ሰብእና

የሰው ልጅ የራሱን ህላዌና ባሕሪዩን ሲመረምር ከግዑዙና ከግሡሡ (ከሚዳሰሰው) ቁስ አካላዊ ክልል የወጣና የተለየ ፍጡር መሆኑን ያስተውላል፡፡ እርግጥ ነው፤ በዓለም ውስጥ ከምድራችን ከሚገኙት በተለመደው አባባል ከአራቱ  ባሕርያት የተፈጠረና የእነርሱም ተረጂና ተጠቃሚ ቢሆንም ከእነርሱ የበላይነት ችሎታ ስላለው ተፈጥሮውን እየተቆጣጠረ ለአገልግሎት እንዳዋላቸው እናያለን፡፡

የሰው ልጅ ሰብእናው ማለትም እኔነቱ፥ አእምሮውና ልቡናው፥ ሰብአዊነቱና ፍቅሩ፥ ስሜቱና ሌሎቹም መንፈሳዊ ጠባይዓነቱ እንደቁስ አካል ተፈጥሮ ክብደታቸው ስንት እንደሆነ በሚዛን ተመዝኖ፥ ጎናቸውና ቁመታቸው በክንድ ተለክቶ፥ ቅርጻቸውና መልካቸው በስዕልና በቀለም ተገልጾ በቤተ ሙከራ ገብቶ በልዩ ልዩ መሣሪያዎች ተመርምሮ ሊታወቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ ሰውን ሰው የሚያደርጉት የተለዩ ጠባይዓቱ ከግዑዝ ከግሡሡ ማለት ከሚታዩና ከሚዳሰሱት የተገኙ ነገሮች እንዳልሆነ ያመለክተናል፡፡ እንግዲህ ከሥጋ ባሕርይ የተለየች መንፈሳዊ ህላዌ ያላት ባለ አእምሮ ጥበብ ማስተዋልን የተጎናጸፈች ‹‹ነፍስ›› ተብላ የምትጠራው በሰው ተፈጥሮ ውስጥ እንዳለች እንገነዘባለን፡፡

እነዚህ የሚይታዩትና የማይዳሰሱት፥ የማይመዘኑትና የማይመለኩት የነፍስ ባሕርያት ከቁስ አካል ተፈጥሮ የተለዩ መሆናቸውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የእነርሱ መገኛ ምንጭ ምንድን ነው? ከቁስ አካል ተፈጥሮ ውጭ እንደሆነ የተገነዘበ ነው፡፡ የነፍስ መንፈሳዊ ህላዌና ሉዓላዊ ባሕርይ ከየት መጣ? ለተባሉት ጥያቄዎች ሰው ከአራቱ ባሕርያት ሥጋ ማለትም ከነፋስ ከእሳት ከውኃና ከመሬት ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስም ማለትም ለባዊነት፣ ነባቢትነትና ሕያውነት በሰው ተፈጥሮ ውስጥ እንደሚገኙ በሁሉ ዘንድ የታመነ ነው፡፡ የሥጋ ግን ጥያቄያችን የሚያተኩረው ሦስቱ የነፍስ ባሕርያት ማለትም የማሰብ፣ የመናገርና የሕያውነት ኅሊናው የቁስ አካል ንጥረ ነገሮች ውሕደት ውጤት ናቸው ብሎ ማመን እጅግ ያዳግታል፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር መሰሉን ዘሩን ያስገኛል እንጂ እንዴት ከባሕርዩ ውጭ የሆኑትን ነገሮች ሊያመነጭ ሊፈጥር (ሊያስገኝ) ይችላል፡፡ ስለዚህ የሰው መንፈስ በባሕርይ ከማይመስለው ከቁስ አካል ባሕርይ አይገኝም፡፡

እንግዲህ የእነዚህ መንፈሳዊ ነገሮች ሁሉ መንሥኤያቸውና መገኛቸው ከቁስ አካል ተፈጥሮ ማለት መሬት ጥንተ ነገሮች ተፈልጎ ከሌለ ግዴታ ከቁስ አካል ክልል ውጭ ከልዩ ምንጭ መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር ያለ አንዳች ምክንያት ያለ ምንም መንሥኤ እንዲሁ ወደ መኖር አይመጣምና ነው፡፡ ስለዚህ የነፍስን ባሕርያት ዓይነት የመሰሉ ባሕርያትንና መንፈሳዊያን ጠባያዓትን ሊያስገኝ የሚችል ከቁስ አካል ውጭ ከሥነ ፍጥረት ሁሉ የላቀ፣ ባሕርዩ ረቂቅ አኗኗሩ ምጡቅ የሆነ ታላቅ መንፈሳዊ ኃይል እንዳለና እንደሚኖር በሰው የተለየ ተፈጥሮ ምክንያት የተነሣ ለማመን እንችላለን፡፡ ይህም መንፈሳዊ ኃይል ከቁስ አካል የማይገኝ ልዩ ባሕርያትን ለነፍስ ያጎናጸፈ፣ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ እናምናለን፡፡

