ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቀ ጉባኤ በወሊሶ ተካሄደ።

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

መጋቢት 1፣ 2003 ዓ.ም

በምዕራብ ሸዋ ሃገረ ስብከት በወሊሶ ከተማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ሥርዓትና ቀኖና ውጪ የሆነ ጉባኤ ተካሄደ።

ከየካቲት 25 እስከ 27፣ 2003 ዓ.ም ባሉት ቀናት የተካሄደው ጉባኤ ምእመናንን ለመጠበቅና ለማጽናት በ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጥሪ የተዘጋጀ ቢሆንም በጉባኤው ማለቂያ ቀን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በዐቢይ ፆም መዝሙር በከበሮና በጭብጨባ ሊቀ ጳጳሱ በተገኙበት ሲዘመር እንደነበር ታውቋል።
ከማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ “በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በዐቢይ ፆም ማኅሌት አይቆምም፣ ከበሮ አይመታም፣ ጸናጽል አይንሿሿም፣ እልልታም የለም። ስብሐተ እግዚአብሔር የሚደርሰውም በዘንግ /በመቋሚያ/ ብቻ ነው፤ በዝማሜ። የሚቆመውም ፆመ ድጓና የፆም ምዕራፍ ነው።” በማለት ሥርዓቱን ያብራራሉ።
እሑድም ቢሆን የመወድስ አደራረስ እንዳለና ቅኔም በየምዕራፉ እንደሚደረግ፥ ማኅሌት ግን እንደማይቆም፣ ከበሮም እንደማይመታ ጨምረው ያስረዳሉ።
በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት በዐቢይ ፆም መሐል ከሚውሉ ክብረ በዓላት ውጭ ማኅሌት መቆም፣ ከበሮ መምታትና ማጨብጨብ እና ሌሎች ደስታን የሚፈጥሩ ነገሮችን ማድረግ ክልክል ነው።
ይህንንም ብያኔ ለማሻሻል የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ መሆኑን የሚገልጹት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አንድ ሀገረ ስብከት በተናጠል ሥርዓት መለወጥ እንደማይችልም አስረግጠው ይናገራሉ።
በጉባኤው የነበሩ በርካታ ምእመናን በነበረው የሥርዓት መፋለስ ማዘናቸውንና በጉባኤው ላይ የተሰጡ ትምህርቶችም ብቁ ያልነበሩና የታለመውን ግብ ይመታሉ ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።