ቁጣና መዘዙ

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

ጥር ፩፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

“በወንድምህ ላይ በከንቱ አትቆጣ” ከስድስቱ ቃላተ ወንጌል አንዱና የመጀመሪያው ትእዛዘ እግዚአብሔር ነው:: (ማቴ.፭፥፳፪-፳፮) ኃይለ ቃሉ ሲብራራም:- ሰው የሆነው ሁሉ ወንድምህ፣ ወዳጅህ ነው፤ ስለዚህ አትጥላው፤ አትጣላውም፤ በሆነውም ባልሆነውም አትቆጣው ለማለት ነው። ሰዎች ከድንገተኛ ቁጣ ተነሥተው እስከ ነፍስ መግደል ይደርሳሉና፡፡ ቁጡ ሰው ጠላቶቹን ብቻ ሳይሆን ወዳጆቹንም ይጎዳል፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ቁጣህን ከአንተ አርቅ። በቁጡ ሰው ተዋሕዶት የሚኖር መንፈሰ እግዚአብሔር የለምና።

ቁጣ የሚጫር የእሳት ክብሪት ማለት ነው፡፡ እሳት አንድ ጊዜ በክብሪት ከተጫረች በኋላ ሰደድ እሳት ትሆናለች፡፡ በቁጣ ሁሉም የኃጢአት ዓይነቶች ከመዛግብቶቻቸው ወጥተው ይቀጣጠላሉ፡፡ አንድን ሰው ድንገት አንድ ቁጡ ሰው ተነሥቶ ክፉ ቢናገረውና በይቅር ባይነት መንፈስ ቢያልፈው እንኳን ያ ቁጡ ሰው ቀኑን ሙሉ በቁጣ ላይ ሠልጥኖ ይውላል። በመሆኑም ተገቢ የሆነ ቁጣ ብንቆጣ እንኳን ቶሎ ልንተወውና ይቅር ልንል ይገባል። ካልሆነ ግን ይህ ቃል በፍርድ ቀን በእኛ ላይ ምስክር ይሆንብናል፡፡ “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት” ብሎ ሐዋርያው የመከረን ምንም በጫና ውስጥ ብናልፍ በእኛ ውስጥ ተፀንሶ ያለ ቁጣ ሕይወታችንን ሊጎዳ ስለሚችል ነው። (ኤፌ.፬፥፳፯)

ለጊዜው ንዴታችንን በቁጣ ስንወጣ የሚያስደስት መስሎ ቢታይም ይህ በእኛ ውስጥ ሰይጣን የዘራውን ክፋ ዘር ፍሬ (ተገቢ ያልሆነ ቁጣ) ከማፍራቱ በፊት ከሥሩ ነቅለን ልንጥለው ይገባል።ተገቢ ያልሆነ ቁጣ ከርኩስ መንፈስ አነሣሽነት የሚመነጭ እንጂ ከቅዱስ መንፈስ የሚገኝ አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል ተገቢ ያልሆነ ቁጣን እንደሚያወግዝ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ላይ ተገልጿል።

ተገቢ ያልሆነ ቁጣ ትዕግሥት ከሌላቸው ሰዎች የሚመነጭ ነው። ትዕግሥት ማጣትና ቁጣ ተመሳሳይነት አላቸው። ትዕግሥት ካለን የሚያስቆጣንንና የሚያበሳጨንን ነገር ሁሉ እናልፈዋለን፡፡ የሚያጣላን ነገር ቢሆን እንኳን እስከ መጨረሻ ጥግ ድረስ ክፉ የምንለውን ነገር ሁሉ ሊያስደርገን የሚችል ነገር ሁሉ ቢገጥመንም በአስተማማኝ ሁኔታ ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን ማለት ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሥጋ ሥራን ሲዘረዝር ቁጣንም ይጨምራል። እነርሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖት ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካርና ዘፋኝነት በማለት ነው። በመቀጠልም ቅዱስ ጳውሎስ እንደዚህ ያሉት የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ይናገራል። (ገላ.፭፥፲፰)

