“ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” (ዘፍ.፩፥፳፮)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
የካቲት ፳፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በዕለተ ዐርብ እግዚአብሔር አራት ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡ እነርሱም በእግር የሚሽከረከሩ፣ በክንፍ የሚበሩና በልብ የሚሳቡ፣ በየብስ፣ የሚኖሩ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ ፍጥረታትን ነው፡፡ በመጨረሻም እግዚአ ዓለም ሥላሴ “ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” ብለው በነግህ አራቱን ባሕርያተ ሥጋ አምስተኛ ባሕርየ ነፍስን አዋሕደው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ አድርገው በማዕከለ ምድር በቀራንዮ ፈጠሩት፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮)

ሰው ምንድነው? ማን ፈጠረው? ከዬት መጣ? የሚሉት ሰውነቱን ማእከል ያደረጉ ጥያቄዎች በሳይንስና በፍልስፍና ሰዎች ሲጠየቁ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ሳይንስም ሆነ ፍልስፍና የሰውን አመጣጥ ደርሰንበታል ከሚሉት ነገር ግን ደግሞ እርግጠኞች ካልሆኑበት ዕውቀታቸውና ዕውቀታቸውን መሠረት አድርገው ከቆሙበት “እምነት” አንጻር በየቀኑ እያሻሻሉና እየለወጡ “ከዚህ ነው፤ ከዚያ ነው” ቢሉንም የሰውን ፍጻሜ በእነርሱም ዘንድ በብዥታ ስለሚታየው ከሰው ሞት በኋላ ስለሚኖረው አኗኗር እስካልነገሩን ድረስ ከጥያቄ አያመልጡም፡፡

ፍልስፍናውና ሳይንሱ ሰው ምንድነው? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ የሚሰጡትን መልስ እንተወውና ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ሰው ምን ያስተምሩናል? የሚለውን መመልከቱ በብዙ መንገድ ተገቢና ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ስለ ሰው ማንነትና ምንነት ማወቅ ራስንም ፈጣሪንም ማወቅ ነው፤ ሌሎችንም መረዳት ነው፡፡ ስለ ሰው ማንነትና ምንነት ማወቅ ሰው ሆነን በተፈጠርንበት ዓላማና ግብ እንድንኖር ያደርገናል፡፡ እኛነታችንንም ለአልባሌ ነገር እንዳናስገዛው ለራሳችንም ክብር እንድንሰጥ ሰውነትንም ከሚጎዱ ውጪያዊም ሆነ ውስጣዊ ነገሮች ለመጠበቅ ያስችለናል፡፡ ስለ ሰው ማንነትና ምንነት ማወቅና መገንዘብ እንደእኛ የሆነውን ሰው ከሰውነት በኋላ በመጡ፣ በጥንተ ነገዱ፣ በብሔረ ሙላዱ፣ በጎሳው፣ በአፍአዊ ማንነቱ፣ በሀብቱ፣ በንብረቱ፣ በክሳቱ፣ በውፍረቱ፣ በእጥረቱ፣ በርዝማኔው፣ በቆዳ ቀለሙ፣ በዕውቀት ደረጃውና በሌሎች መሰል ውጪያዊ መመዘኛዎች ከማየት ተቆጥበን ክቡር በሆነ የሰውነት ማንነቱ መመልከት ስንጀምር ክቡር ግሩምና ድንቅ አድርጎ የፈጠረውን ፈጣሪው እግዚአብሔርን መመልከትና ማክበር እንጀምራለን፡፡

ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው ሰው ግሩምና ድንቅ ሆኖ የተፈጠረ ፍጡር ነው፡፡ (መዝ.፻፴፰÷፲፬) ሰው አስቀድሞ በፈጣሪው በልዑል እግዚአብሔር ሲፈጠርም አፈጣጠሩ በብዙ መንገድ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ ሆኖ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ በሥነ ፍጥረት ትምህርት እንደተማርነው እግዚአብሔር በዓለም ያሉ ፍጥረታትን በኃልዮ (በሐሳቡ ይሁኑ በማለት) በነቢብ (በቃል በመናገር ይሁኑ በማለት) ሲፈጥር ሰውን የፈጠረው ግን በገቢር በእጆቹ ነው፡፡ ነቢዩ “እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም” ብሎ እንደመሠከረ፡፡ (መዝ.፻፲፰÷፸፫) ይህም ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በእርሱ መልክና እንደ ምሳሌው አድርጎ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም አለ፥ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ዘፍ.፩÷፳፮) ሰው ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ ካገኘን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እንደርሳለን የምንልበትን (ያልንበትን) ምክንያት ይህን ቃል መሠረት አድርገን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

