pro.bya yemame

ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ምን ይላሉ?

ታኅሣሥ  4 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ዕረፍት ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀጣዩ ፓትርያርክ ማንነት እያነጋገረ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቀጣዩ ፓትርያርክ አሰያየም ሂደትና ቀጣዩ ፓትርያርክ የሚጠብቃቸው ሓላፊነቶች በተመለከተ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ውይይት አድርገናል፤ የሰጡንን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

 

ፕሮፌሰር ባዬ ይማም

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ


የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በሞት ሲለዩ ማን ይተካቸዋል? የሚተኩት አባት እንዴት ይመረጣሉpro.bya yemame? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም፡፡ ከተነሣ ደግሞ የምርጫ መስፈርት ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከአሁን በፊት ቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ መርጣ የምትሾምበት ሥርዐት ካላት፤ ያ ሥርዐት አሁንም በተግባር መዋል አለበት፡፡ ምናልባት አዲስ የመምረጫ መስፈርት ማውጣት የሚያስፈልግ ከሆነ፣ ሲኖዶሱ ተጨማሪ መስፈርት ሊያወጣ፣ ያሉትን መስፈርቶች ሊያሻሽል የሚችልበት ሥልጣን አለው፡፡ በዚህም መሠረት ምርጫው ይከናወናል፡፡

 

በፓትርያርክ ምርጫው ላይ ምእመናን አስተዋጽኦዋቸው ምን ይሆናል የሚለውን ስንመለከት፦ ቤተ ክርስቲያኗን የሚጠብቅ፣ ምእመናኑን የሚያስተምሩ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን በልማት ማሰለፍ የሚችሉ መልካም አባት እንዲሰጠን በጾም፣ በጸሎት እግዚአብርሔርን መለመን ከምእመናን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ይህን ከመፈጸም ባለፈ በአደባባይ ወጥቶ እገሌ ይጠቅመናል ይሾምልን፣ እገሌ ይጐዳናል አይሾም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

 

የምሁራኑንም አስተዋጽኦ ስንመለከት፦ ምሁራኑን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ እነዚህም ዓለማዊ ምሁራንና መንፈሳዊ ምሁራን /ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን/ ናቸው፡፡ ዓለማዊ ምሁራን ሆነን በተለያየ የሙያ መስክ የምንገኝ፣ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የሆን፣ የነፍስ አባትም ያለን አለን፡፡ እንደ ባለሙያ ዜጋ ቤተ ክርስቲያኗ የእኛም ስለሆነች የእርሷን ደኅንነት፣ የእርሷን አመራር በሚመለከት አሳብ መስጠት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፦ ምሁራኑ በቤተ ክርስቲያኗ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ በማማከር ወዘተ በሙያቸው አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ምርጫውን በሚመለከት ግን የምሁራኑ ተሳትፎ ይፈለጋል ተብሎ ከምሁራኑ መካከል ተጠቁመው በምርጫው ሂደት ላይ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ሁኔታ ካለ፤ እዚያ ላይ ሊሳተፉ  ይችላሉ፡፡ ከሌለ ግን በየሙያ መስካቸው ከቤተ ክርስቲያኗ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ መልኩ በልማቱ፣ በትምህርቱ በኩል አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

 

መንፈሳዊ ምሁራን /ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን/ ግን ለየት ያለ ሓላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የፓትርያርክ ምርጫ እንዴት ብሎ መፈጸም እንዳለበት ድምፃቸውንም የበለጠ ሊያሰሙ ይገባል፡፡ በአጥቢያ የሰበካ ጉባኤያት የአሳብ፣ የተግባር አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከምርጫው በፊት፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለያየ ምክንያት ሳይበታተን በአንድነት በጾም፣ በጸሎት ተወስኖ እግዚአብሔር መልካሙን አባት እንዲሰጠን መጸለይ፣ ምርጫው የተሳካ እንዲሆን፤ ሊያስተምሩ፣ ሊመሩ፣ ሊወቅሱም፣ ሊያሞግሱም ይገባል፡፡ ከውጭ ተመልካች ሳይሆኑ፤ ከውስጥ ሆነው በሲኖዶሱ አካባቢ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ የመምከር፤ የማማከር ሓላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ከምርጫውም በኋላ ተመራጩን አባት በሚመለከት በሕዝቡ ዘንድ ብዥታ እንዳይኖር፣ ልዩ ልዩ ወሬ ለሰማው ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ የመስጠት፣  የተመረጠውን አባት ተቀብሎ በአዲስ መንፈስ በየሀገረ ስብከታቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ከተመረጡ በኋላ የሚጠብቋቸው ተግዳሮቶችንም በሁለት በኩል ማየት ይቻላል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ሕዝበ ክርስቲያኑን የመምራት፣ የማስተማር፣ የማቀራረብ ለልማት የማስተባበርና የማሰለፍ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ ከአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ጀምሮ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ባለው መዋቅር በልማቱም፣ በመንፈሳዊ ትምህርቱም፣ በአመራሩም አሳብ እንዲንሸራሸርና ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምእመኑን ድርሻ ምን እንደሆነ ማሳወቅ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በተዋረድ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ሕዝቡን ማንቀሳቀስ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን በሀገር ውስጥም፣ ከሀገር ውጭም አገልግሎቷን ማስፋፋት፣ ማጠናከር፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን መሰባሰብ፣ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዓለም የማስፋፋትና ትምህርቱን የማዳረስ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የለውጥ ሂደት እንቅስቃሴ ውስጥ እየገባች ስለሆነ፤ በተጀመሩት የልማት መስመሮች ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዴት ሊሰለፍ ይችላል? ቤተ ክርስቲያኗ በትምህርቱ፣ በጤናው፣ በማኅበራዊ ዘርፍ የድርሻዋን ለመወጣት፣ የተጀመረውን የማስፈጸም ሓላፊነት ያለባት ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ የሚመረጡት አባትም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱም ይህን ማቀናጀትና መምራት ትልቅ ሓላፊነት ያለባት ይመስለኛል፡፡

