ቅዱስ ገላውዴዎስ

ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የሮሙ ንጉሥ የኑማርያኖስ ወንድም ከሆነው አባቱ አብጥልዎስ የተወለደው ገላውዴዎስ የመላእክት አርአያ የተባለ ቅዱስ ነው፡፡ የአንጾኪያ ሰዎችም አባቱን እጅግ ይመኩበትና ይወዱት ነበረ፤ በሕይወት እያለም በጦርነት ድል ሲያደርግ የሚያሳይ ሥዕሉን በከተማው ላይ አሠርተው ያከብሩት ነበር፤ ልጁ ቅዱስ ገላውዴዎስ ግን የቤተ ክርስቲያንን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዘወትር ያነብ ነበር፤ የሮሙ ንጉሥም ዜናውን ሰምቶ ሊያየው ስለወደደ ልጁን እንዲልክለት መልእክት ላከ፤ ሄዶ ሲያየውም ንጉሡ ከነሠራዊቱ ወጥቶ በክብር ተቀበለው፡፡

ከዚህም በኋላ የቁዝና የሌሎች ጣዖት አምላኪ የሆኑ ሀገሮችን ቅዱስ ገላውዴዎስ ድል እያደረጋቸው ጣዖቶቻቸውንም ሰባበረባቸው፤ ወደ አንጾኪያም በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስ ጌታችንን ክዶ ጣዖት ማምለክ መጀመሩን ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ እርሱና ቅዱስ ፊቅጦርም የመጻሕፍትን ቃል ዘወትር ያነቡ ነበር፤ ሁለቱም ስለ ጌታችን ክብር ሰማዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ በምክር ተስማሙ፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀንም ሰይጣን በሽማግሌ አምሳል ተገልጦ ያዘነላቸው በመምስል ‹‹ልጆቼ ሆይ መልካም ጎልማሶች ናችሁ፤ የነገሥታት ልጆችም ናችሁ፤ እኔ ስለ እናንተ አዝንላችኋለሁ፤ ስለዚህም ከንጉሡ ጋር ተስማምታችሁ አማልክቶቹን ታጥኑ ዘንድ እመክራችኋለሁ፤ ሲያዛችሁም ትእዛዙን አትተላለፉ፤ እናንተም ክርስቶስን በቤታችሁ አምልኩት፤ ይህ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ግን እጅግ ጨካኝና ኃይለኝ ነው›› ብሎ መከራቸው።

እግዚአብሔርንም ይህን የሚናገራቸው ሰይጣን መሆኑን ገለጸላቸውና ‹‹አንተ የሐሰት አባት ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ትቃረናለህ›› ብለው በገሠጹት ጊዜ መልኩን ለውጦ ጥቁር ባሪያ ሆነ፡፡ ‹‹እነሆ ከንጉሡ ጋር አጣልቼ ደማችሁን እንዲፈስ አደርገዋለሁ›› ብሎ ወደ ከሃዲው ንጉሥ ወደ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ በመሄድ ‹‹ፊቅጦርንና ገላውዴዎስን ካልገደልካቸው በአንተ ላይ ይነሱብሃል፤ አንተንም ገድለው መንግሥትህን ይወስዳሉ፤ እነርሱም የመንግሥት ልጆች መሆናቸውን ዕወቅ›› አለው፡፡
ከዚያም ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ገላውዴዎስን አስጠርቶ የአባቱን ሹመት እንደሚሾመው በመናገር ሊሸነግለው ሞከረ፤ ለጣዖቱ እንዲሰዋም አዘዘው፤ ነገር ግን ቅዱስ ገላውዴዎስ በድፍረት ጣዖቱንና ንጉሡን ሰደባቸው፡፡

የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኅርማኖስ የተባለው ባለሟሉ ‹‹እንደ ልጄ ዐመፀኛ ነውና ወደ እስክንድርያ ልከነው በዚያ እንዲገድሉት እናድርግ›› ብሎ ዲዮቅልጥያኖስን መከረው፤ አሠቃይተው እንዲገድሉትም ከደብዳቤ ጋር አድርገው ወደ እንዴናው ሀገር ገዥ ወደ አርያኖስ ላኩት፡፡ አርያኖስም ቅዱስ ገላውዴዎስን ባየው ጊዜ በክብር ተቀብሎ ‹‹ጌታዬ ስለምን የንጉሡን ትእዛዝ ትተላለፋለህ?›› እያለ መከረው፡፡ ቅዱስ ገላውዴዎስም ‹‹ንጉሡ ያዘዘህን ትእዛዝ ልትፈጽም እንጂ በነገርህ ልታስተኝ አልተላኩም›› አለው፡፡ ለበርካታ ጊዜም እያባበለው በተነጋገሩ ሰዓት ንጉሡ እጅግ ተቆጣና በያዘው ጦር ወግቶ ገደለው፡፡

ምእመናንም ቅዱስ ሥጋውን ወስደው ከቅዱስ ፊቅጦር ጋር በሣጥን አኖሩት፡፡ የቅዱስ ፊቅጦርም እናት ቅድስት ሶፍያ ወደ እንዴና ሀገር መጥታ የሁለቱን ቅዱሳን ሥጋቸውን ወደ አንጾኪያ ወስዳ በክብር አኖችው፡፡

የሰማዕቱ የቅዱስ ገላውዴዎስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን፡፡