በሚበጅ ተግባር ላይ ለማበርከት በቀናነት የተሳተፉት ምሁራን ልጆቿ የሚመሰገኑ ናቸው፡፡ አገልግሎታቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ መቃናት፣ በዘመናዊ አሠራር በተደራጀ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቷ የተሳካ አፈጻጸም እንዲኖረውና በልማት እንድትበለጽግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት በልዩ ልዩ የሥራ መስኮችና ቦታዎች የተሰማሩት ምሁራን ልጆቿ በየተሰጣቸው ጸጋና ሞያ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲያበረክቱ በማነሣሣት ረገድ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡

 

በየደረጃው ያሉት የቤተ ክህነቱ መዋቅርና አካላት ይህንኑ በጎ ልምድ መነሻ በማድረግ፤ በተለያየ ሙያና የሥራ መስክ የተሰማሩ ምሁራን በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በራቸውን ክፍት ማድረግና የአገልግሎት መድረኮችን ማመቻቸት እንደሚጠበቅባቸው ያመላክታል፡፡

 

በሠላሳ አንደኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ከቀረቡት ጽሑፎች መካከል፤ ለምሳሌ “የዘመናችንን ትወልድ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማብቃት የአባቶች ሚና” በሚል ርእስ የቀረበው ጽሑፍም ከላይ ያነሣና ቸውን ነጥቦች በአጽንዖት የጠቆመ ነው፡፡

 

በጥናት ወረቀቱ እንደተጠቀሰው፤ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ጎልቶ አይታይ ይሆናል እንጂ በየጊዜው ሃይማኖታቸውን የሚተው፣ ከቤተ ክርስቲያናቸው የሚኮበልሉ ምእመናን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ምእመናንን ወደ ውጪ የሚገፉ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ይበልጥ እየተሻሻሉ ዘመኑን መዋጀት ካልቻሉ ውጤቱ ያማረ አይሆንም፡፡ ለዚህም ነው የዛሬውን ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቁ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ የሚሆነው በማለት የቀረበው ሐሳብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡

 

ምናልባትም በታላላቅ ከተሞች ባሉ ገዳማትና አድባራት የሚታየው እንቅስቃሴ፤ በወርና በዓመት የንግሥ ወይም ዐበይት በዓላት የሚታየው የሕዝበ ክርስቲያኑ ብዛትና ድምቀት በየገጠሩና በየበረሐው ያለውን አገልግሎት እንቅስቃሴና የምእመናኑን መጠን የሚያሳይ ነው የሚል የተሳሳተ ግምት ካለ፤ ገሐድ እውነቱ ከተሳሳተው ግምት የተለየ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

ስለዚህ ትውልዱን በቤተ ክርስቲያን እቅፍ ሰብስቦ ለአገልግሎት በማብቃት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ዘመኑን በዋጀ ውጤታማ አሠራር በተሳካ ሁኔታ ማፋጠን የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ባለው ዘመንና ትውልድ ደግሞ ሉላዊነትን (Globalization) መሠረትና ጉልበት ያደረገ ሥልጣኔ የተስፋፋበት፣ ዘመናዊነት የነገሠበት እንደመሆኑ፤ በዓለማችን የሚከሠቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ አቸው እያየለ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕልውናና አገልግሎት ፈተናዎች እየሆኑ ይታያል፡፡

 

ከዘመኑ የኑሮ ሁኔታ፣ የሥልጣኔ ውጤቶች፣ በተዛባ የዘመናዊነት ግንዛቤ የሚከሠቱት ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዎች በተለይ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያሳድሩበትን ጫና እንዲቋቋም አድርጎ ለጥያቄዎቹ ምላሽ በመስጠት ትውልዱን ይዞ ለመቀጠል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አፋጣኝ መፍትሔ ልትሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡

 

ስለዚህ በየአጥቢያው የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ማስፋፋት፣ ጉባዔያትን ማጠናከር፤ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በቅርበት ዕለት ዕለት መከታተል፣ መምህራነ ወንጌል መመደብ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማሟላት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከርና በማስፋፋት አገልግሎታቸውም በበለጠ ጥረት የተሻለ ውጤት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቃል፡፡

 

ከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማቱን በተሟላ አደረጃጀትና ዘመናዊ አሠራር እያጠናከሩ ማስፋፋት እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በቀና ዓላማ ገብተው በቂ ዕውቀት ቀስመው ለአገልግሎት እንዲዘጋጁ ያስችላቸዋል፡፡ ሌሎችም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መንገዶችን የቴክኖሎጂውን እድገትና ዕድል በመጠቀም፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በመላው ዓለም በየቦታው ላይ ለምእመናን፤ በመገናኛ ብዙኃን ቃለ እግዚአብሔርን ማድረስ የግድ ይላል፡፡

 

አብነት ትምህርት ቤቶቻችን በብዙ ችግሮች ተተብትበው መምህራኑም ሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ፈተና ላይ ወድቀዋል፡፡ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴው ጊዜን፣ ቁሳዊ ሃብትን፣ ወቅትንና ሌሎችም አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ ሁኔታ ተመቻችቶ ባለመካሄዱ በቀጣይነቱ ላይ የተጋረጠ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ችግሮቹን አዝሎ ያንዣበበው አደጋ ከቀጠለ የካህናትና ሊቃውንት አገልጋዮቿ ምንጭ እየተዳከመ የነገይቱ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ስኬትም አጠያያቂ መሆኑን ከወዲሁ ማሰብ፤ አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግና በተግባር ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ሊቃውንቱ እንዲያስተምሩ፣ የተካበተ ዕውቀታቸው ለምእመናን እንዲደርስ መርሐ ግብር ማዘጋጀት፣ መድረኮችን ማመቻቸትና እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህም በላይ ሰፊ የዕውቀት ሀብታቸው፣ ከመንፈሳዊው አገልግሎትና ሕይወታቸው ልምድ ጋር ለትውልድ እንዲተላለፍ ምእመናን እንዲጠቀሙበት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲጽፉ ማበረታታት፣ የሚያስፈልጋቸውን ማገዝ ማሳሰብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

 

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች ትውልዱን ከማስተማር ጎን ለጎን የዕለት ተዕለት ክትትልና መንፈሳዊ ጥበቃ ማድረግ እንዳለባቸው ዋነኛ የአባትነት ሓላፊነታቸው እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በሕይወታቸው መልካም አርአያ በመሆን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መትጋትና ሃይማኖታዊ ሓላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው፡፡

 

በአጠቃላይ በጎቹን በቃለ እግዚአብሔርና በመንፈሳዊ ሕይወት ጠብቆ በእናት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ እንዲዘልቅ፤ በቀና መንፈስ በአገልግሎት እንዲሳተፍ ማስቻል፣ በፍቅርና በመልካም የአባትነት አርአያ መቅረብ፣ መከታተል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ቀዳሚ ሥራ ነው እንላለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 4 2005 ዓ.ም.