 

በሀገር ውስጥና በውጭም በሚገኙ አባቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታትም ይጠበቅባቸዋል፡፡ እኔ በግሌ በአባቶች መካከል ይህ ሁኔታ መፈጠሩ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሲኖዶስ፤ ሕዝቡም እንዲሁ በሁለት፣ በሦስት መከፋፈሉ እጅግ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሁለት ሲኖዶስ ለምን አስፈለገ? ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኗ ለሁለት ተከፍላለች ማለት ነው? ሕዝበ ክርስቲያኑም ለሁለት ተከፍሏል ማለት ነው? ከውስጥና ከውጭ ሲኖዶስ ለመፈጠሩ ምክንያቱ ምንድን ነው? ብሎ አጥንቶ ምንጩን ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱ መካከል የተፈጠረው ክፍተት የዶግማና የቀኖና ሳይሆን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳይ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን ሊከፍላት አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድ ናት፡፡ ሊኖራት የሚገባው አንድ ሲኖዶስ ነው፤ ሊኖራት የሚችለውም አንድ አባት ነው፡፡ ሊኖራት የሚችለው አንድ ሕዝበ ክርስቲያን ነው፡፡ ሁለት፣ ሦስት ብሎ ነገር አይታየኝም፡፡ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በአሜሪካም፣ በአውሮፓም … ያሉት ማእከላዊነቱን ጠብቆ በአንድ ሲኖዶስ በሚሰጠው መመሪያ በልማት፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ ሊሆኑ ይገባል፡፡

 

ሁለቱንም አባቶች /ከሀገር ውስጥም ከውጭም ያሉትን/ ወደ አንድ እንዴት ይምጡ የሚለው የእኛ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ሁለት ፓትርያርክ ሳይሆን አንድ ትርያርክ ይኑር፤ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ወይም ሁለቱ ተማክረው አንድ ይሁኑ የሚለው አሳብ ከራሳቸው ከውስጣቸው ከሃይማኖታዊ ግዴታቸው ቢመጣና አንድ ቢሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ምእመኑ «አንተም ተው፤ አንተም ተው» ብለው ማስማማት መሞከራቸው  ተገቢ አይደለም፡፡ እኛ ተመሪዎች ነን፡፡ መሪዎቻችንን «ኑ ታረቁ፤ አንድ ሁኑ» ለማለት ሥልጣኑ አይፈቅድልንም፡፡ ሥልጣኑ ያለው በአባቶቻችን ስለሆነ፤ መታረቅም፣ መመካከርም የእነርሱ ፈንታ ነው፡፡ እኛ የምንችለው እግዚአብሔርን በጸሎት መለመን ነው፡፡ እነርሱ አንድ ሆነው ሕዝቡን አንድ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ አንድ ሲኖዶስ እዚህ፣ አንድ ሲኖዶስ እዚያ፤ አንድ መሪ እዚህ፣ አንድ መሪ እዚያ በማለት ሕዝቡን መበታተን ለማንም አይጠቅምም፡፡ መንግሥትም በዚህ ላይ የሚያገባው ይመስለኛል፤ ዝም የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ሕዝበ ክርስቲያኑን በአንድነት ለልማት እንዲነሣሱ ለማድረግ አቅሟን ማጐልበት አለባት፡፡ አሁን አንዳንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሽ እያጡ ካህናቱ ወደ ከተማ እየፈለሱ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ወደፊት ቤተ ክርስቲያን ከአገልጋይ ካህናት እጥረት የተነሣ የምትዘጋበት ሁኔታ እንዳይመጣ ከላይ እስከታች ድረስ ማእከላዊነቱን የጠበቀ አሠራር ልትዘረጋ ይገባል፡፡ አንዱ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ ገቢ ኖሮት ሌላው ቀዳሽ አጥቶ የሚዘጋበት ሁኔታ እንዳይኖር ትክክለኛና ፍትሐዊ የሆነ አሠራር መኖር አለበት፡፡

 

ስለዚህ አዲስ የሚመረጡት ፓትርያርክ ይህን ተገንዝበው በከተማም በገጠርም ያለችው ቤተ ክርስቲያን የልማቱ፣ የማንኛውም ነገር እኩል ተሳታፊ፣ እኩል ተጠያቂ፣ እኩል ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ አለባቸው፡፡ ተግዳሮቱም ይህ ይመስለኛል፡፡ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ትልቅ የልማት መስመር በየአቅጣጫው ዘርግታ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ከምታደርገው የበለጠ እንቅስቃሴዋን ማሳየት አለባት፡፡ እንቅስቃሴውን ለማሳየት ደግሞ ሕዝበ ክርስቲያኑን አንድ አድርጋ በማሰባሰብ በአንድ ሲኖዶስ፣ በአንድ አባት መምራት መቻል አለባት፡፡

 

«ለእርቅ፣ ለፍቅር ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው»

ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ


dr.yeraseworke ademasaየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ልትመርጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያ ያለኝ አስተያየት አሜሪካን ሀገር ያለውን ወገንና በዚህ መደበኛው ወይም ዕውቅና ያለውን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን ሲኖዶስ የሚመ ለከት ነው፡፡ ዋናው እዚህ ያለው ነው፡፡ እነኚህ ሁለቱ እኩል ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የአንድ እምነት ተከታዮች እስከሆኑ ድረስ በውጭ ሀገር የሚገኘው የተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናትን ያቀፈ ቢሆንም፤ ሁለቱም አንድ የክርስቶስ ቤተሰቦች ስለሆኑ ለእርቅ፣ ለፍቅር ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡

 

