‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምሕላ፤ ጾምን ለዩ! ምሕላንም ዐውጁ›› (ኢዮ.፩፥፲፬)

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ

ሰኔ ፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጦ ፍርሃትና ሥጋታቸው የተወገደላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ለወንጌል አገልግሎት ከመሠማራታቸው በፊትና ሕገ ወንጌልን ከማስተማራቸው አስቀድሞ አገልግሎታቸው እንዲቃና፣ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለያቸውና የመንፈስ ቅዱስን ምሪትና ኃይል ለመቀበል ሱባኤ ያዙ፤ ሀብተ መንፈስ ቅዱስም በአገልግሎታቸው እንደሚበዛ ሲያረጋግጡ ቅዱሱን ወንጌል የሚያገለግሉበትን ክፍለ ዓለም ዕጣ በመጣጣል ዕጣው ወደ ደረሳቸው የአገልግሎት ቦታ መሰማራታቸውን የቤተ ክርስቲያን የታሪክ መዛግብትና ሊቃውንት አባቶቻችን ያስረዳሉ፤ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ማለትም በዓለ ጰራቅሊጦስን ተከትሎ ከአገልግሎት በፊት በቅዱሳን ሐዋርያት የተጾመ ጾም በመሆኑ‹‹የሐዋርያት ጾም›› ብላ በመሠየም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን  ለሕዝበ ክርስቲያኑ ጾም ታውጃለች፡፡ ‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምሕላ፤ ጾምን ለዩ! ምሕላንም ዐውጁ›› እንዲል። (ኢዮ.፩፥፲፬)

በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው የተሰጡትን ታላቅ አደራ ከመሥራታቸው በፊት የእግዚአብሔር ዕርዳታ የሚጠየቅበት መንፈሳዊ ልምምድ በቀደሙት አባቶቻችን ዘንድም የተለመደ እንደነበር እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ሕገ-ኦሪት ለሚመራቸው ሕዝቦች ከማስተማሩ በፊት ጾሟል፤ በንጉሡ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ጠጅ አሳላፊ የነበረው ነህምያ የፈረሰውን የአባቶቹን ከተማ የኢየሩሳሌም ቅጥር መልሶ ለመሥራት በተነሣ ወቅት ጾምና ጸሎት ይዟል፡፡ (ነህም. ፪፥፲፩-፳፤፱)

ዓለምን ለማዳን የመጣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ የሆነውን ወንጌል ከመስበኩ በፊት ጾም አስፈላጊ መሆኑን ለማስረዳትና ለእኛ አርአያነቱን ሊያስተምረን እንደ ጾመ ጾሙን ከአጠናቀቀና የዲያብሎስን ፈተና ድል ካደረገ በኋላ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለትና ንስሓ ግቡ በማለት እንዳስተማረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡ (ማቴ.፬፥፩-፫) በዚህም መሠረት ሁለቱ ዐበይት አጽዋማት ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት በዓለ ጰራቅሊጦስን ተከትለው ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ) ይጀመራሉ፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማሩ በፊት ጾሟል፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም የተስፋውን ቃል መፈጸም እየተጠባበቁ እግዚአብሔርን መውረድና መወለድ እያሰቡ ይጾሙ እንዲሁም ይጸልዩ ነበር፡፡ (ዘፀ.፴፬፥፳፰)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የምግባር መሠረት መሆኑን ሊያስተምረን ወንጌልን ከመስበኩ አስቀድሞ ጾሟል፤ ሐዋርያትም በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ሕገ ወንጌልን ለሕዝቡ ከማስተማራቸው አስቀድሞ ጾመዋል፡፡ እኛም እነርሱን ተከትለን፣ በእነርሱ ሥርዓት በመመራት፣ በሐዋርያት ላይ ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብት በእኛም ላይ እንዲያድርብን በየዓመቱ ጾመ ሐዋርያትን እና ጾመ ድኅነትን፣ ሌሎችንም አጽዋማት አክብረን መጾም እንደሚገባን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል፡፡ (ማቴ.፬፥፩-፲፩፤ፍት.ነገ. ፲፭፥፭፻፹፮)

ጾመ ሐዋርያት ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው በመላው ዓለም ተዘዋውረው ወንጌልን ከመስበካቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ድኅነት ደግሞ ስያሜው እንደሚያመለክተው የመዳን ጾም ማለት ሲሆን ይህም በብሉይ ኪዳኑ አጽዋማት በጾመ አስቴር እና በጾመ ዮዲት የተተካ የሐዲስ ኪዳን ጾም ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በሐማ ምክንያት በእስራኤል ላይ ታውጆ የነበረው ሞት በጾመ አስቴር እንደ ተሻረ ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም በዕለተ ረቡዕ በጌታችን ላይ በተፈጸመው ምክር የሰይጣን ሴራ ፈርሷልና በጾመ አስቴር ምትክ ረቡዕን እንጾማለን፡፡

በብሉይ ኪዳን በጾመ ዮዲት ምክንያት ሆሎሆርኒስ ድል እንደ ተደረገበት ሁሉ፣ በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነት ዲያብሎስ ድል ስለተደረገ በጾመ ዮዲት ምትክ ዓርብን እንጾማለን፡፡ ዕለተ ረቡዕ የጌታችን ሞት የተመከረበት፣ ዓርብም አምላካችን የተሰቀለበት ዕለት ነውና በመስቀሉ መሥዋዕትነት ያገኘውን ድኅነት ዘወትር ማሰብ ስለሚገባን ሁል ጊዜ እንድንጾማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ሥርዓት ተሠርቶልናል፡፡ የእነዚህ የሁለቱ ቀናት (የረቡዕ እና ዓርብ) ጾም ጾመ ድኅነት ነው፡፡

በአጠቃላይ ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት እንደ ጾመ ነነዌና ዐቢይ ጾም የበዓላትና የአጽዋማት ማውጫ ቀመርን ተከትለው የሚመጡ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል የሚመደቡ የጾም ጊዜያት ናቸው፡፡ የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ (መፈጸሚያ) የቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በዓለ ዕረፍት ሐምሌ ፭ ቀ) ሲሆን፣ ጾመ ድኅነት ግን ከበዓለ ኀምሳ በስተቀር ዓመቱን ሙሉ የሚጾም ጾም በመሆኑ ፋሲካው በዓለ ትንሣኤ ነው፡፡

በዚህ ዓመት ጾመ ሐዋርያት ሰኔ ፮፣ ጾመ ድኅነት ደግሞ ሰኔ ፰ ቀን ይጀመራሉ፡፡ በመሆኑም የምንጠቀመው በራሳችን መልካም ተግባር፣ የምንወቀሰውም በራሳችን ኃጢአት መሆኑን ተረድተን ይሄ ቄሶች ወይም መነኰሳት የሚጾሙት ጾም ነው የሚል ሰበብ ሳንፈጥር ሁላችንም በአንድነት ብንጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ፣ ጸጋና ምሕረትን እናገኛለንና ራሳችንን ለጾም አዘጋጅተን እንጹም!