እንደሊቃውንቱ አስተምህሮ ሰው በሥጋው አራት ባሕርያት በነፍሱ ሦስት ባሕርያት ያሉት ፍጥረት ነው፡፡ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ የሚባሉት ነፋስ ߹ እሳት ߹ ውኃና መሬት ሲሆኑ ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የሚባሉትም ለባዊነት (ማወቅ) ነባቢነትና (መናገር) ሕያውነት ናቸው፡፡ በእነዚህ የሥጋና የነፍስ ባሕርያት ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን ገልጧል፡፡ ካስተዋልነው በሰው የሥጋ የነፋስ ባሕርይ የእግዚአብሔር ፈታሒነቱን እንረዳለን፡፡ ገበሬ በነፋስ አማካኝነት ምርቱና ግርዱን፣ ፍሬና ገለባውን ይለያል፡፡ እግዚአብሔርም በፈታሒነቱ (በሚዛናዊ ፍርዱ) ኃጥአንን ከጻድቃን፣ እውነተኞችን ከሐሰተኞች፣ ርኩሳንን ከቅዱሳን ይለያል፡፡ (ማቴ.፫÷፲፪፣፳፭÷፴፪) እርሱ ኃጥኡን ጻድቅ ነህ፤ ሐሰተኛውን እውነተኛ ነህ አይለውምና፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ኃጥእ አይገኝም፤ ጻድቅ ግን የዘለዓለም መሠረት ነው” ማለቱም የእግዚአብሔር ፈታሒነቱ በዐውሎ ነፋስ እንደሚመሰል ያስተምረናል፡፡ (ምሳ.፲÷፳፭)

ሁለተኛው የሰው የእሳት ባሕርይ በእግዚአብሔር ከኃሊነት ይመሰላል፡፡ እሳት፣ ገደልና ወንዙ ካልከለከለው ሁሉን ማቃጠል እንዲችል እግዚአብሔርም ቸርነቱ ካልከለከለው ሁሉን ማድረግ የሚችል የሚሣነው የሌለ ከኃሌ ኩሉ ነው፡፡ (ሉቃ.፩÷፴፯፣ ዘፍ.፲፰÷፲፰) በዘዳግም መጽሐፍ “አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነውና” ተብሎ መነገሩም ለዚህ ነው፡፡ (ዘዳ.፬÷፳፬) በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተነገረ እግዚአብሔር ራሱን በእሳት ውስጥ ብዙ ጊዜ ገልጧል፤ ቃሉንም አሰምቷል፡፡ (ዘዳ.፭÷፬፣፭÷፳፫፣፱÷፲፭) የሚያጸና፣ የሚያነጻ፣ ፣ የሚፈርድ ቅዱስ ቃሉም በእሳት እንደሚመሰል በራሱ አንደበት ሲመሠክር “በውኑ ቃሌ እንደ እሳት ድንጋይም እንደሚያደቅ መዶሻ አይደለምን?” ብሏል፡፡ (ዘካ.፯÷፲፪) እግዚአብሔር በሰውነታችን ባለ እሳታዊ ባሕርይ የተመሰለበትና ራሱንም በእሳት የገለጠበት ምክንያት ብዙ ነው፡፡ እሳት ብሩህ ነው፤ እግዚአብሔርም ብሩሃ ባሕርይ ነው፡፡ እሳት በምልዓት ሳለ ድንጋይን በድንጋይ ካላጋጩ ክብሪት ካልመቱ አይታይም፤ እግዚአብሔርም ካልፈለጉት አይታይም፤ ከፈለጉትም አይታጣም፡፡ እሳት አንዴ ከለኮሱት በኋላ ማገዶ ሲጨምሩበት እየሰፋ ይሄዳል፤ እግዚአብሔርም ለሰዎች ጸጋውን በጥቂቱ ይሰጣል፤ በእምነት በምግባር በትሩፋት እያበዙት ይሄዳሉ፡፡

ሦስተኛው የሥጋ ባሕርይ ውኃዊ ነው፡፡ በሰውነታችን ያለ የሥጋችን ውኃዊ ባሕርይ የእግዚአብሔር የቸርነቱ ምሳሌ ነው፡፡ ውኃ የማያጸዳው ዕድፍ ጉድፍ የለም፤ ሰው ንስሓ ከገባ እግዚአብሔርም በቸርነቱ ይቅር የማይለው ኃጢአትና በደል የለም፡፡ (ዘዳ.፴፬÷፬፣ ሚክ.፯÷፲፰)

አራተኛው የሥጋ ባሕርይ መሬታዊ ባሕርይ ነው፡፡ “አዳም ሆይ መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ” እንዲል፡፡ (የሰኞ ውዳሴ ማርያም) የሰው መሬታዊ ባሕርይ የእግዚአብሔር የባዕለጠግነቱ ምሳሌ ነው፡፡ ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “ምድርን ጎበኘሃት፤ አጠጣሃትም፤ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ” ብሎ እንደመሠከረ፡፡ (መዝ.፷፬÷፱) መሬት (ምድር) ባዕለጠጋ ናት፤ ሁሉን ታስገኛለችና፤ እግዚአብሔርም ለባዕለጠግነቱ መጠን ስፍር ቁጥር የሌለው አምላክ ነው፡፡ (፪ኛቆሮ.፰÷፱፣ ሮሜ.፲፩÷፴፫)

ሰው እነዚህ አራት ባሕርያተ ሥጋ ብቻ ያሉት ፍጡር ሳይሆን ለባዊት (ዐዋቂ) ነባቢት(ተናጋሪ) እና ሕያዊት የሆነች ነፍስ ያለው ፍጡር ነው፡፡ (ዘፍ.፴፭÷፲፮፣ መክ.፲፪÷፯፣ ማቴ.፲÷፳፰፣ የሐዋ.፯÷፶፱) በመሆኑም ከእግዚአብሔር በተሰጠው የዐዋቂነት፣ የተናጋሪነትና ሕያውነት ጸጋ ያውቃል፤ ይናገራል፤ እንደፈጣሪው ፈቃድ ከኖረም በደስታ በተድላ መንግሥተ ሰማያት ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ማወቅ፣ መናገርና ሕያውነት ደግሞ የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቦቹ ሲሆኑ በመልኩ እንደምሳሌው አድርጎ ለፈጠረው ሰውም በጸጋ ገንዘቦቹ እንዲሆኑ ሰጥቶታል፡፡

ሰው ምንድነው? የሚለውን ጉዳይ በእውነትና በእምነት ስንረዳም በሰው ሰውነት ውስጥ የእግዚአብሐርን ፈታሒነት፣ ከሀሊነት፣ ቸርነትና ባዕለጠግነት እንዲሁም ዐዋቂነቱን፣ ነባቢነቱንና ዘለዓለማዊነቱን እናውቃለን፤ እናያለንም የምንለው ለዚሁ ነው፡፡ የሰውን ማንነትና ምንነት ለማስረዳት ሊቃውንቱ ከላይ በጥቂቱ ለመግለጥ ከሞከርንበት መንገድ በተጨማሪ ሰው በእግዚአብሔር መልክና እንደምሳሌው ተፈጥሯል ተብሎ የተነገረውን ቃል ለማስረዳት የእግዚአብሔር መልክ ማለት ምን ማለት ነው? የእግዚአብሔር ምሳሌ መሆንስ በምን ይገለጣል? የሚለውን አስፍተውና አምልተው በማብራራት ያስተምራሉ፡፡ እንደ ሊቃውንቱ አስተምህሮ የእግዚአብሔር መልክ የሚባለው ቅድስና፣ ፍቅር፣ ቸርነት፣ ነጻነት፣ ጥበብ፣ ገዥነት፣ ክብር፣ ንጽሕና፣ ፍትሐዊነት፣ ርኅራኄ፣ አሳቢነት፣ ዕውቀትና የመሳሰሉት ነው፡፡ እነዚህ የአምላካችን የእግዚአብሔር የባሕርይው መገለጫዎች የሆኑ ነገሮች ሰው በተፈጠረ ጊዜ በጸጋ ተሰጥተውታል፡፡ (መክ.፯÷፳፱፣ ዘሌ.፲፱÷፪፣ ሉቃ.፮÷፴፮፣ ፩ኛጴጥ.፩÷፲፮)