ታላቅ የሆነው ወንድም ታናሹን ወንድም ወደ አንድ አባታቸው ቤት እንዲመለስ፤ አብረው እንዲሆኑ የተቻለውን ቢያደርግ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ከምርጫው በፊት የግድ ማለቅ የለበትም፤ ከምርጫው በኋላም የግድ መሆን የለበትም፡፡ ከምርጫው በፊት እርቅ መካሄድ አለበት ማለት ለዚያኛው ዕውቅና መስጠት ይሆናል ይህም አያስኬድም፡፡ ስለዚህ የተሻለ የሚሆነው ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው የሚካሄደው በሀገር ውስጥ በቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ምርጫው ከማለቁ በፊትም ሆነ ከአለቀም በኋላ ቢሆን፤ ያንን ወገን ወደዚህ ለመሳብ የሚቻለውን ሁሉ አድርጐ ቅሬታቸውንም አዳምጦ የቤተ ክርስቲያኑን አንድነት ለመመለስ ማንኛውንም ሙከራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 

በምርጫው ወቅትም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ለምርጫ የሚቀርቡት አባቶች በቤተ ክህነት አካባቢ ያሉ ናቸው፤ አቋማቸው ይታወቃል፡፡ የሚመረጡት አባት ከዚህ በፊት በነበራቸውና አሁንም ባላቸው አቋማቸው ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አገልግሎት ይሰጣሉ? ይህችን ቤተ ክርስቲያን ይታደጓታል ወይ? ይህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ችግር ይፈታሉ ወይ? ይህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ መጥፎ አዝማሚያዎችን ያርሟቸዋል ወይ? ቤተ ክርስቲያኒቱ በፊቷ ተደቅነው ያሉ ተግዳሮቶችን እልፍ የሚያደርግ ርዕይ ያላቸው ናቸው ወይ? ቁርጠኝነት ያላቸው ናቸው ወይ? ለማንኛውም ወገን ቢሆን ከትክክለኛው መንገድ ውጪ የሆነ ወገናዊነት የሚያሳዩ ሰው አይደሉም ወይ? የሚሉት ነጥቦች መታየት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዋናው መሪ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የዴሞክራሲ ጨዋታ አይደለም ያለው፡፡ ስለዚህ አንድ አባትን ቅዱስ ሲኖዶስ መረጠ ማለት፤ ከአሁን በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት /ዐሥርት ዓመታት/ አንድ ዓይነት አመራር የሚሰጡ አባት ተመረጡ ማለት ስለሆነ፤ ምርጫው ላይ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ይህ ጥንቃቄ ሊኖር የሚችለው ግልጽ የሆነ ውይይት ሲኖር ነው፡፡ ግልጽ የሆነ ውይይት የሚያስፈልገው የመጀመሪያው በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ልክ  አሁን ሐመር መጽሔት በጀመረችው የውይይት መድረክ ላይ በመሳተፍ አስተያየቶችን በመስጠት ነው፡፡ እንዴት ዓይነት አባት እንምረጥ የሚለውን መነጋገር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

 

ሌላው ሊታወቅ የሚገባው በዚህ ምርጫ ላይ ከጳጳሳት ጀምሮ እስከ ምእመኑ ድረስ ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጽኦዎች በየደረጃቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ ጳጳሳቱ በሲኖዶሱ ውስጥ መድረክ አላቸው፡፡ እንደውም መጨረሻ ላይ እነርሱ ናቸው መራጮች፡፡ የምእመናኑ አስተዋጽኦ ጸሎትና ምህላ መያዝ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ግልጽ የውይይት መድረክ ካለ፤ በዛ መድረክ አማካኝነት «እንደዚህ ያለ ሰው ይሁንልን፣ እንደዚህ ያለ ሰው ቢሆን ቤተክር ስቲያንንም ምእመናኑንም ይጠቅማል» ብለው በግልጽ ሰውየውን ራሱን ሳይሆን የቆመለትን ዓላማና የሚያንጸባርቀውን ጠባይ በመግለጽ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡

 

የምሁራኑንም አስተዋጽኦ ስንመለከት፦ ምሁራኑን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት የሚያውቁ ተሰሚነትና ዕውቀትም ያላቸው መንፈሳዊ ምሁራን  አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የሆኑ ልዩ ልዩ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ዓለማዊ ምሁራን አሉ፡፡ በተለይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የአሁኑ የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው፡፡ የአሁኑ ዘመናዊ ትምህርት እየተስፋፋበት ሁሉም ልጆች ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የሚሄዱባት ኢትዮጵያ፣ ወደፊት የሕዝቧ ብዛት አንድ መቶ ሠላሳ ሚሊዮን፤ የከተማ ነዋሪዋ ወደ ሠላሳ ሚሊዮን የሚያድግ ኢትዮጵያ፣ ዜጐቿ ቀለም መማር ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚችሉ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ያላቸው ዜጐች የሚኖሯት ናት፡፡ ይሄን የመዘመን ተሽከርካሪ ማንም ሊያቆመው የማይችል በመሆኑ ከዚህ ጋር ለመሄድ ራስን ማስተካከል ስለሚያስፈልግ ያንን ሥራ ላይ የሚያውል አመራር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን አመራር በአሳብ ሊደግፉ የሚችሉ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ምሁራን ግን የቤተ ክርስቲያናችንን ፍላጐትና የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር የራሳቸው ያደረጉ ምሁራን አሉ፡፡ ቀደም ሲል ሃይማኖተ አበው የሚባል በጥቂት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቋቋመ ማኅበር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን አለ፡፡ እነኚህ የድሮውንና ዘመናዊ  ያደረጉ ምሁራን ይመስሉኛል፡፡ ቀደም ሲል ሃይማኖተ አበው የሚባል በጥቂት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቋቋመ ማኅበር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን አለ፡፡ እነኚህ የድሮውንና ዘመናዊውን፤ ቀደምቱንና ዘመናዊውን ለማያያዝ የሚጠቅሙ ሰንሰለቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምሁራን በፓትርያርክ ምርጫ ውይይት ውስጥ እንደ አስፈላጊነቱ ቢሳተፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ፡፡ ይህንንም ስል ምሁራን ስለሆኑ ይበልጥ ተደማጭ መሆን አለባቸው ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ምሁርነታቸው ጠቃሚ የሆነ አሳብ ማቅረብ ስለሚችሉ ነው፡፡

 

ፓትርያርኩ ከተመረጡም በኋላ ብዙ የሚጠብቋቸው፣ ማስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ውጪ የሆኑ ከጐንና ከጐን የገቡ አንዳንድ ነገሮችን ማረምና ማስተካከል አለባቸው፡፡ ለምሳሌ- ብዙ ነገር ሥነ ሥርዐትም ሥርዐትም ያንሰዋል፡፡ የሰው ኃይሉ፣ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚሰጠው ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ወዘተ  ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

መቃብር ባሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት በአንዳንድ ቦታዎች መቃብራት እየተነሡ ለገቢ ማስገኛ ተብሎ ሕንፃ እየተሠራበት ነው፡፡ መሠራቱ ጥሩ ቢሆንም ሕዝቡ የሚቆምበት ቦታ መኖር የለበትም) በአንዳንድ ቦታዎች የሚሠሩ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናትም እጅግ በጣም ትልቅ የሆኑ ከአቅም፣ ከትውፊታችን ጋር የማይያያዙ አሠራሮችን እየተመለከትን ነው፡፡ ይሄ መቅረት አለበት፡፡ ከዚህ ይልቅ ልክ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም እንደሠሩት ዓይነት ትምህርት ቤት ማነፅ ይገባቸዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች የቀድሞውን ምሁራዊ እሴት ያልዘነጉ ልጆች በብዛት ለማውጣትና እነኛን ልጆች ለከፍተኛ ትምህርት ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡ ዛሬ በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ለገቢ ማስገኛ ከሚሠሯቸው ቤቶች ይልቅ እንደዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች ቢሠሩ ሁለት ጥቅም ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው ገቢ ያስገኛል፤ አንደገና የወደፊት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ተከታዮች፣ ደጋፊዎችን ማፍራት ይቻላል፡፡

 

ሌላው ካህናቱን ስንመለከት ምን ያህል ለድኻው የቆሙ ናቸው? እንዴት ነው ድኻውን የሚያጽናኑት? የድኻ ቤተሰብ ሰው ሲሞትበት አሳዛኝ በሆነ መንገድ ስንቱ ነው የሚሄደው? በተለይ በአሁኑ ዘመን እኮ ሰው «የቦሌ ቄስ፣ የእንትን ቄስ …» እያለ መቀለድ ጀምሯል፡፡ ካህናቱን የሚስባቸው ዘመናዊ ነገር ነው፡፡ ገንዘብ ያለው፣ የለቲካ ሥልጣን ያለው … እና ለድኻው የሚሰጠው አገልግሎት ይለያያል፡፡ ስለዚህ ብዙ የሚታረሙ ነገሮች አሉ፡፡

 

ፓትርያርኩም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ትልቅ ሓላፊነት ለመወጣት በመጀመሪያ ደረጃ የፓትርያርኩ ቢሮ ክፍት ሆኖ ከልዩ ልዩ አቅጣጫ የሚመጣውን አሳብ መቀበል አለበት፡፡ የፓትርያርኩ ቢሮ መቀበል ያለበት እንደዚህ ያለውን እንጂ፣ ዳቦ፣ ኬክ አስጋግረው የሚመጡ  ባልቴቶችን ማስተናገድ የለበትም፡፡ ልዩ ልዩ ተቃራኒ የሆኑ፤ ከእነርሱም የሚቃረን አሳብ ማዳመጥ አለባቸው፡፡ ሁለተኛው እርስ በርስም በውይይት ነገሮችን በሚገባ፣ በዝርዝር እየተወያዩ የተማመኑበትን በሥራ ላይ ማዋል አለባቸው፡፡ ፓትርያርኩ መሪ ነው የሚሆኑት፤ የፓትርያርኩን አሳብ አዳምጦ ያንን አሳብ አሰላስሎ ለብዙኃኑ የሲኖዶስ አባላትና ሌሎች በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለእነርሱ አቅርቦ አሳምኖ ፖሊሲ አውጥቶ ያንን ማስፈጸም መቻል አለበት፡፡ በዚህ ውስጥ ዝምድና፣ ወዳጅነት የመሳሰለው ነገር መጥፋት አለበት፡፡ በተለይ አሁን የተማረው ሰው ቤተ ክህነትን እንደጦር ነው የሚፈራው «ወይ እነርሱ» ነው የሚለው፤ ተጠራጣሪ፣ ምቀኛ… የሆኑ ሰዎች ዋሻ ነው ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ይህን አተያይ ለመፋቅ፣ ለማስወገድ መጣር አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ ግልጽ ሆነው ሲያደምጡ ነው፡፡ ስለዚህ ፓትርያርኩም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንና ሌሎችም ክፍተቶች ለመሙላት ትልቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡

 

«አንድ  ሆናችሁ ቤተክርስቲያናችንን ምሩ»

ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ


በአሁኑ ወቅት ሊደረግ ስለታሰበው የፓትርያርክ ምርጫ  አስተያየት ከመስጠቴ በፊት፤ ያለፉት አምስት ፓትርያርኮች አመራረጥ ሂደት ምን ይመስል እንደ ነበር ለግንዛቤ እንዲረዳን እርሱን ላስቀድም፡፡

 

dr.wedue tafeteእስከ አሁን ድረስ የተመረጡት አምስት ፓትርያርኮች በሦስት የተለያዩ  መንግሥታት፤ በዘውዳዊው አገዛዝ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለት፣ በወታደራዊው ደርግ ሁለት፣ አሁን ባለው በኢሕአዴግ መንግሥት አንድ ፓትርያርክ ተመርጠዋል፡፡ የመጀመሪያው ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ሲመረጡ ለፓትርያርክነት ለመምረጥ ውድድር አልተካሄደም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ «አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው እንዲሾሙልን» ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ፡፡ አቡነ ባስልዮስ ከዐረፉ በኋላ ፓትርያርክ ለመምረጥ ዝግጅቱ አምስት ወራት ፈጅቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የወጣው ሕግ  «ከእንግዲህ በኋላ ፓትርያርክ ቢሞት ምርጫው በዐርባ ቀናት ውስጥ መፈጸም አለበት» የሚል ድንጋጌ ይዟል፡፡ በወቅቱ የቀረቡት ሦስት እጩዎች  አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ያዕቆብና አቡነ ጢሞቴዎስ ነበሩ፡፡ ከ156 መራጮች ውስጥ አቡነ ቴዎፍሎስ በ123፣ ድምፅ ማግኘት ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ፡፡ የምርጫውን ውጤት በቅድሚያ የሰሙት ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ፡፡ እርሳቸው ካጸደቁት በኋላ የምርጫው ውጤት ይፋ ሆነ፡፡

 

በደርግ ዘመነ መንግሥት አቡነ ቴዎፍሎስ ሲታሰሩ ሁለት ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ሲኖዶሱ የራሱን ኮሜቴ አቋቋመ፣ በመንግሥት በኩል በዶ/ር ክነፈ ርግብ የሚመራ የቤተ ክርስቲያን ጊዜያዊ ኮሚቴ የሚል ተቋቋመ፡፡ ፓትርያርክ ለመምረጥ ሁለት ኮሚቴ አስፈላጊ ባለመሆኑ፤ ሁለቱ ተነጋግረው አንድ ኮሚቴ ተዋቀረ፡፡ ኮሚቴውን የመሩት የጊዜያዊው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዶ/ር ክነፈ ርግብ ነበሩ፡፡ ይህ የተደረገበት ምክንያት መንግሥት ድርጊቱን መቆጣጠር ስለሚፈልግ ነበር፡፡ ለምርጫው አምስት ጳጳሳት ቀረቡ፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ከነበሩት 555 ወረዳዎች ውስጥ ሁለት፣ ሁለት መራጮች እንዲወከሉ ተደረገ፡፡ ምርጫው ሲካሄድ የሚታዘቡ ሁለት የደርግ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የነበሩትና፤ በኋላም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር አክሊሉ ሀብቴም ተገኝተው ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎች መንግሥትን በመወከል የተገኙ ነበሩ፡፡ ከ1049 መራጮች ውስጥ በ809 ድምፅ አባ መላኩ ተመረጡ፡፡ በወቅቱ ከቤተ ክርስቲያንም፣ ከመንግሥትም «ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ የዴሞክራቲክ ምርጫ» ተብሎ ተነገረ፡፡ አባ መላኩም ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተባሉ፡፡

 

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲያርፉ እንደገና ምርጫ ተደረገ፡፡ በዚህም ሦስት ተመራጮች አቡነ ሳሙኤል፣ አቡነ ገሪማና አቡነ መርቆሬዎስ ቀረቡ፡፡ 109 መራጮች የመረጡ ሲሆኑ፤ መንግሥትን በመወከል በምርጫው የተገኙት የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ዲበኩሉ ዘውዴ ነበሩ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ፡፡ ኋላም አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ስደት ሲሄዱ ምርጫ ተካሄደ፡፡ ከዚያ በፊት በስደት ላይ የነበሩት አባ ጳውሎስ ተመረጡ፡፡

 

ስለዚህ እዚህ ላይ ማየትና ማወቅ የሚገባን በሦስቱም መንግሥታት ፓትርያርክ ከተመረጡ በኋላ መንግሥት እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡ በምርጫው የሚስማማ ወይም የማይስማማ መሆኑን ለማወቅ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የመንግሥት ይሁንታ ደግሞ አስፈላጊ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ነው እስከ አሁን ድረስ በተደረገው የፓትርያርክ ምርጫ የመንግሥት እጅ አለበት የሚያሰኘው፡፡ ስለዚህ በንጉሡ፣ በደርግ ጊዜም ሆነ አሁን ባለው መንግሥት፤ መንግሥት ሳያውቀው የሚደረግ የፓትርያርክ ምርጫ ይኖራል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

 

ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ እንደሚከተለው እገልጻለሁ፡፡ አቡነ ባስልዮስ ዐርፈው አቡነ ቴዎፍሎስ ሲሾሙ የወጣው ሕግ አሁን ይሠራል? ወይስ ከዛ በኋላ ሕጉ ተሻሽሏል? መራጮች ሊሆኑ የሚገባቸው እነማን ናቸው? ጳጳሳት ብቻ የቤተ ክርስቲያን አና የገዳማት መምህራን ናቸው? ምእመናን ይሳተፉበታል? የምንመርጠው ምን ዓይነት አባት ነው? የሚለውን ነገር ማየት አለብን፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ፈተና ውስጥ ያለችበት ወቅት ነው፡፡ ይህን ፈተና ለማለፍ ምን ዓይነት ስትራቴጂ፣ ምን ዓይነት የአመራር ዘዴ ቀይሶ ወደሚቀጥለው ጊዜ ለማስተላለፍ ምን ይደረግ? የሚ ሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዛሬ የአስተዳደር ችግር፣ ከተለያዩ ሃይማኖቶች የሚመጡ ችግሮች አሉ፡፡ ተመራጩ አባት ቤተ ክርስቲያን ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፉ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርጉ፣ ሃይማኖቷን የሚያስፋፉ፣ ምእመናንን የሚጠብቁ፣ እገሌን ከእገሌ የማይከፋፍሉ፣ አባት መሆን አለባቸው፡፡

 

ሌላው መታየት ያለበት ተመራጩ ፓትርያርክ ትምህርት አላቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ትምህርት ስል ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት በተጨማሪ ዘመናዊ ትምህርት አላቸው? ከሌላው ዓለም ጋር ይተዋወቃሉ? የሚለውንም ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አባል ናት፡፡ በውጭ ትወክላለች፡፡ አቡነ ጳውሎስ ምን ምን ዓይነት ሹመት እንደነበራቸው እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ከሌላው ዓለም ጋር የሚያስተዋውቁን፤ ቢያንስ አንድ የውጭ ቋንቋ የሚያውቁ አባት ቢሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ላላት ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ጠቃሚ ይሆናል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡

 

ይህች ቤተ ክርስቲያን ከደርግ ጊዜ ጀምሮ  በሁለት እንደተከፈለች አድርገን መቁጠር እንችላለን፡፡ በውጭ ሀገር ስደተኛ ሲኖዶስ አለ፡፡ ከዚህ ቀደም ፓትርያርክ የነበሩ ሰው አሉ፤ ስደተኛ ሲኖዶስ መርጦ የሾማቸው ጳጳሳት አሉ፡፡ እኛ ነን ትክክለኛዋ የቤተ ክርስቲያን አመራር የሚሉ ፓትርያርክም ሲኖዶስም ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ ይሄ መከፋፈል ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አይጠቅምም፡፡ ውጭ ሀገር ስንሄድ በስደተኛው ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፤ አዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከሁለቱም ያልወገኑ ገለልተኛ የሆኑ አሉ፡፡ ይሄ መከፋፈል መቼ ይቆማል? እንዴት ወደ ሰላም መምጣት እንችላለን? እርቅ ተጀመረ እንጂ፤ ምን ተነጋገሩ? ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ አይሰማም፡፡ እርቁን ተግባራዊ ለማድረግ እዚህ የሚመረጡት ፓትርያርክ ብቻ ሳይሆኑ፤ እዛ ያሉትም ሰዎች በቅንነት ይህችን አሐቲ ቤተ ክርስቲያን ለምን እንከፋፍላታለን? ብለው ወደ እርቅ ለመምጣት መሞከር አለባቸው፡፡ አንድ ሰው እጁን ዘርግቶ አየተራመደ ለእርቅ ሲጠራ፤ ሌላኛው እየሸሸ እጁን አጥፎ የሚቀመጥ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ የሩሲያን ቤተ ክርስቲያን ብንመለከት እ.ኤ.አ. 1917 በተካሄደው አብዮት ለሁለት ተከፍላ፣ ለረጅም ጊዜ ተለያይተው ነበር፤ አሁን ግን ታርቀዋል፡፡ የእኛም ቤተ ክርስቲያን የማትታረቅበት ምክንያቱ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም በውጭ ያሉትን አሻግሮ መመልከት ሳይሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት  አለባቸው፡፡ ይህንን የሚያደርግ አባት ይህች ቤተ ክርስቲያን የምትፈልግበት ወቅት አሁን ነው፡፡

 

ዛሬ በገጠሪቷ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ አባቶች እየቸገራቸው ወደ ከተማም ከዚያም ከኢትዮጵያ ውጭ እየተሰደዱ ነው፡፡ ካህናቱና መነኮሳቱ እንደ ዓለማዊ ሰው ኑሮአቸውን ለማሻሻል ውጭ ሀገርን እየተመለከቱ ነው፡፡ ይህን ፍልሰት የሚያስቀር፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት የሚከፈቱት፣ የተዳከሙ ትምህርት ቤቶችን የሚያጠናክር አባት ያስፈልጋል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤት ተዘጋ ማለት እኮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተዘጋ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር በሰላም፣ በመተሳሰብ እንዲኖሩ፣ የገንዘብ አሰባሰቡ ሥርዐት እንዲኖረው፣  ወጣቱን ትውልድ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያሉትን የሚያሰባስቡ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዳይዘጉ የሚያደርጉ፣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆችን የሚከፍቱ አባት እንጠብቃለን፡፡

 

ሌላው ቤተ ክርስቲያኗን ዘመናዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዘመናዊ ስል ያሉትን ቀኖናዎች፣ ዶግማዎች ይሻሻሉ ማለት አይደለም፡፡ የአስተዳደር ዘርፍ፣ የገንዘብ አያያዟ ዘርፍ፣ የትምህርት አሰጣጧን ዘርፍ ዘመናዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዘመናዊ ለማድረግም ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ  ጊዜ ዲያቆናቷና ካህናቷ ዘመናዊ ትምህርት ተምረው በተለያየ የሙያ ዘርፍ የሠለጠኑ ናቸው፡፡ እነዚህን በቤተ ክርስቲያኗ የአስተዳደር ዘርፍ ውስጥ በመቅጠር ዘመናዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያኗ ባሏት ኮሌጆች ውስጥ፤ በሒሳብ አያያዝ፣ በአስተዳደር፣ በሌሎችም የሥራ መስኮች የተማሩ ሰዎችን ማፍራት ትችላለች፡፡ ስለዚህ የሚመረጡት አባት በእነዚህ ላይም ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በሚመረጡት ፓትርያርክ ትከሻ ላይ ብቻ የሚጣሉ አይደሉም፡፡ ከሥር ያሉ አማካሪዎቻቸው፣ ጳጳሳቱ፣ በተዋረድ በሀገረ ስብከት የሚመደቡ አስተዳዳሪዎች፣ የሥራ ሓላፊዎች ብቃትና ጥራት አብረው የሚታሰቡ ናቸው፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስም ለፓትርያርኩ ሥራ ቀና መንገድ መምረጥ አለበት፡፡ ጠንካራ ሲኖዶስ በሌለበት አንድ አባት ብቻቸውን ጠንካራ ሆነው ይሠራሉ ማለት አይቻልም፡፡ ሲኖዶሱ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የሚቀጥለው ርምጃዋ ምንድን ነው? የት መድረስ አለባት? በምን ዓይነት ሁኔታ ተራምዳ ነው እዛ ልትደርስ የምትችለው? ብሎ ማቀድ አለበት፡፡ በተለይ እንደ አሁኑ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ፈተና በበዛባት ጊዜ፤ የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና አቋም ይሄ ነው ብሎ መግለጫ የሚሰጥ ጠንካራ ሲኖዶስ መኖር አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለሙ ሁሉ ተስፋፍታለች ጠንካራ መሪና ጠንካራ ሲኖዶስ ከሌለ ደግሞ ይህን ሁሉ ድካም ከንቱ ነው የሚያደርገው፡፡ ስለዚህ ሲኖዶሱ ከፓትርያርኩ ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

 

ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የምንሰማው የቤተ ክርስቲያን ጭቅጭቅና የሌሎች መሳለቂያ መሆናችን መቅረት አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሰበክ ያለበት ሰላም ነው፡፡ በሲኖዶሱ መካከልም አለመግባባት ተወግዶ፤ በአዲስ አስተሳሰብ፣ በአዲስ ራእይ አንድ ሆነው ሀገራችን በጀመረችው የልማት ጐዳና አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ደግሞ የራሷን ገቢ በመፍጠር፣ ንብረት አያያዟን በማደራጀት፣ ቅርሶቿን በሙዚየም በማስቀመጥ ቱሪስቶች እንዲመለከቷቸው ልታደርግ ይገባል፡፡ ይህንንም ተመራጩ ፓትርያርክ ትኩረት ሊሰጡባቸው ይገባል፡፡

 

ፓትርያርክ ለመምረጥ የሚገቡ ሰዎችም ሊያስተውሉት የሚገባው ነገር አለ፡፡ ዝም ብለው መጥተው አዳምጠው ድምፅ ሰጥቶ ለመሄድ አይደለም፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከእኛ ምንድን ነው የምትፈልገው ብለው፤ ሊሠሩ የሚችሉትን አባት ለይተው ድምፃቸውን መስጠት አለባቸው፡፡ መራጮቹ ወክለው የሚመጡት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ምእመን ነውና፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ በተለያየ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ በርካታ ምሁራን ልጆች አሏት፡፡ እነዚህን ምሁራን በአማካሪነት ልትጠቀምባቸው ትችላለች፡፡ ምሁራኑም ሐመር መጽሔት አሁን በከፈተችው የውይይት መድረክ ላይ አሳባቸውን መስጠት አለባቸው፡፡ «ይህን ብናገር፤ እንዲህ ብባልስ» እያልን ከቤተ ክርስቲያን እየራቅን ከሄድን ነገ ያልሆነ ሰው ተመርጦ በቤተ ክርስቲያኗ ችግር ሲከሰት አብረን ማማት የለብንም፡፡ እስከ አሁን አምስት ፓትርያርኮችን ብቻ ነው የመረጥነው፤ ያለን ልምድ አጭር ነው፡፡ ያለፉት የአምስቱ ፓትርያርኮች የሥራ ዘመን ደግሞ ትንሽ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በእያንዳንዱን ዘመን ምን እንደተሠራ እንዴት አንደመረጥን ትምህርት ሊሆነን ይችላል፡፡ ከዛ በመነሣት በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ አባቶች ተስማምተው ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት እንዲያራምዱ፣ ጠንካራ አስተዳደር እንዲኖራት፣ ርእይ ያለው ሥራ እንዲሠራ መጣር አለባቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን ይህን ሓላፊነት ለመወጣት ትልቅ አደራ አለባቸው፡፡

 

«እግዚአብሔር መልካም መሪ እንዲሰጠን ልንለምነው ይገባል»

ኢንጂነር ዮሐንስ ዘውዴ

 

ingn. yohanse zewdeከፓትርያርክ ምርጫው በፊት እርቁ መቅደም አለበት የሚል አሳብ አለኝ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሊታረቀን የሚችለው እርቅ ሲመሠረት ነው፡፡ እርቅ ሲመሠረት፣ እግዚአብሔር የምንጠይቀውን ነገር ያሟላልናል፡፡ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉት ፓትርያርኮች፣ ጳጳሳት ብቻ አይደለም፤ ምእመናኑም ካህናት አባቶቻችንም በሙሉ እርቅ መመሥረት አለባቸው፡፡

 

አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተለያይታ «የእገሌ ሲኖዶስ፤ የእገሌ ሲኖዶስ» ልትባል አይገባም፡፡ ከዚሁም ጋር ተያይዞ ደግሞ እገሌን አልቀበልም የሚሉ አሉ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቱን መለያየቶች ለማስቀረት እርቅ ሰላሙ አንድ መስመር መያዝ አለበት፡፡ በካህናቱም መካከል ሰላም እንዲወርድ ቤተ ክርስቲያንን በአንድነት እንዲያገለግሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁ የተጣሉ ምእመናንም  የሚታረቁበት መድረክ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዘጋጀት አለበት፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ሁላችንም በፍቅር ሆነን እግዚአብሔርን በንጹሕ ልብ ልንለምነው ይገባል፡፡ ይህን እርቅ ከመሠረትን በኋላ ነው እግዚአብሔርም ይታረቀናል፤ የምንጠይቀውን በጎ ነገር ይሰጠናል፡፡ በውጭም፣ በሀገር ውስጥም ያሉት አባቶቻችን የራስን አቋም በማሰብ ሳይሆን  የእግዚአብሔርን መሻት ፈቃድ በማሰብ ሁሉን ነገር ለእርሱ አሳልፎ መስጠት ይገባል፡፡

 

ምርጫው ላይ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ በቅድሚያ የአመራረጡ ሂደት ነው፡፡  እኔ ከቅዱሳን መጻሕፍት እንደተረዳሁት ሁለት ዓይነት ምርጫዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ቅዱስ ድሜጥሮስ የተመረጠበት መንገድ ነው፡፡ የእስክንድርያው ጳጳስ የነበሩት ዩልያኖስ ከማረፋቸው በፊት ሱባኤ ገብተው ሕዝቡም ሱባኤ እንዲገቡ አድርገው እግዚአብሔር ድሜጥሮስን እንዲመረጥ ገልጾላቸዋል፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው፤ በይሁዳ ምትክ የተተካው ማትያስ የተመረጠበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ሁለተኛውን መንገድ በመከተል  በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክ ምርጫ ሲከናወን ለቦታው ብቁ ናቸው፣ ይመጥናሉ የሚባሉ ሦስት አባቶች አስቀድመው ቢመረጡ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡም፣ ጳጳሳቱ፣ ካህናቱ ሁሉ በአንድነት ሱባኤ ገብተው  እግዚአብሔር የፈቀደውን ከሦስቱ እንዲመርጥ ቢደረግ መልካም ይመስለኛል፡፡ ሌላው በፓትርያርክ ምርጫው ላይ ልንጠነቀቅ የሚገባው ምርጫውን በሥጋዊ ዐይናችን ተመልክተን ዘርን፣ ጎሣንና ፖለቲካን እንደመስፈርት ማየት የለብንም፡፡ እኛ ሰማያዊ ነገረ ነው የምናስበው የምንነሣውም እግዚአብሔርን  እንጂ ሰዎችን ብለን አይደለም፡፡

