‹‹ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሺ፥ ተመለሺ›› (መሓልየ መሓልይ ዘሰሎሞን ፯፥፩)

ክፍል አንድ
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
መስከረም ፳፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በብሥራተ መልአክ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችውን አንድያ ልጇን ሄሮድስ ሊገድልባት በፈለገው ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሀገር ወደ ሀገር መሰደዷን የሚያመለክተውን፣  ከስደትም እንድትመለስ ጠቢቡ በትንቢት ቀድሞ የተናገረው ይህን ቃል ነው፡፡ ወቅቱ አብዝተን ስለ ስደቷና ተያያዥ ታሪኮች የምንማርበት፣ የምንጸልይበት፣ የምናስተምርበትና የምንዘምርበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ርእስ ተከታታይ ጽሑፎችን ለማቅረብ እንሞክራለን፤ እንድትከታተሉን እናሳስባችኋለን፤ ምልጃዋ አይለየን!!!

ቤተ ክርስቲያናችን መቼም ይህ ቀረሽ የማትባል ስንዱ እመቤት መሆኗን ሁሉን በዓይነቱና በፈርጁ ያዘጋጀች ለሁሉ የሚሆን፣ ከሁሉ የሆነ ነገር ያላት እመቤት ናት፡፡ ትምህርቷን በወቅትና በሁኔታ ከፋፍላ እንደሚመች እንደሚመች፣ ለመብላት፣ ለመጠጣትና ለማጣጣም እንዲመች አድርጋ እንደምታቀርብ ወርኃ ክረምት ላይ አንድ ጽሑፍ አጋርተናችሁ ነበር፡፡ ስለ እመቤታችን ስደትና መከራ ስለተነሣንበት እርስ ከማብራራታችን በፊት ስለወቅቱ ትንሽ ማለት የግድ ነውና ስለ ወርኃ ጽጌ/ዘመነ ጽጌ/ የተወሰነ እንላለን፡፡

ጽጌ የሚለው ቃል በቁሙ ሲፈታም አበባ የሚል የአማርኛ ትርጉም አለው፡፡ ወርኃ ጽጌ የክረምቱን ማለፍ፣ የውኃውን መጉደል፣ የነገድጓዱን፣ የጎርፉን፣ የጨለማውን፣ የመከራ ምልክት የሆነውን የክረምቱን ማለፍ፣ የምድሩን መርጋት፣ የውኆችን መጥራት፣ የጨለማውን መገፈፍ፣ የብርሃንን መውጣት፣ የአበቦችን መፍካት፣ የምድርን ውበት የሚያመለክት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት ወቅት ነው፡፡

የጽጌ ወር ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው፡፡ ጽጌ፣ ምድር በአበባ፣ ማኅሌቱ በያሬዳዊ ዜማ የሚፈካበት ልዩ ወቅት፣ ምድር የምትዋብበትና የምትቆነጅበት፣ ተራሮች የሚንቆጠቆጡበት የጌጥ፥ የውበት ወቅት እንደሆነ ጠቢቡ ሲገልጽ “እነሆ ክረምቱ አለፈ፤ ዝናቡም አልፎ ሄደ፤ አበቦችም በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ” ይላል፡፡ (መሓ. ፪፥፲፩) “አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳን በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም” እንዲል፤ (ሉቃ.፲፪፥፳፯) ተራሮችና ኮረብቶች በሰው እጅ ያልተጌጠውን ውብ የሆነ ልብሳቸውን ተጎናጽፈው የሚመለከታቸውን ሁሉ ትኩረት የሚስቡበት፣ ለአፍንጫ ተስማሚ የሆነውን ጥዑም መዓዛቸውንም እንካችሁ ብለው ያለስስት የሚቸሩበት፣ አዕዋፍ ዝማሬያቸውን ከወትሮው በላቀ ሁኔቴ የሚያንቆረቁሩበት፣ ንቦች ከአበባ ወደ አበባ እየባረሩ ጣፋጭ ማርን የሚያዘጋጁበት፣ ሁሉ አምሮ፣ ሁሉ ደምቆ፣ አዲስ ሆኖ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ ይህ ጊዜ ወርኃ ጽጌ፣ ዘመነ ጽጌ በመባል ይታወቃል፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ዝማሬዋን፣ ትምህርቷን፣ ዜማዋን፣ ንባቧን፣ ለወቅቱ እንዲስማማ እያደረገች በምሳሌና በኅብር፣ በሰምና ወርቅ እያዋዛች ለጀሮ እንዲስማማ፣ ለልብ እንዲያረካ፣ ለሥጋ ስክነትን ለነፍስ ዕረፍትን እንዲሰጥ አድርጋ ታቀርብበታለች፡፡ በሰማዩ ፍካት፣ በውኃው ጥራት፣ በኮከቦች መውጣት፣ በአበቦች ውበት፣ በተዘሩት አዝርዕት፣ በጸደቁት አትክልት፣ በዛፎቹ ልምላሜ፣ በአዝርዕቶቹ ፍሬ ሁሉ ቃሉን እየመሰለች ታስተምራለች፤ ትዘምራለች፤ ትቀድሳለች፤ በጥበብ ረቅቃ ታራቅቃለች ተቀኝታ ታስቀኛለች፡፡

ቤተ ክርስቲያን በምልዓትና በሙላት ያለች ናት፡፡ ይህን ዘመነ ጽጌንም እንደ ሌሎች ወቅቶች/ወንጌልን ለማስተማር፣ የራቀውን አቅርባ የረቀቀውን አጉልታ፣ የጎደለውን ሞልታ፣ የጠመመውን አቅንታ ለማስተማር በብዙ መልኩ ትጠቀምበታለች፡፡ በልዩ ሁኔታ ነገረ ማርያምም ነገረ ክርስቶስም በስፋት የሚሰበክበት ወቅት በመሆኑ ዘመነ ጽጌ እጅግ ተወዳጅ ወቅት ነው፡፡ ወርኃ ጽጌን ልዩ የሚያደርገው አንዱና ዋናው የእመቤታችን እና የተወዳጅ ልጇ ስደት የሚታሰብበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

ውድ የዚህ ጽሑፍ ተከታታዮች ‹‹ሱላማጢስ ሆይ ተመለሺ ተመለሺ›› በሚል ርእስ ስለ ስደቷና ተያያዥ ታሪኮች በቀጣይ ክፍል ሰፋ አድርገን እናቀርብላችኋለን፡፡

እስከዚያው ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን!