“ስለ ወንጌል እተጋለሁ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ተከፈተ

                                                                                                                በእንዳለ ደምስስ

በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን “ስለ ወንጌል እተጋለሁ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የማኅበሩ አባላትና ምእመናን በተገኙበት ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ስድስት ኪሎ በሚገኘው የስብሰባ ማእከል ተከፈተ፡፡

ዐውደ ርእዩ ከሰኔ ፲፬ – ፲፮ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ኬንያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የአውስትራልያና የኒውዚላንድ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎተ ወንጌል በማድረስ በይፋ ከፍተውታል፡፡

በዐውደ ርእዩ ክፍል አንድ “ቅዱስ ወንጌል ለሁሉ” በሚል የቀረበ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት?የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማ፣ ወንጌል ማስፋፋት ነው፣ የወንጌል መስፋፋት መገለጫዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ተዳሰውበታል፡፡

የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም የግብጽ፣የሕንድና የሩሲያ ተሞክሮ በክፍል ሁለት ቀርቧል፡፡አማኞቻቸውን ማጽናት መቻላቸው፣ ከተከላካይት አልፈው የተሻለ ተቋማዊ አቅም መፍጠር መቻላቸው ዛሬ ለደረሱበት አስተዋጽኦ ማድረጉ እንደ ተሞክሮ መታየት እንደሚገባው ተገልጿል፡፡እንደ ምሳሌም በመገናኝ ብዙኃን  ደረጃ ግብጽ ፲፬ የቴሌቪዥን፣ ፲፻፬፻ ድረ ገጾች፣በሕንድ ፰፣በሩሲያ ፭፻ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ዘርፍ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት ያሳየ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አንጻር ከእኛ ምን ይጠበቃል? በሚለው ትእይንት የተጀመሩት የቴሌቪዥንና የድረ ገጽ አገልግሎቶችን ማጠናከርና ማስፋፋት፣ በስብከተ ወንጌል ላይ የሚሠሩ አካላትን ማጠናከር፣ የአስኳላ ትምህርት ቤቶችን በስፋት መከፈትና ትውልድን ማነጽ፣እንዲሁም ሌሎች በስብከተ ወንጌል ዙሪያ የተቀናጀ አገልግሎት ለማበርከት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በትዕይንቱ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

“ቤተ ክርስቲያን በመጪው ዘመን ምን መሆን አለባት” የሚለው ትዕይንት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የሚያስችሉ መልካም ዕድሎችን፣ ፈተናዎች እንዲሁም መፍትሔ ሰጭ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነበር፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በጠረፋማ አካባቢዎች የሚያካሔደውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተመለከተም በደቡብ ኦሞ፣ የቤንች ማጂ እና የመተከል አህጉረ ስብከት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንደምሳሌ ቀርበዋል፡፡ ከአንድ መቶ ሰባ ሺሕ በላይ አዳዲስ አማንያንን ማስጠመቅ እንደተቻለም ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የአውስትራሊያ እና የኒውዚላንድ አህጉረ ስብክት ሊቀ ጳጳስ ዐውደ ርእዩን ከተመለከቱ በኋላ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክትም “ወንጌል የሚለው ሐሳብ ሰውን ማዳን ነው፡፡ አባላት መሰብሰብ፣ ማብዛት ማለት አይደለም፡፡የሰውን ልብ ማግኘት፣ የእግዚአብሔርንና የሰውን ልብ ማያያዝ፣ በሌላ መልኩ ማዳን ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ስለ ዐውደ ርእዩ ብጹዓን አባቶች አስተያየታቸውን በጹሑፍ ሲያስቀምጡ

ብፁዕነታቸው ኦርቶዶክሳዊነት ላይ በማተኮር “ኦርቶዶክሳዊነት ዝም ብሎ በአንድ ጊዜ የሚጠፋ ወይም በአንድ ጊዜ የተገኘ ነገር አይደለም፡፡ ክርስትና ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስካለንበት ጊዜ ድረስ በመንፈሳዊ  ሐረገ ትውልድ ተያይዞ የመጣ ዕንቊ የሆነ ነገር ነው፡፡ ይህንን ትውልዱ መቀበል ከቻለ ዓለምን ማዳን ይችላል፡፡” ብለዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ እሰከ ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣በየዕለቱ ትምህርተ ወንጌል፣ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ዶክመንተሪ ፊልሞች ይቀርባሉ፡፡