ቅዱስ ሲኖዶስ

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ
«አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት»
kidusSinodos.jpg
በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባዔ ጌታ በሚያውቃት ዕለት ይህች ዓለም ታልፋለች፡፡ እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ይህ ዓለም ካለፈ በኋላ የማይጠፋ እና የማይለወጥ የዘለዓለም መኖሪያ የሆነ ሌላ ዓለም ደግሞ አለ፡፡ ያም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡ የሰውን ልጆች ለእግዚአብሔር መንግሥት የምታበቃው እውነተኛዋ ፍኖት ደግሞ ክርስትና ናት፡፡ /ኤር 6.16/ እርሷም አንዲት ናት፡፡ የተሰጠችውም ፈጽማ አንድ ጊዜ ነው፡፡ /ይሁዳ 1-3/

ክርስትና አንድ ጌታ የሚመለክበት በአንዲት ጥምቀት ልጅነት የሚገኝበት በአንድ ተስፋ በአንድነት የሚኖርበት ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ እምነት በየጊዜው በዓለም በሚነሱ መጤ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች እንዳይበከል በእርሱም አምነው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚጓዙ አማንያን አንድነታቸው እንዳይፈታ በእግዚአብሔር የተሠራ ጉባዔ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስለቤተክርስቲያን ዶግማ ቀኖና ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም አስተዳደር የሚመክሩበት በመንፈስ ቅዱስ የሚቃኝ ጉባዔ ነው፡፡ ይህም «ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳትና ኤጲስ  ቆጶሳት የሚያደርጉት ዓቢይ ጉባዔ ነው፡፡» ተብሎ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተገለፀው ነው፡፡ /ሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 2(2)/፡፡

አንዳንድ ሊቃውንት የቅዱስ ሲኖዶስን ሥርዓት አጀማመር ጌታ ከሐዋርያት ጋር ያደረጋቸው ስብሰባዎች መነሻ አድርገው ያመጣሉ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው የሚገኙ ሦስት ጉባዔያትን አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያው በይሁዳ ምትክ አንድ አባት መርጠው ሐዋርያ ለመሾም ያደረጉት ጉባዔ ነው፡፡/የሐዋ 1፥15-16/ ሁለተኛው ሰባቱን ዲያቆናት ለመሾም የተደረገው ጉባዔ (ሲኖዶስ) ነው፡፡ /የሐዋ 6.1-6/ የመጨረሻው ከአሕዛብና ከአይሁድ ወደ ክርስትና በመጡት መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው ነው፡፡/የሐዋ.15፥1/

በጉባዔ ኬልቄዶን ምክንያት የሃይማኖት መከፋፈል ከመጀመሩ በፊት የአካባቢ ሲኖዶሶች እምብዛም የተለመዱ አልነበሩም፡፡ ዛሬ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሦስቱ ጉባዔት ብቸኞቹ ዓለም አቀፍ ጉባዔያት ናቸው፡፡ እርሱም በኒቅያ በ325 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም እንዲሁም በኤፌሶን 431 ዓ.ም የተካሔዱት ናቸው፡፡

ከዚያ በኋላ ግን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በየራሣቸው መንበር የአካባቢ ሲኖዶስ ማድረግ ቀጥለዋል፡፡ እነሆ የእኛም ቤተ ክርስቲያን በራሷ ሲኖዶስ መመራት ከጀመረች ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ሆኗል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መገለጫ ነው፡፡ በየጊዜው በሚወለዱ ክስተቶች ዶግማዊ ቀኖናዋ ሥርዓቷ ትውፊቷ እንዲሁም አስተዳዳሯ እንዳይፈታ መጠበቂያ ነው፡፡ በዚህም በመሠረት እምነቷ ላይ ጥያቄ ሲነሳ ማብራሪያ መስጠት አዳዲስ አስተምህሮዎች ሲመጡ በዶግማዊ መሠረት ማረቅ ማቅናት የጾም የጾሎት ሥርዓትን መሥራት ልጆቿን የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ተግባራት ናቸው፡፡

አስቀድመን እንደገለጽነው ክርስትና በማኅበር የሚኖርበት በማኅበር ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡

ይህ ማኅበር በአንዳች ምክንያት እንዳይበተን የአንድነት መገለጫው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

ምዕመናን ሁል ጊዜ ሊሰሙት የሚገባው የቤተ ክርስቲያን ድምጽ ይህ የአንድነቷ መገለጫ ከሆነው ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጣው ድምጽ መሆን አለበት፡፡ አንድ ክርስቲያን በአኗኗሩ ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሚደነግጋቸው ድንጋጌዎች ተገዢ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ አልተስማማኝም ይህ ጐረበጠኝ ብሎ በግልም በቡድንም መጓዝ ከሕይወት መንገድ ይለያል፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ፍጹምና የማይሳሳት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሲኖዶስ ተሳሳተ ተብሎ ሌላ አቋራጭ መንገድ መከተል ደግሞ የበለጠ ለጥፋት የሚዳርግ ነው፡፡ ሲኖዶስ ቢሳሳት የሚስተካከለው በራሱ በሲኖዶሱ ሥርዓትና ደንብ ብቻ ነው፡፡

ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መገዛት የማኅበረ ምዕመናን አባልነት በዚህ ምድር ያላችው የእግዚአብሔር መንግሥት ነዋሪነት መገለጫ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ እግዚአብሔር ሃሣቡን ፈቃዱን ለልጆቹና ለቤተ ክርስቲያን የሚያስተላልፍበት መንፈሳዊ ጉባዔ ነው፡፡
ለእስራኤል ዘሥጋ ሥለ አንድነታቸው ስለአኗኗራቸው በነሊቀነብያት ሙሴ በኩል ሥርዓትን የሠራ እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ክርስቲያኖች እስራኤል ዘነፍስም ሥለ አንድነታችን ማኅበራችን እንዴት በሥርዓት ልንኖርበት እንዲገባ ሥርዓቱን የሚሠራልን በብጹአን አበው አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም ከመንጋው ተለይቶ ላለመቅበዝበዝ የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ መስማት ተገቢ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር