ስዊድናዊው ፕሮፌሰር አምሳ ሁለት መጻሕፍትን አበረከቱ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በስዊድን አገር የሉንድ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የኾኑት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሮቢንሰን በልዩ ልዩ ባለሙያዎችና በተለያዩ አርእስት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ አምሳ ሁለት መጻሕፍትን ለማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል በስጦታ መልክ አበረከቱ፡፡

ፕ/ር ሳሙኤል ሮቢንሰን መጻሕፍታቸውን ሲያስረክቡ

‹TAITU Empress of Ethiopia; Lake Tana and The Blue Nile an Abyssinian Quest; Education in Ethiopia Prospect and Retrospect; The Abyssinian Difficulty the Emperor Tewodross and the Magdala Campaign 1867-68; Slavery, Slave Trade and Abolition Attempts in Egypt and Sudan› የሚሉት ከአምሳ ሁለቱ መጻሕፍት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ መጻሕፍቱን ሲረከቡ

ወላጅ አባታቸው ፕሮፌሰር ሮቢንሰን፣ ከሌላ እምነት ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የተመለሱ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እንደ ነበሩና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግሎት እንደ ሰጡ ያስታወሱት ፕሮፌሰር ሳሙኤል፣ ማኅበሩ የሚያከናውነውን የጥናትና ምርምር ተግባር ለመደገፍና ለማበረታታት በውድ ገንዘብ የገዟቸውን እነዚህን መጻሕፍት በወላጅ አባታቸው ስም ለማእከሉ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በምጣኔ ሀብት፣ በታሪክ፣ በኅብረተሰብና አካባቢ ሳይንስ፣ በፖለቲካ እና ሌላም የትምህርት መስክ የተዘጋጁት መጻሕፍቱ በተለይ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ መጻሕፍቶቻቸውን ለማኅበሩ ያበረከቱት በስዊድን አገር የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በሚገኙት የቀድሞው የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዳይሬክተር ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜ አስተባባሪነት መኾኑን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሞላ ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንዳስታወቁት መጻሕፍቱ በተበረከቱበት ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከልዩ ልዩ ዓለማቀፍ የትምህርት ተቋማት የመጡ የውጭ አገር ዜጎች ከፕሮፌሰር ሳሙኤል ጋር በማኅበሩ ሕንጻ ተገኝተዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች በከፊል

በዕለቱ በነበረው መርሐ ግብር፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ዶክተር ዮሐንስ አድገህ (የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዋና ዳይሬክተር) የማኅበረ ቅዱሳንን አመሠራረትና የማእከሉን ተግባር በአጭሩ ለእንግዶቹ አቅርበዋል፡፡ ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜም ማኅበሩ በጥናትና ምርምር ማእከሉ አማካይነት ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን አገልግሎት አስረድተዋል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ፡- ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜ፣ ፕ/ር ሽፈራው በቀለ እና ፕ/ር ሳሙኤል ሮቢንሰን

መጻሕፍቱ አንባብያን ይጠቀሙባቸው ዘንድ በሕጋዊ ደረሰኝ ወደ ማኅበሩ ቤተ መጻሕፍት ገቢ መደረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ሞላ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ምሁራንን በማሳተፍ የሚያከናውነውን የጥናትና ምርምር ሥራ የውጭ አገር ዜጎች ለመደገፍ መነሣሣታቸው ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጩ ዓለም ዘንድ ያላትን ልዩ ቦታ ያመላክታል፡፡ መጻሕፍት ልገሳውም የጥናትና ምርምር ማእከሉን ወደ ተቋም ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ያግዛል›› ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ሞላ የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር

በመጨረሻም ፕሮፌሰር ሳሙኤልንና ሌሎች የትምህርት ባልንጀሮቻቸውን በማስተባበር መጻሕፍቱ ለማኅበሩ ቤተ መጻሕፍት ገቢ እንዲኾኑ ያደረጉትን ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜን የማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር በቤተ ክርስቲያን ስም አመስግነው ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የሚሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመደገፍ ፈቃደኛ የኾናችሁ አጋሮቻችን! እንደ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሮቢንሰን ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ለቤተ መጻሕፍታችን በማበርከት መንፈሳዊ ድርሻችሁን እንድትወጡ ይኹን›› ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጥናትና ምርምር ማእከሉ ሥር የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ቤተ መጻሕፍት ቅዱሳት መጻሕፍትን ብቻ ሳይኾን በልዩ ልዩ የትምህርት መስክና ቋንቋ የተዘጋጁ በርካታ ዓለማቀፍ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ለንባብ እንደሚያቀርብ፤ ዘወትር ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡3 – ምሽቱ 1፡00 ሰዓት (የምሳ ሰዓትን ጨምሮ) አገልግሎት እንደሚሰጥ ያስረዱት የማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር፣ ‹‹መንፈሳዊም ኾነ ዘመናዊ ዕውቀታችሁን ለማዳበር የምትፈልጉ ዅሉ ከማኅበሩ ሕንጻ ስድስተኛ ፎቅ ድረስ በመምጣት በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ኹኑ›› ሲሉ መንፈሳዊ ጥሪአቸውን አቅርበዋል፡፡