እነዚህን የቅድስና መንፈሳዊ ባሕርያት መገለጫዎች እያጎለበተና እያሳደገ ሲሄድም የእግዚአብሔር ምሳሌ ወደ መሆን ይደርሳል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን “ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” ማለቱም ይህን ያጠነክርልናል፡፡ (፪ኛቆሮ.፫÷፲፰) ይህ የሐዋርያው ምሥክርነት ሰው ራሱን በእምነት፣ በምግባርና በትሩፋት እያሳደገ ሲሄድ ፈጣሪውን ወደ መምሰል እንደሚደርስ ያስገነዝበናል፡፡ ሐዋርያው በሌላ ስፍራ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ” ብሎ ተናግሯል፡፡ (፩ኛቆሮ.፲፩÷፩) ሐዋርያው ክርስቶስን የመሰለው በምንድነው? በአኗኗሩ አይደለምን ? “በክርስቶስ እኖራለው የሚል ክርስቶስ እንደተመላለሰ ይመላለስ ዘንድ ይገባዋል” ተብሎ እንደተነገረ፡፡ (፩ኛዮሐ.፪÷፮)

ሰው ክርስቶስ ባሳየው የትሕትና፣ የፍቅር፣ የትዕግሥት፣ ለሌሎች ራስን አሳልፎ የመስጠት ሕይወት፣ የመታዘዝ መንገድ ሲጓዝ ክርስቶስን መሰለው ይባላል፡፡ እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር” ብሎ የተናገረው ቃል ሰው ምንኛ የከበረ ፍጥረት መሆኑን ያመለክተናል፡፡ በጥንተ ተፈጥሮ ሰውን አክብሮና አግኖ የፈጠረው እግዚአብሐር ሰው ከሳተም በኋላ እንደወደቀ፣ እንደረከሰና እንደተሰናከለ ይቅር ብሎ ሳይንቀውና ሳይተወው በሐዲስ ተፈጥሮ (በማዳኑ ሥራ) ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶታል፡፡ ዛሬ በኃጢአት የምናረክሰው፣ በአደንዛዥ ዕፆች የምናቆሽሸው ሰውነታችን እንዲሁም አለአግባብ በልዩ ልዩ መንገድ ሥር ምሰን፣ ቅጠል በጥሰን የምናጎሳቁለው በድንጋይ ወግረን፣ በስለት መሣሪያዎች በሳስተን፣ በጥይት ነድለን የምናጠፋው ሰው እግዚአብሐር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተለት ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ ሰው ከምድርና ከሰማይ በላይ ዋጋ ተከፍሎለታል፡፡ ጌታችን ሰውን ዘለዓለማዊ አድርጎ ሲፈጥረው ሰማይና ምድርን ግን የሚያልፉ አድርጎ ፈጥሯቸዋል፡፡ (ማር.፲፫÷፴፩፣ ፪ኛ.ጴጥ.፫÷፲፣ መዝ.፻፩÷፳፭)

ሰው የእግዚአብሔር ሕንጻ ነው

በዚህ ዓለም ያለን ሰዎች እንደ የአቅማችን በጭቃም ቢሆን በሣር ወይም በከበረ ድንጋይ የሠራነውን ቤት እንጠብቃለን፤ እንከባከባለንም፡፡ ከፍ ሲልም ሙያተኞች ቀጥረን የምንፈልገውን ንድፍ አሠርተን ጊዜና ገንዘብ፣ ሐሳብና ጉልበት መድበንና አውጥተን ያቆምነውን ሕንጻ እንጠነቀቅለታለን፡፡ በየጊዜውም ዕድሜውን ሊያረዝሙ የሚችሉ ተጨማሪ ጥገናዎችን እያደረግን ውበቱንና አገልግሎት የመስጠት አቅሙን እንጨምራለን፡፡ ይህ ብልሃት ጥበብና የሚገባም ነገር ነው፡፡ እኛ በሠራነው ሕንጻ ማን ሊያዝዝ ይችላል? ያለ ፈቃዳችንስ ማን ሊጠቀምበት ይችላል? ሰውም ሕያው የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕንጻ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን ስለዚህ ጉዳይ ሲያስተምራቸው “እናንተ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ” ብሏቸዋል፡፡ (፩ኛቆሮ.፫÷፱)