 

ለምርጫው መሳካት ሊቃውንቱ፣ ጳጳሳቱ፣ ምእመናኑ ሁሉም በጸሎት መትጋት ይገባናል፡፡ ይህም በሥጋ ፈቃድ ተመርተው «እገሌ ይሾምልን» የሚለውን አመለካከት ከእኛ ማራቅ የምንችለው በጸሎት ስንተጋ ብቻ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የሚመርጥ እግዚአብሔር እንጂ ሰው መሆን የለበትም፡፡ ምርጫውንም የተሳካ እንዲያደርግልን ለእርሱ እንስጠው፡፡ፓትርያርኩ ከተመረጡ በኋላም ሊፈጽሟቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ጥቂቱን ልጥቀስ፡፡ ከላይ እስከ ታች ባሉ የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ተሰግስገው የሚገኙትን ሃይማኖት ቦርቧሪዎችን በመለየት እንዲታረሙ አድርጎ ለንስሐ ማብቃት ካልሆነም ከአገልግሎት ማራቅ ቢቻል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት አላግባብ ለሥጋዊ ኑሮአቸው ማበልጸጊያ የሚያደርጉትን ሕገ ወጦች መቆጣጠር ማረም መቅጣት ቢቻል፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ደብር ያለው አሠራር በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ ወጥና የተሟላ መረጃ ሊኖረው የሚችል ባለሙያ የተጠናና የታገዘ አሠራር በመዘርጋት በገጠርዋ የምትገኘው ደሳሳዋና በከተማ በዘመናዊ ሕንፃ የተገነባው ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱም ክብሩም አንድ ዓይነት በመሆኑ በማእከል የተጠናና ገጠሩንም፣ ከተማውንም የአካተተ የአገልግሎት ክፍያ በማደላደል በገጠሩም ሆነ በከተማ አገልግሎት የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

ዛሬ የአብነት ትምህርት ቤቶች በየቦታው እየተዘጉ መምህራንና ተማሪዎች እየተሰደዱ ናቸው፡፡ እነዚህ የአብነት ትምህርት ቤቶች የነገ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች  የሚወጡበት ቦታዎች ናቸው፡፡ ምእመናኑም በየገጠሩ አገልጋይ፣ እረኛ፣ አስተማሪ በማጣቱ  በቀበሮ እየተነጠቀ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በገጠር አካባቢ ስብከተ ወንጌል አልተስፋፋም፡፡ በጥቂቱም ተስፋፍቶ የምናየው በከተማ አካባቢ ብቻ ነው፡፡ አገልጋይ ባለመኖሩ ወንጌል ባለመስፋፋቱ ብዙ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን በመሳሰሉ ነገሮች ላይ ጠንከር ያለ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ ስለዚህ ተመራጩ ፓትርያርክ እነዚህን ችግሮች በሂደት ለመቅረፍ ቆርጠው ሊነሡ ይገባል፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስም በርካታ ተግዳሮቶች ይጠብቁታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ህልውና መሠረት ቅዱስ  ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ የሚሆኑበትን ነገር መከታተል ይገባዋል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው በሲኖዶስ ተወስነው፣ ተግባራዊ ያልሆኑ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ካህናቱ እንዲሁም ምእመናኑ ይፈተኑበታል፡፡ ለሲኖዶስ የሚሰጠውን ክብርም ያዛባዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስን መንፈስ ቅዱስ ነው የሚመራው በመሆኑም  መንፈስ ቅዱስ የሚወሰነው ተግባራዊ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ መንፈስ ቅዱስ ነው የሚወሰነው የሚለው አጠያያቂ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወሰኑትን ውሳኔዎች በሙሉ ተግባራዊ ሊያደርግ፣ ተግባራዊነታቸውንም ሊከታተል ይገባል፡፡

 

ይህን ትልቅ ሓላፊነት ለመወጣት ከንጉሥ ሰሎሞን መማር ያስፈልጋል፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ሲሾም እግዚአብሔር «ይህን ሕዝብ የሚያስተዳድርበትን ጥበብ ስጠኝ» ብሎ ነው የጠየቀው፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ይህችን ሃይማኖት ጠብቀው አቆይተዋል፡፡ ዛሬም አባቶቻችን ይህንን ሓላፊነት ለመወጣት ለተተኪው ትውልድ ሳትሸራረፍ፣ ሳትከለስ፣ ሳትበረዝ ሊያስተላልፉ የሚችሉበትን ኃይልና ጥበብ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው መለመን ይገባቸዋል፡፡

 

በአጠቃላይ ይህ የፓትርያርክ ምርጫ የተሳካ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔርም መልካም መሪ እንዲሰጠን ሃይማኖታችን ከጎበጠችበት የምትነሣበትን ትንሣኤ እንድናገኝ በጸሎት እንትጋ፡፡ አስተዋይ መንፈሳዊ መሪ፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚያስብ፣ መንጋውን ሊጠብቅ የሚችል ትጉህ እረኛ እንዲሰጠን መንጋውም የእረኛው ቃልን የሚሰማ አስተዋይ እንዲሆን እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡

 

  • ምንጭ፡- ሐመር 20ኛ ዓመት ቁጥር 6 ጥቅምት 2005 ዓ.ም.