በሰው ነፍስ ባሕርያና ህላዌ መነሻነት እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እንደደረስን እንዲሁም ደግሞ በተፈጥሮ ባሕርዩ በሰው ልቡና ውስጥ በሚገኘው የኅሊና ሕግና ፍርድ መነሻነት የሕግና የፍትሕ ባለቤት የሆነው ትክክለኛ ዳኛ መኖሩን ለመገንዘብ እንችላለን፡፡ ሕግ ሳይሰጣቸው፣ የሃይማኖት መምህር ሳይኖራቸው አሕዝብ በሕገ ልቡና ክፉውንና ደጉን በመለየት የሚያሳዩት የኅሊና ፍርድ ከፍተኛ የፍትሕ ርትዕ እውቀት እንዳላቸው ያስረዳናል፡፡ የሰው ልጅ ማድረግ የሚገባውንና የማይባውን ነገር ትክክል ለይቶና አመዛዝኖ የሚያውቅበትና የሚመራበት የግብረ ገብ ሕግ በልቡናው ተጽፎ መገኘት እጅግ ያስደንቃል፡፡

ሥነ ምግባር በሰው ባሕርይ ውስጥ በሚገኘው የሞራል ግዴታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ማንም ሳያስገድደው የግል ፍላጎቱን ወደ ጎን ትቶ አንድ ሰው በበጎ ፈቃዱ ማድረግ የሚገበውን ነገር ሲያደርግ የመንፈስ ደስታና እርካት ይሰማዋል፤ የሚገባውን ሳያደርግ ሲቀር ግን ያዝናል፤ ኅሊናውም ይወቅሰዋል፤ የቁጭት ስሜትም ያድርበታል፡፡

በሕገ ልቦና ሰዎች ሁሉ ክፉውን ከደጉ፣ ስሕተቱን ከትክክለኛው፣ የሚገባውን ከማይገባው ነገር ለይቶ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚያስረዳን ሕግ እንደ ተሰጣቸው፣ ነቢያት እንደ ተኩላቸው፣ እንደ ቤተ እስራኤል የሕግ ትእዛዛት ሳይኖራቸው አሕዛብ ‹‹ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ›› ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ አሕዛብ ‹‹ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ኅሊናቸውም ሲመሰክርላቸው ሀሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰሱ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያያሉ፡፡›› በሰው ልቡና በሚገኘው የሥነ ምግባር ሕግ መነሻነት የሀልዎተ እግዚአብሔርን ፍትሐዊነት (ጽድቅና ርትዕ) እንጂ ከሌላ ምንጭ ስለማይገኝ ነው፡፡ በዚህም ሆነ በሌላ፣ ሰው ሁል ጊዜ በአርአያው የፈጠረውን የእግዚአብሔርን ጠባይነት በትክክለኛው ሥራውና በመንፈሳዊ ሕይወቱ ሲያንጸባርቁ ይታያል፡፡

ሥነ ፍጥረት ውበትና መልካምነት፣ የሰው ነፍስ ባሕርያት አስደናቂነት ሌሎችም ዓላማና ትርጉም ያላቸው የተፈጥሮ ሥርዓቶችና ክሥተቶች ሁሉ የመለኮታዊ ጥበብ አሠራርን ያመልክታሉ፡፡

ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ በሕገ ልቡና በምርምር ፈጣሪውን የመፈለጉና በአምልኮት እግዚአብሔር የመኖሩ እውነት በአባታችን አብርሃም ታሪክ ተመስክሯል፡፡ ጻድቁ አብርሃም በእምነት ፍጡራንና ፈጣሪ፣ ፍጥረትና ግዑዝ ተለይቶ በማይታወቅበት የጨለማ ዘመን አምላኩ እግዚአብሔርን በልቡናው ሽቶ እና ተመራምሮ ያገኘ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔርም አብርሃምን ባረከው፤ እርሱም በአምልኮተ እግዚአብሔር እስከ ዕለተ ዕረፍቱ ኖሯል፡፡

ሰዎች ሰብእናችን በበጎ ምግባር ይታነጽ ዘንድ የሥጋም ሆነ የነፍስ ባሕርያትን ልንረዳ ይገባል፡፡የተፈጠርንበትን ምክንያትም አውቀን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መኖርና በሃይማኖት መጽናት አለብን፤ ያም ለተዘጋጀልን ሰማያዊ ርስት ያበቃናል፡፡

ምንጭ፡ ‹‹የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም›› በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