ሕንጻችንን በሥርዓትና በንጽሕና እንደምንጠብቀው የእግዚአብሔር ሕንጻ የሆነ እኛነታችንንም በንጽሕና ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ሰው የእግዚአብሔር ሕንጻ መሆኑን ብንረዳ ኖሮ ሰውን በሆነውም ባልሆነውም አንጎዳውም ነበር፡፡ ሰውነታችንንም ሊያረክስ በሚችል ክፉ ሥራም አንሠማራም ነበር፡፡ የሕንጻ ጥንካሬውና የመሸከም አቅሙ እንዲሁም ዕድሜው የሚወሰነው በመሠረቱ እንደሆነ ሰውም በዚህ ዓለም በሚገጥመው ፈተና፣ መከራ ችግርና ሥቃይ ተሸንፎ ተስፋ እንዳይቆርጥ፣ ከፈጣሪውም እንዳይለይ፣ በጎ ሥራን ከመሥራት እንዳይታክት፣ በክፉ ሕሊናት (ሐሳቦች) እግዚአብሔርን በሚያስክድ አእምሮ የነፍስ ጥፋት ምክንያት በሆነ ክህደትና ኑፋቄ እንዳይሸነፍ መሠረቱ ሃይማኖት ነው፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት፣ የባሕርይ አምላክነት፣ ፈጣሪነት፣ ፈራጅነትና ዘለዓለማዊነት በልቡናችን የምታኖር ከወዳጆቹ ከቅዱሳን ጋር እንደምንኖር እንድንረዳ ዕውቀትን የምትሰጥ፣ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ከመቃብር በኋላ ትንሣኤ መኖሩን በማመን ተስፋ በማድረግ በእምነትና በበጎ ሥራ እንድንጸና በምታስገነዝብ በጸናች፣ በቀናች፣ በጎላች፣ በተረዳች፣ ተዋሕዶ ሃይማኖት መመሥረት በዚህ ዓለም በሚገጥሙን ፈተናዎች ተሸንፈን ታላቅ በሆነ አወዳደቅ እንዳንወድቅ ያደርገናል፡፡ ጌታችን በወንጌል “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን (ቤተ ልቡናውን) በዓለት (በነቢያትና በሐዋርያት እምነት) ላይ የሠራ ልባምን ሰው ይመስላል፤ ዝናብም ዘነበ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ (የዚህ ዓለም ፈተናና መከራ) ያንም ቤት መታው፤ በዓለትም ላይ ስለተመሠረተ አልወደቀም ” ብሎ እንዳስተማረን፡፡ (ማቴ.፯÷፳፬)

ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው

በቅዱሳት መጻሕፍት ሰው ቅዱስና ሕያው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሮናል፤ “እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና”፤ (፪ኛቆሮ.፮÷፲፮) “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?” እንዲል፡፡ (፩ኛቆሮ.፫÷፲፮) ሰው ራሱን ለእግዚአብሔርና ለፈቃዱ ካስገዛ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆኖ ስለሚቀር እግዚአብሔር ሰውነቱን መቅደስ፣ ልቡናውን ዙፋን አድርጎ ያድርበታል፡፡ በጥንተ ተፈጥሮም ሆነ በሐዲስ ተፈጥሮ (በክርስቶስ ማዳን) የተፈጠረበት ዋና ዓላማ ይህ ነው፡፡ በአንጻሩም ከእግዚአብሔር ስንርቅ፣ ለሰይጣንና ለፈቃዱ ስንገዛ ፣በሥጋ ፈቃዳችንም ስንሸነፍ መንፈሰ እግዚአብሔር እየተለየን የሰይጣን ማደሪያዎች እንሆናለን፡፡ ሰው የሰይጣንና የሠራዊቱ ማደሪያ እንዲሆን የእግዚአብሔር ፈቃዱ ባይሆንም በክፉ ሥራው ግን የሰይጣን ማደሪያ ይሆናል፡፡ ሰይጣን ሲያድርበትም ቅድስናን፣ ንጽሕናን፣ ሰላምን፣ በጎነትንና የቀናውን ሐሳብ ያጣል ያሳጣልም፡፡

የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነን የሰው ልጅ ቅዱሳን መላእክት እንኳን በዙሪያው ሆነው ይጠብቁታል እንጂ አያድሩበትም፡፡ (መዝ.፴፫÷፯፣መዝ.፺÷፲፩) በንጉሥ ዙፋን ላይ አገልጋይ ይቀመጥ ዘንድ በእልፍኙም ያድር ዘንድ እንዴት ይቻለዋል? ቅዱሳን መላእክት ሰውን ከመጠበቅ አልፈው በሰው እንደር አለማለታቸው ለእግዚአብሔር የሚሰጡትን ክብር ከማሳየቱም በላይ የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ብቻ ማደሪያ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ ቅዱሳን መላእክት እንኳን ከመጠበቅ ባለፈ በማያድሩበት በሰው ሰይጣን ለምን ያድርበታል ? ቢሉ መልሱ ግልጽ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰይጣን የእግዚአብሔር የሆነን ነገር በመውሰድ ወደ ጥልቁ ማውረድ ስለሚፈልግ አንድም ሰው በዚህ ምድር ሲኖር በእምነት ጸንቶ፣ በምግባር ቀንቶ፣ በሕጉ በትእዛዙ ተጠብቆ ካልኖረ በገዛ ፍቃዱ የሰይጣን ማደሪያ ለመሆን እንደወሰነ ያጠይቃል፡፡ (ማቴ.፲፪÷፵፬)

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ እንደሆነ ሰውም ራሱን በቅድስና መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ራሱን በቅድስና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎችን የኃጢአትና የርኩሰት ሥራ እንዲሠሩ በመከረ፣ ባነሣሣና ባባበለ ቁጥር ንጹሕ በሆነው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ለዐይን የሚከፋ ለአፍንጫ የሚከረፋን ቆሻሻ ወይም ጉድፍ እየከመረ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ መጽሐፍ “ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ” ብሎ እንደተናገረ፡፡ (፩ኛቆሮ.፫÷፲፯) ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን በሥጋችን ሞትን በነፍሳችን ጥፋትን ሊያመጣ የሚችል ነገርን በማድረግ ለሞተ ሥጋ ለሞተ ነፍስ መዳረግ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው፡፡ ሰው በገዛ ፍቃዱ ተነሣሥቶ ራሱንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን እንዲገድል ያልተፈቀደበትም ሰውን መግደል ማለት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ማፍረስ ማለት ስለሆነ ነው፡፡

ዛሬ በአገራችንም ሆነ በዓለማችን ሰውን በሰውነቱ ማየት ተስኖን፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑን መረዳት አቅቶን፣ በቋንቋው በጥንተ ነገዱ በብሔረ ሙላዱ (በተወለደበት ነገድና ሀገር) እየለየን የምንገድለው፣ የምናሠቃየውና የምናከራትተው ሰው ክቡር የሆነ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ሰውን በመግደላችን፣ በማሠቃየታችንና በማንከራተታችንም ከባዱን ፍርድ ከእርሱ ዘንድ እንደምንቀበል መረዳት ይኖርብናል፡፡ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለዓይን የሚማርክ፣ ለልቡና የሚመስጥ፣ ለአፍንጫ የሚስማማ በጎ መዐዛ ያለውን ነገር (ዕጣን) ያጤሱበታል እንጂ ለዓይን የሚከፋውን፣ ለልቡና የማይስማማውን፣ ለአፍንጫ የሚሰነፍጠውን ነገር እንደማያጤሱበት የእግዚአብሔር መቅደስ በሆነ ሰውነታችንም ሰውነታችንን የሚያደነዝዝ፣ የሚያጉሳቁል፣ የሚያከረፋ፣ ዕድሜያችንንም የሚያሳጥር እንዲሁም የሚያረክስ ነገር ልናደርግበት አይገባም፤ ሌሎችም ያንኑ እንዲፈጽሙም መገፋፋት ተገቢ አይሆንም፡፡ ሰው የራሱ ያልሆነ፣ በክርስቶስ ወርቀ ደም የተገዛ፣ የተዋጀ ፍጥረት ነውና “ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሰችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (፩ኛቆሮ.፮÷፲፱-፳)

