ስምና የስም ዓይነቶች

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

…ካለፈው የቀጠለ

የስም ሙያ ቃላት በዐረፍተ ነገር ላይ ያለ ሙያ ሊገቡ አይችሉም፡፡ ስምም ከቃል ክፍሎች እንደመሆኑ መጠን ያለ ሙያ በዐረፍተ ነገር ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ስም በዐረፍተ ነገር ውስጥ ሦስት ሙያዎች አሉት፡፡ እነሱም ባለቤትነት፣ ተሳቢነትና ቅጽልነት ናቸው፡፡

. ባለቤትነት፡-  በአንድ ዐረፍተ ነገር ውስጥ የተከናወነውን ድርጊት የፈጸመ ወይም ድርጊቱን የሚያከናውን ማለት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ድርጊቱ የሚፈጸምበት አካልም ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ዐረፍተ ነገር በገቢር እና በተገብሮ ወይም በአዳራጊና በተደራጊ ግስ ሲመሠረት የባለቤቱም ሁኔታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ፡- ዐረፍተ ነገሩ የተመሠረተበት ወይም ድርጊት አመልካች ግሱ ገቢር ከሆነ የዐረፍተ ነገሩ ባለቤት ድርጊት ፈጻሚ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዐረፍተ ነገሩ የተመሠረተበት ወይም ድርጊት አመልካች ግሱ ተገብሮ ከሆነ የዐረፍተ ነገሩ ባለቤት ድርጊት ፈጻሚ ሳይሆን ድርጊት ተቀባይ ወይም ድርጊቱ የሚፈጸምበት ይሆናል፡፡ ምሳሌ ፡- ዳዊት ቀተለ ጎልያድሀ፡፡ በዚህ ዐረፍተ ነገር ግሱ ቀተለ ነው ገቢር ግስ ይባላል፡፡ ባለቤቱ ደግሞ ዳዊት ነው፡፡ ለተፈጸመው ድርጊት ፈጻሚ፣ አከናዋኝ ነው፡፡ የተከናወነው ድርጊት ግድያ ነው፡፡ ስለዚህ ዳዊት የሚለው ስም ባለቤት ነው፡፡ ድርጊት ፈጻሚ ነው፡፡ ከላይ የተለገለጸውን ዐረፍተ ነገር በተገብሮ እንመልከተው፡፡ ጎልያድ ተቀትለ በእደ ዳዊት፡፡ ግስ ተቀትለ ተገብሮ ይባላል፣ ባለቤት ጎልያድ፣ድርጊት ግድያ ነው፡፡ በዚህ ዐረፍተ ነገር ድርጊት ተቀባዩ ባለቤት ነው፡፡

. ተሳቢነት፡- ተሳቢ የሚባለው በዐረፍተ ነገር ውስጥ የተፈጸመውን ድርጊት የሚቀበል ወይም ድርጊቱ የሚፈጸምበት ማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ ሁለት ዓይነት ተሳቢ ይኖራል፡፡ ርቱዕ (ቀጥተኛ) እና ኢ ርቱዕ (ኢ ቀጥተኛ)  በመባል ይታወቃል፡፡

ሀ. ርቱዕ (ቀጥተኛ)፡- የሚባለው ድርጊቱ የሚፈጸምበት ወይም በቀጥታ ድርጊቱን የሚቀበል ነው፡፡

ለ. ኢ ርቱዕ (ኢ ቀጥተኛ)፡- ደግሞ ድርጊቱ የሚፈጸምለት ወይም የሚፈጸመውን ድርጊት በተዘዋዋሪ መልኩ የሚቀበል ነው፡፡ በምሳሌ እንመልከት፡- ሰሎሞን ጸሐፈ ጦማረ ለአቡሁ፤ ሰሎሞን ለአባቱ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ በዚህ ዐረፍተ ነገር ሰሎሞን ባለቤት ነው፤ ጸሐፈ ማሰሪያ አንቀጽ፤ ጦማር ቀጥተኛ ተሳቢ፣ አቡሁ ኢ ቀጥተኛ ተሳቢ ይባላል፡፡ ጦማር በቀጥታ ድርጊቱ የተፈጸመበት ሲሆን አቡሁ የሚለው ደግሞ ድርጊቱ የተፈጸመለት ነው፡፡ አንድን ቃል ቀጥተኛ ተሳቢ ለማድረግ የሚከተሉትን ሕጎች ይከተላል፡፡ ስሙ በግእዝ፣ በራብዕ፣ በኃምስ፣ በሳብዕ ከጨረሰ እንዳለ ይሳባል፡፡ ስሙ በካዕብ ከጨረሰ ወደ ሳብዕ፤ በሣልስ ከጨረሰ ወደ ኃምስ፤ በሳድስ ከጨረሰ ወደ ግእዝ ይለወጣል፡፡ ምሳሌ፡- ቤቱ = ቤቶ፤ ቤት= ቤተ፤ ሐናጺ= ሐናጼ   የተጽውዖ ስም ሲሆን “ሀ” ይጨመርበታል፡፡

