ሥጋዌ – የድኅነት ቍልፍ – ክፍል ሁለት

በመምህር ፀሐዬ ዳዲማስ

ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በምስጋናው ብርሃን ያበራው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ነገረ ሥጋዌ ከሰው ልጆች ድኅነት ጋር ያለውን ቍርኝነት ጥልቅ ምሥጢር ባለው በመጽሐፈ ድጓ ድርሰቱ ጽፎልን እናነበዋለን። ቅዱስ ያሬድ በምስጋናው አንሥቶ ከማይጠግባቸው ምስጋናዎች መካከል የአምላክ ሥጋዌ (ሰው መኾን) እና ነገረ ስቅለት ቀዳሚዎች ሲኾኑ የሚያነሣቸውም ከነገረ ድኅነት ጋር በተያያዘ ምሥጢር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎችን የማዳን ተግባራት ከሚመለከቱ ድርሰቶቹ መካከል ለአብነት የሚከተለውን ትምህርት መጥቀስ እንችላለን፤

‹‹ዘዲበ ኪሩቤል ይነብር ወበአርያም ይሴባሕ እምሰማያት እምልዑላን ወረደ አምላክ ያድኅን ዓለመ መጽአ ይክሥት ብርሃነ ይናዝዝ ኅዙናነ ወልድ ተወልደ ለነ ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ውእቱኬ ወልደ አምላክ ውእቱ ወልድ ዋሕድ ውእቱ፤ በኪሩቤል ላይ የሚኖር በአርያምም የሚመሰገን ከሰማያት ከልዑላን ወረደ፤ አምላክ ዓለምን ያድን ዘንድ መጣ፤ ብርሃንን ይገልጥ ዘንድ፣ ያዘኑትን ያጽናና ዘንድ፣ [እግዚአብሔር] ወልድ ተወለደልን፡፡ ለሰዎች ዕረፍትም ሰንበትን ሠራ፤ እሱም የአምላክ ልጅ ነው፡፡ [እሱም] በተዋሕዶ የከበረ [እግዚአብሔር] ወልድ ነው፤›› (ድጓ ዘዘመነ ልደት)፡፡

እነዚህ የቅዱስ ያሬድ የምስጋና ቃላት እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ለብሶ ሰው መኾኑን ከማስረዳታቸውም ባሻገር እግዚአብሔር አምላካችን ሰው በመኾኑ የሰው ልጆች ያገኙትን ጥቅምም የሚያስረግጡ ናቸው። ዘማሪው አምላክ ወልደ አምላክ ዓለምን ያድን፣ ብርሃንን ይገልጥ፣ ያዘኑትንም ያጽናና ዘንድ ከሰማያት እንደ ወረደ እና ወደ ዓለም ወይም ወደ ሰዎች እንደ መጣ ሲነግረን የተለያዩ ጽጌያትን እንደሚቀስም ንብ መጽሐፍ ቅዱስን በማጣቀስ እንደ ኾነ ስንረዳም የአበው ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮን ልብ እንድንል ያስችለናል።

እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን ወደ ዓለም የላከው ዓለም በልጁ እንዲድን እንደ ኾነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ትምህርት ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ጽፎልናል (ዮሐ. ፫፥፲፮)። የነቢያት ትንቢት በክርስቶስ መፈጸሙን ደጋግሞ በማውሳት የሚታወቀው ሐዋርያው እና ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢት በሥግው ቃል በክርስቶስ እንደ ተፈጸመ በሚያስረዳ የወንጌሉ ክፍል ‹‹‹በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው› የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ኾነ›› በማለት ጽፏል (ማቴ. ፬፥፲፬-፲፮ ኢሳ. ፱፥፪)።

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም በተመሳሳይ መልኩ የነቢዩን የኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ ክርስቶስ በዘመነ ስብከቱ ስለ ራሱ እና ሰው ስለ ኾነበት ምክንያት ሲያስረዳ የተናገረውን ‹‹የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፤ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ ‹የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፤ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፤ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል› ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ዅሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም ‹ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ› ይላቸው ጀመር፤›› (ሉቃ. ፬፥፲፯-፳፩) በማለት ትንቢቱ መፈጸሙን ተናግሯል።

የነቢዩን ቃላት በምልአት ስንመለከታቸው ‹‹የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፤ ለተማረኩትም ነፃነትን፣ ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት፣ አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፤ የሚያለቅሱትንም ዅሉ አጽናና ዘንድ፤ እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፤ በአመድ ፋንታ አክሊልን፣ በልቅሶም ፋንታ የደስታ ዘይትን፤በኀዘን መንፈስ ፋንታም የምስጋና መጐናጸፊያን እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል፤›› የሚሉ ናቸው (ኢሳ. ፷፩፥፩)።