ሰው የእግዚአብሔር እርሻ ነው

ብርሃነ ዓለም መምህረ አሕዛብ የተባለ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “እናንተ የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ” ይላል፡፡ (፩ኛቆሮ.፫÷፱) የልባምና ትጉኅ ገበሬ እርሻ በተገቢው ጊዜ ስለሚኮተኮት ዐረም እንዳይበቅልበት፣ ቀበሮ እንዳይዘልበት ጥበቃ ስለሚደረግለት፣ ድንጋይ ስለሚለቀምለት፣ በዐጥር ስለሚታጠር፣ ቅጥር ስለሚደረግለት፣ መልካም ዘርም ስለሚዘራበት መልካም ፍሬን ያፈራል፡፡ ሰውም ዐረም የተባለ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የተነቀለለት፣ ቀበሮ የተባለ ተንኮለኛ ሰይጣን እንዳይዘልበት፣ ሥልጣን የተሰጠው እንደ ድንጋይ የደነደነና የጠነከረ ልቡና እንዳይኖረው፣ በእግዚአብሔር ቃል የተነገረው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከኖረም የእግዚአብሔር ረድዔት እንደ አጥር ቅጥር ሆኖ የሚጠብቀው የደጉ ገበሬ የእግዚአብሔር እርሻ ነው፡፡ (ኢሳ.፭÷፩-፲፣ ዮሐ.፲፭÷፩፣ ኢዮ.፵፩÷፲፮)

አንድ ገበሬ በራሱ እርሻ ላይ ያሻውን ዘር ሊዘራ ይችላል፤ ከእርሱም በቀር በእርሻው ላይ ማንም አያዝም፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው እኛ በክርስቶስ ወርቀ ደም የተገዛን የእርሱ እርሻዎች ነንና የእርሱ እርሻ በሆነ ሰውነታችን እንደ ዐረምና ቋያ የሆነ ክፉ ነገርን፣ የኑፋቄና የክህደት ትምህርቶችን፣ እርሱን የሚያስክዱ ሰብዓዊነትን፣ መተባበርንና መተዛዘንን የሚያጠፉ ርዕዮተ ዓለምንና ፍልስፍና መሰል መራዥ አስተሳሰቦችን፣ የነፍሳችንን ነገር ሙሉ ለሙሉ አስለቅቀው ለሥጋችን ፈቃድ ብቻ እንድንኖር የሚገፉ ዲስኩሮችን እንዳንዘራ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ (ማቴ.፲፮÷፮፣ ፊል.፫÷፪) ሌሎች ሰዎችንም የተሳሳተ እምነት አስተሳሰብና አመለካከትን እንዲይዙ የሚያደርጋቸውን ክፉ ምክር በልቡናቸው ላይ ከመዝራት ልንቆጠብ ግድ ይለናል፡፡ ሰውን መጉዳት የእግዚአብሔርን እርሻ መጉዳት፣ ሰውን ማጎሳቆል የእግዚአብሔርን እርሻ ማጎሳቆል፣ በሰው ላይ ክፉ ምክርና አስተሳሰብን መጫንም በእግዚአብሔር እርሻ ላይ ዐረምን እንደመትከል፣ ድንጋይን እንደመቅበር እንዲሁም መርዝን እንደመርጨት ነው፡፡

እንደሚጠፉ እንስሳት አንሁን

ፈጣሬ ፍጡራን፣ ዓምጻዔ ዓለማት፣ አኃዜ ዓለማት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ የሞተለት ሰው የተሰጠውን ክብርና ጸጋ የተዋለለትን ውለታ ባለማወቁ ምክንያት ጠባዩን ባለማረቅ፣ ፈቃዱን ባለመግራት፣ ክፉ ግብርን የሙጥኝ በማለቱ ክብሩን ትቶ እንደ እንስሳት ይሆናል፡፡ ልበ አምላክ ነቢየ ዳዊት “ሰው ክቡር ፍጥረት ሆኖ ሳለ አላወቀም፡፡ ነገር ግን እንደሚጠፉ እንስሳት መሰለ” ብሎ እንደተናገረ፡፡ (መዝ.፵፰÷፲፪)