ምሳሌ፡- ዳዊት ዳዊትሃ፣ ጎልያድ ጎልያድሃ፣ ቶማስ ቶማስሃ… ከላይ የተገለጹትን ሕጎች በግልጽ ለመረዳት በምሳሌ እንመልከተው፡፡

ሀ. ኢሳይያስ ተነበየ ትንቢተ፤ ኢሳይያስ ትንቢትን ተናገረ፡፡

ለ. ኦርዮ ኢያእመረ ሞቶ፤ ኦርዮ ሞቱን አላወቀም፡፡

ሐ.ዜነወነ ገብርኤል ልደቶ ለወልደ አብ፤ገብርኤል የወልደ አብን ልደት ነገረን ፡፡

መ.ጻድቅ አዝለፈ ሰብሖ፤ ጻድቅ ምስጋናን አዘወተረ፡፡

ሠ. ዜነወ ገብርኤል ዜና ሠናየ በእንተ ልደቱ ለወልደ አብ፤ ገብርኤል ስለወልደ አብ ልደት መልካም ዜናን ነገረን፡፡

፫. ዘርፍነት፡- ዘርፍ የሚባለው በዐረፍተ ነገር ውስጥ ባለንብረትነትን፣ ባለሀብትነትን የሚያመለክት ነው፡፡ አንድ ስም በዐረፍተ ነገር ውስጥ ዘርፍ ለመሆን የሚከተሉትን ሕጎች ማሟላት አለበት፡፡ ሀ. እንተ፣ ዘ፣ እለ፣ ለ፣ የሚባሉትን አገባቦች በመጠቀም ነው፡፡ ምሳሌ፡- ወንጌል ዘዮሐንስ፣ ዘጊዮርጊስ እድ፣ እለ ሐዋርያት አግብርት፣ እንተ ጳውሎስ ረድእ ወዘተ ለ. ከሚዛረፈው ቃል ጋር መዛረፍ አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ግን የሚዛረፈው ቀድሞ ዘርፍ የሚሆነው ተከትሎ መምጣት አለበት፡፡ ምሳሌ፡- ክንፈ ገብርኤል፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ጸሎት፣ ኃይለ ሚካኤል ወዘተ ውድ አንባብያን በሚከተለው ቅኔ ያሉትን ስሞች በመዘርዘር ሙያቸውን እንመልከት፡፡

ዘአምላኪየ

ትምህርት አልቦሙ ለሰብአ ሮምያ ቀደምት፤

ቁልቁሊተ እስመ አኀዝዎ ለጴጥሮስ ዳዊት፤

ወሰሐቁ ቦሙ አርድእተ ጴጥሮስ ገድላት፡፡

ቀደምት የሮምያ ሰዎች ትምህርት የላቸውም፤

ጴጥሮስ ዳዊትን ወደ ታች (ዘቅዝቀው) ይዘውታልና፡፡

የጴጥሮስ ተማሪዎች ገድላትም ሳቁባቸው፡፡

ባለቅኔው በዚህ ቅኔ ውስጥ ለመግለጽ የፈለጉት ማንበብ የማይችሉ ሰዎች አርእስትና ሕዳግ ስለማያውቁ ዳዊቱን (መጽሐፉን) ዘቅዝቀው ይይዙታል፡፡ ይህን የተመለከቷቸውም ሁሉ ይስቁባቸዋል፡፡ ይህ ሰሙ ሲሆን ወርቁ ደግሞ በሮም የሚኖሩት ከሓድያን ቅዱስ ጴጥሮስን ዘቅዝቀው መስቀላቸውንና የቅዱስ ጴጥሮስም ተጋድሎ ቅዱስ ጴጥሮስን በሥጋ ቢያሰቃዩትም ሰማያዊውን ክብር እንደሚያሰጠው ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ቅኔ ያሉት ቃላት በእያንዳንዳቸው ሙያ አላቸው፡፡

ስሞች፡- ትምህርት፣ ሰብእ፣ ሮምያ፣ ጴጥሮስ፣ ዳዊት፣ አርድእት፣ ጴጥሮስ፣ ገድላት ትምህርት የቅኔ ባለቤት፣ ሰብእ የማድረጊያ (ለ) ባለቤት

ሮምያ ዘርፍ

ጴጥሮስ ዳዊት ተመስሎ ተሳቢ (ቀጥተኛ ተሳቢ)

አርድእት፣ ገድላት ተመስሎ ባለቤት ነው

ጴጥሮስ ዘርፍ

ማስታወሻ ዘርፍ የሆኑትን ስንመለከት ሰብአ ሮምያ፣ አርድእተ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ ሁለቱም ተናበዋል፡፡ የተናበቡትም  ዘርፍ የሚሆነውን ቃል ተከትሎ ነው፡፡

ተሳቢ የሆኑትንም ስንመለከት “ለ” የወደቀበት፣ ነው፡፡