እነዚህን አጠቃልሎ ቅዱስ ያሬድ ድኅነተ ሰብእን ሲያመለክት ‹‹ዓለምን ያድን ዘንድ መጣ፡፡ብርሃንን ይገልጥ ዘንድ፤ ያዘኑትን ያጽናና ዘንድ፤ [እግዚአብሔር] ወልድ ተወለደልን፤›› በማለት በዝማሬ አመሰገነ። እግዚአብሔር የሰውን ሥጋ ለብሶ ሰውን ያድን ዘንድ ያስገደደው የገዛ ባሕርዩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ወደ ዓለም የመጣበትን ምክንያት ብዙ ሊቃውንት በብዙ መንገድ ጽፈዋል። አንዳንዶቹም የማይረገጠውን ረግጠው በድፍረት ‹‹መጽአ በኵርሕ፣ ተገዶ መጣ›› ብለው እስከ ማስተማር በመድረሳቸው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለይተዋል። ፍጹማን የኾኑት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ግን እግዚአብሔር የሰው ልጆችን እንዲያድን ያደረገው ባሕርዩ እንደ ኾነ በምስጋና ድርሰቶቻቸው ጽፈውልናል።

ቅዱስ ያሬድ በበዐለ ኖላዊ ሳምንት በሚደርሰው የድጓ ድርሰቱ ‹‹አናኅስዮ አበሳነ አፍቂሮ ኪያነ ፈነወ ለነ ወልዶ መድኅነ፣ በደላችንን ይቅር ብሎ እኛን ወዶ አዳኝ ልጁን ወደኛ ሰደደልን፤›› በማለት ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው እኛን ለማዳን መኾኑን ነግሮናል። ሊቁ በዚህ ድርሰቱ እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድን ለድኅነት ወደ እኛ ወደ ሰዎች የላከልን በይቅር ባይ እና ፍቅርን መሠረት ባደረገው ባሕርዩ እንደ ኾነ ያስረዳል። እጅግ ጥልቅ በኾነ ምሥጢር ነገረ ድኅነትን የሚገልጠውን ሌላኛውን የቅዱስ ያሬድን ምስጋና እናንሣ፤ ‹‹ይእዜኒ ንትልዋ ለሰላም እስመ ተወልደ ክርስቶስ ዮም በሀገረ ዳዊት አናኅስዮ አበሳነ ወልዱ ለአብ ቀዳሜ በኵሩ ኃይሉ ለአብ መጽአ ኀቤነ ይክሥት ብርሃነ ተመሲሎ ኪያነ ሰብአ ዘይከውን ኵሎ ኮነ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ፤›› (ድጓ ዘዘመነ ልደት)፡፡ ትርጕሙም፡- ‹‹እንግዲህማ ሰላምን እንከተላት፤ ዛሬ ክርስቶስ በዳዊት አገር ተወልዷልና፡፡ በደላችንን ይቅር ብሎ የአብ አንድያ ልጁ፣ የአብ ኃይሉ፣ ወደ እኛ መጣ፤ ብርሃንን ይገልጥ ዘንድ፣ እንደ እኛ ሰው ኾነ፡፡ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር ሰው የሚኾነውን ዅሉ ኾነ፤›› ማለት ነው፡፡

ከዚህ የምስጋና ክፍል እንደምንረዳው የጌታችን ልደት የሰላም ምንጭ መኾኑን ነው። ይህ ሰላም ደግሞ ዓለም የምትሰጠው ሰላም አይደለም፤ ድኅነተ ሰብእን የሚያሳይ ሰላም፤ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ልዩነት ተወግዶ ዕርቅ መመሥረቱን የሚያሳይ ሰላም ነው እንጂ። በክርስቶስ ልደት ለዓለም የተሰጠው ሰላም ደግሞ የሚሠራው ሰዎች ዅሉ ሲሹትና ሲከተሉት ነውና ‹‹ንትልዋ ለሰላም›› እያለ በረጅሙ ይሰብካል። ለዚህም ነው መላእክቱ ከእረኞቹ መካከል ተገኝተው፣ ከሰዎች ጋር በአንድነት ኾነው በአዲስ ምስጋና ሲያመሰግኑ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን! ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ፤›› በማለት የዘመሩት (ሉቃ. ፪፥፲፬)።

ይቆየን