ሰው በክፉ ግብር ሲጸና፣ እግዚአብሔርን ማሰብ ሲያቅተው መንፈሳዊውን ነገር ቃለ እግዚአብሐርን መማሩን፣ ንስሓ መግባቱን ሲተው ጠባዩ ከእንስሳዊነት አልፎ አውሬያዊ ይሆናል፡፡ ነቢዩ ኤርሚያስ በሰቆቃው “ቀበሮች እንኳ ጡቶቻቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጎን ጨካች ሆነች” ብሎ በንጽጽር የተናገረው ቃል ይህንኑ ያስገነዝበናል፡፡ (ሰቆ.ኤር. ፬÷፫) ንጉሥ ናቡከደነጾር ከዙፋን ላይ ያስቀመጠው በሕዝብ ላይ ያሠለጠነው ፈጣሪው እግዚአብሔርን ረስቶ ግፍን መፈጸም ሥራዬ ባለ ጊዜ ከሰውነት ተራ ወጥቶ ከምድረ በዳ አህዮች ጋር እንዲያድር ሆኗል፤ እንደ በሬ ሣር በልቷል፤ ከሰው ልጆችም ተለይቶ ተሰዷልም፡፡ (ዳን.፭÷፳፩) ናቡከደነጾርን ለዚህ ያበቃው ትዕቢትና ዕብሪት እንዲሁም በማን አለብኝነት ይፈጽም የነበረው ግፍ ነው፡፡

ከትዳራችን ወጥተን ስናመነዝር ካለፈ ካገደመው ጋር ስንዳራ፣ በሐሰት ስንመሠክር፣ በጥንቆላና በመተት ስንተበትብና ስናስተበትብ፣ ስንሴስን ከሰውነት ወጥተን ውሾችን እንመስላቸዋለን፡፡ (ራእ.፳፪÷፲፭) በሆነው ባልሆነው ስንቆጣ፣ በቁጣችንም ሰዎችን ስናስደነግጥ፣ የሚሠሩት እንኳን እስኪጠፋቸው ድረስ ስናስደነብራቸው አናብርትን አናብስትን እንመስላቸዋለን፡፡ (መዝ.፳፩÷፲፫) ለመኖር መብላት ሲገባን ለመብላት ብቻ እንኑር ስንል፣ ለሆዳችንም ስንገዛ፣ ለሆዳችንም ተገዝተን ሃይማኖታችንን ስንክድ ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን ስናጠፋ፣ ስናበላሽ ጅቦችን እንመስላቸዋለን፡፡ (ሕዝ.፲፫÷፲፱፣ ሮሜ ፲፮÷፲፰) የተስተካከለ፣ የታረመና ወጥ በሆነ ስብዕና መጓዝ ተስኖን ጊዜያዊ ጥቅምን ለማግኘት በእምነት ስፍራዎች መንፈሳውያን ከዘማርያን ጋር እንደ ዘማርያን፣ ከቸር ሰዎች ጋር እንደ መጽዋች እያስመሰልን፣ ዘፋኞችን ስናገኝ የምንዘፍን፣ ከአመንዝሮች ጋር የምናመነዝር፣ ከሌቦች ጋር የምንሰርቅ እንዲሰርቁም የምናደፋፍር ከሆንን እስስቶችን እንመስላቸዋለን፡፡

ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት “በልባብና በልጓም ጉንጫቸውን እንደሚለጉሙአቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ” ብሎ የተናገረው ቃል ይህንኑ ያጠነክርልናል፡፡ (መዝ.፴፩÷፱) ሐሳዌ መሲሁ ሰው ሆኖ ክፉ አውሬ የተባለው በክፉ ግብሩ መሆኑን ልብ ልንል ይገባናል፡፡ (፪ኛተሰ. ፪÷፫፣ ራእ.፲፫÷፩) ዛሬ እርስ በርሳችን መዋደድ፣ መከባበር፣ ተስማምተን በአንድነት መኖር አቅቶን ወደ መበላላትና መገዳደል መድረሳችን ከሰውነት ወጥተን ወዴት እየሄድን እንደሆነ የሚያመለክተን ነገር ነው፡፡

ይቆየን!

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!!!

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት ፳፯ኛ ዕትም ፳፻፲፩ ዓ.ም.