ፍጹማን ሆነው ያሉ የገዳም አባቶቻችን እንኳን በተገቢ ነገር ይቆጡና ወዲያውኑ “ይቅር በለኝ ፈጣሪዬ” ብለው ምልስ ይላሉ። ስለዚህ ሰው ሆነን በለበስነው ሥጋ የሚቆጣ ሥጋ ስላለን “ተቆጥቻለሁ፤ ይቅር በለኝ” ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከሰው ጋር የተቆጣንበት ካለም ወዲያው “ጀንበር ሳይገባባችሁ ቶሎ ቁጣችሁን በቸርነት በይቅርታ በምሕረት አስወግዱ ስለተባለ ወዲያው ሄዶ ያስቆጡት፣ የተጣሉት፣ ያስቀየሙት ወይም ያስቀየማቸው ካለ “ይቅር በለኝ ወንድሜ!”፣ “ይቅር በይኝ እኅቴ” ተባብለው ወዲያው ይታረቃሉ። ስለዚህ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በመልአካዊ ባሕርያችን ይቅር ባዮች እንሆናለን ማለት ነው። ስለዚህ ቁጣን በትዕግሥት ብናሸንፈው ሰውንም፣ ራሳችንን እንጠቅማለን፡፡ ቁጡዎች ሆነን ብንቀጥል ደግሞ በነፍስ ብቻ አይደለም በሥጋችንም ስለምንጎዳ ቶሎ በትዕግሥት መብረድና መመለስ ተገቢ ነው።

ቁጣንና ንዴትን እንዴት መተው እችላለሁ?

የሚቆጣ ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የለውም፡፡ የእግዚአብሔርን መልካም ነገር እንዳንሠራ የሚያደርገን ነው፡፡ በእርግጥ የሚገባ ቁጣና፣ የማይገባ ቁጣ እንዳለ እናምናለን፡፡ ዋጋ ያለው ቁጣ መቆጣት እንደሚገባ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም አስቀምጠዋል፡፡ ይኸውም ሃይማኖት ሲሸረሸር፣ ዶግማው፣ ቀኖናውና ሥርዓቱ ሲጠፋ፣ ምእመናን የተማሩትን ሲዘነጉ፣ መናፍቃን ሲሠለጥኑ ተቆጥቶና ገሥጾ ማስተማር ይገባል፡፡ ነገር ግን እንዲሁ ከእኅት፣ ከወንድም፣ ከጎረቤት ጋር መቆጣት ተገቢ አይደለም፡፡ ስለሆነም ተቆጥተንስ የምናገኘው ጥቅም ምንድን ነው? የሚለውን ማወቅና መረዳት ይገባናል ማለት ነው::

እንድንቆጣ የሚያደርጉትን ነገሮች በተከሠቱ ጊዜ ራስን መግዛት ይገባል፤ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል መንፈሳዊው ሰው ዘወትር ከቁጣ ለመራቅ ይሞክራል፡፡ «… የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና፡፡›› (ያዕ.፩፴፥፳) ንዴት በልቡ ውስጥ መንቀሳቀስ መጀመሩን ሲያውቅ ምላሱንና ነርቩን እንዲቆጣጠሩበት አይተዋቸውም፡፡ ስለሆነም በቁጣ ጊዜ ቃላቱን በሚገባ ለመቆጣጠር እንዲችል ዝም ማለት ይመርጣል፡፡ በዚህም በሚችለው ሁሉ በቁጣ አንዳይቀጣጠልና ድምፁ ከፍ ብሎ እንዳይወጣ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጊዜ አኳኋኑ ሁሉ የሐዋርያውን ቃል የተከተለ ይሆናል፡፡ «ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ይሁን . . .›› (ያዕ.፩፥፲፱:) ለቁጣ የፈጠነ ሰው በጥድፊያ ስለሚወድቅ ብዙ ኃጢአት ይፈጽማል፡፡ በተረጋጋ ጊዜ ቀድሞ በችኮላ በወሰደው የተሳሳተ እርምጃው አብዝቶ ይጸጸታል። በመጨረሻም በቁጣው ውስጥ መንፈሳዊውን መልክ ስለሚያጣ ለብዙዎች የማሰናከያ ድንጋይ ይሆናል።

መንፈሳዊው ሰው በቁጣ ውስጥ እያለ ደብዳቤ አይጽፍም:: ብስጭት ውስጥ እያለም ውሳኔ አይወስንም፡፡ ምናልባት ግን በቁጣ ውስጥ እያለ ደብዳቤ ከጻፈ ተጣድፎ ወደ ፖስታ ቤት አይልከውም፡፡ ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ በድጋሚ ያነበውና ወይ ቀዶ ይጥለዋል አለበለዚያም አስተካክሎ ይጽፈዋል፡፡ ይህን በማድረጉም በእርሱ ላይ የኃጢአት መረጃ እንዳይሆንበትና ውጤቱም የማያስደስት ሆኖ እንዳይቀር ያደርጋል። ሰው በተናደደ ጊዜ ውሳኔዎቹን የሚወስደው ባለማስተዋል ስለሆነ እንደነዚህ ዓይነት ውሳኔዎች «ስሜታዊ ውሳኔዎች» ተብለው ይጠራሉ፡፡ ብዙዎቹ የተሳሳቱና ተገቢ ያልሆኑ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፤ ቁጣ በሰነፍ ብብት ያድራልና፡፡» (መክ.፯፥፱)

በሌላ ቦታም “ቁጣን መጎተት ጠብን ያወጣል” ተብሏል፤ (ምሳ.፴፥፴፫) መቆጣት ወደ መሳደብ ደረጃ ያደርሳል፤ ከመሳደብ ወደ አምባጓሮና ድብድብ፣ ከዚያም አካል ወደማጉደል በመጨረሻም ወደ ነፍስ መግደል የሚያደርስ ነው። መቆጣት የመጀመሪያው ደረጃ ስለሆነ ከዚያ በላይ ላለማለፍ ቁጣችንን በትዕግሥት መግታት ያስፈልጋል። መንፈሳዊው ሰው አንደበቱን መግታት እንደ ቻለ ሁሉ አሳቡንም መግዛት ይችላል፡፡ እርሱ የጀመረውን መንፈሳዊ መንገድ በሆነ አሳብ ምክንያት ስቶ እንዳይወጣ አሳቡን ይገታል፡፡ ወደ አሳቡ የሚመጣውን የኃጢአት አሳብ ሁሉ አይቀበልም፡፡

ነፍስ ከመግደል መለስ የሚፈጸሙ የዓመፅ ሥራዎች እንዳሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል። እነርሱም በከንቱ መቆጣት፣ መሳደብ ከሰው ጋር መጣላት፣ መደባደብና ክፉን በክፉ መቃወም ብቀላና ጥላቻ የመሳሰሉት ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ሁሉ በስድስቱ ቃላተ ወንጌል ተከልክለዋል፡፡ (ማቴ.፭፥፳፩-፵፰) በወንጌል ትእዛዝ መሠረት እንኳን መግደል ቀርቶ መቆጣትና መሳደብ ያስፈርድብናል። “አትግደል እንደተባለ ሰምታችኋል የገደለ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነም እሳት ፍርድ ይገባዋል” እንዲል፡፡ (ማቴ.፭፥፳፩-፳፮)

በቀልና ቁጣ የሚያስከትለው ጸጸት፦

በቀልና ቁጣ ስርየተ ኅጢአትንና ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን የሚያሳጡ እኩይ ግብራት ናቸው። እኛ “ይቅር በለን” ስንል የበደሉንን ይቅር ማለታችንን ማረጋገጥ አለብን። አምላካችን ዘወትር በምንጸልየው “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ይቅር በሉ “ቂምና በቀልን አውላችሁ አታሳድሩ” እያለ አስተምሮናል። መጸጸታችን በቁጣና በትዕቢት በሽንገላና በማስመሰል ከሆነ አሁንም መጸጸታችን ትክክለኛ አይደለም።

ቁጣና ንዴት ከትንሽ ጀምሮ ራስን ወደ ማጥፋት የሚያድግ ተግባር ነው፡፡ ራስ ማጥፉት በተአምራዊ ኃይል የተገደድንበት ሳይሆን የአስተሳሰባችን ውጤት ነው፤ ይህ ደግሞ ተቀጣጥሎ ውጤቱ ዐመጽ /ሞት/ እንዲሆን የሚያደርገው የሚያራግበው ጭንቀት፣ ንዴት፣ ቁጣ ናቸው፡፡ ራስን ማጥፋት ደግሞ ሌሎችን ወይም ከዚህ ውሳኔ ያደረሰንን ችግር የምንበቀልበት ሳይሆን ራሳችንን የምንበቀልበት የተሳሳተ የውድቀት ምላሽ ነው። “ተወዳጆች ሆይ! ራሳችሁን አትበቀሉ!” (ሮሜ ፲፪፥፲፱)