ሞክሼ ፊደላት

 

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ሞክሼ ማለት ተመሳሳይ ስያሜ ኖሮት ተመሳሳይ ትርጉም ሲያስተላልፍ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአንድ ቋንቋ ውስጥ ሁለት የተለያዩ ምልክቶች በአንድ ድምፅ እየተጠሩ የትርጉም ለውጥ የማያመጡ ከሆነ ሞክሼ (ዘረ ድምፅ) ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዘረ ድምፅ የሚባለው አንድ ድምፅ ከሌላ ድምፅ ጋር በተመሳሳይ ስያሜ እየተጠራ ነገር ግን የፍች ለውጥ የማያመጣ ከሆነ አንዱ ለሌላኛው ዘረ ድምፅ ይባላል፡፡ ለምሳሌ በአማርኛ ቋምቋ በድምፅ ቁጥር ውስጥ የሚጠናው “ህ” ሲሆን ሌሎች በተመሳሳይ ስያሜ የሚጠሩ “ሕ” እና “ኅ” አሉ እነዚህ በአማርኛ ቋንቋ ዘረ ደምፅ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ምክንያቱም የፍች ለውጥ ስለማያመጡ ነው፡፡

የቋንቋ ምሁራን የግእዝ ሞክሼ ፊደላትን በተመለከተ የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡

የሞክሼነትን ሁኔታ ከላይ በገለጽነው መሠረት አንድ ድምፅ በቅርጽ፣ በድምፅ፣ የሚለይ ከሆነና የፍች ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ዘረ ድምፅ ሊባል አይችልም፡፡ በግእዝ ቋንቋ ሞክሼ ፊደል የለም የሚሉት ምሁራን ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ ምክንያቱም በግእዝ ቋንቋ ተመሳሳይ ድምፅ፣ ተመሳሳይ ፍች፣ ተመሳሳይ ቅርጽ ያለው ድምፅ (ፊደል) ስለሌለ ነው፡፡ ይህ ሲባል ሀ፣ ሐ እና ኀ፣ ሰ እና ሠ፣ ጸ እና ፀ በተመሳሳይ ድምፅ ይጠሩ የለም የሚል ጥያቄ ቢነሳ ከጊዜ በኋላ ድምፀታቸውን አጥተው ነው እንጂ ተመሳሳይ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የሚፈጠሩበት ቦታ ( መካነ ፍጥረት)፣ ድምፆቹ ሲፈጠሩ በመካነ ፍጥረታቸው በሚያሳዩት ባሕርያት (ባሕርየ ፍጥረት)፣ እና የንዝረት ሁኔታ ማለትም በነዛሪነትና ኢ ነዛሪነት የተለያዩ እንደነበሩ ልብ ማለት ይገባል፡፡

ይህን ሐሳብ በአጽንዖት ከሚያስረዱን ምሁራን መካከል አንዱ መምህር ዘርዐ ዳዊት አድሐና እንደገለጹት ሐሳባቸውን እንደሚከተለው እንጥቀስ “በልሳነ ግእዝ ውስጥ ፊደል የሌለው ድምፅ፣ ድምፅ የሌለው ፊደል የለም፡፡ ወይም የተዳበለ ሞክሼ ፊደልና ድምፅ የለም፡፡  እያንዳንዱ ፊደለ ግእዝ የየራሱ ድምፅ አለው፡፡ ይሁን እንጂ “የሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ አ፣ ዐ፣ ሠ፣ ሰ፣ ጸ፣ ፀ ፊደላት ድምፃቸው ተዘንግቷል፡፡” ይሉንና የታሪክ ምሁራን ከሆኑት መካከል አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስን (፲፱፻፵፰) መጽሔተ ጥበብ ስለ ግእዝና አማርኛ ቋንቋ ታሪክ በሚል የጻፉትን በመጥቀስ የእነዚህ ፊደላት ድምፆች እስከ ፲፭፻፴ ዓ.ም ድረስ ማለትም እስከ ዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ድረስ የእነዚህ ፊደላት ድምፅ ተለይቶ ሲነገር እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ (ልሳናተ ሴም ገጽ፲፭)፡፡

በመሆኑም ዛሬ ላይ ድምፀታቸውን አጥተው በተመሳሳይ ድምፅ እየተጠሩ ስለሆነ ሞክሼ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ተመሳሳይ ድምፅ ስላላቸው ሞክሼ ግን ሊባሉ አይችሉም፡፡ ሞክሼ ፊደላት (ድምፅ) የምናገኘው በአማርኛ ቋንቋ እንጂ በግእዝ አይደለም፡፡ አማርኛ የድምፅ ሥርዓቱን ከግእዝ ሲዋስ በመካነ ፍጥረትና በባሕርየ ፍጥረት የተለያዩ ሆነው የየራሳቸው ንጥረ ድምፆች የነበሩትን፣ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ድምፀታቸውን ያጡትን ድምፆች ከነጠፋ ድምፃቸው ተውሷቸዋል፡፡ የፍች ሥርዓታቸውንም ትቶ እንዲሁ ከንጥረ ድምፆቹ ጋር በዘረ ድምፅነት እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡

ከላይ እንደገለጽነው በግእዝ ቋንቋ ድምፀታቸውን ቢያጡም ማለትም መካነ ፍጥረታቸው፣ ባሕርየ ፍጥረታቸው፣ የንዝረት ሁኔታቸውን አጥተው በተመሳሳይ ድምፅ ቢጠሩም የፍች ለውጥ ያመጣሉ፡፡ በቋንቋ ጥናት ደግሞ የፍች ለውጥ ካመጣ ሞክሼ (ዘረ ድምፅ) አይባልም፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለጸው አገባብ ከሆነ በግእዝ ቋንቋ ሞክሼ ድምፅ የለም የሚለውን ሐሳብ እንድናጸና እንገደዳለን፡፡

ነገር ግን በተመሳሳይ ድምፀት በመጠራታቸው ሰዎች በጽሑፍ ሥርዓት ላይ አንዱን በአንዱ ቦታ እያቀያየሩ ይጽፏቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ስሕተቶች ይፈጠራሉ፡፡ በርከት ያሉ ምሳሌዎችን እያነሳን ስሕተቶችንም ለማሳየት እንሞክራለን፡፡

ቃል               ፍች/ትርጉም

በርሀ            ብርሃን ሆነ

በርሐ            በራ ሆነ

ሠረቀ            ወጣ፣ ተወለደ

ሰረቀ             ሰረቀ

ኀለየ             አሰበ

ሐለየ             ዘፈነ

ኀመየ            አሰረ፣ ቀፈደ

ሐመየ            አማ

ሀደመ            አንቀላፋ

ሐደመ            አወጋ፣ ተረተ

ፈፀመ            ዘጋ፣ አሰረ

ፈጸመ            ጨረሰ

ከላይ የተዘረዘሩት በትክክለኛው አጻጻፍ የተቀመጡት ሲሆኑ የፊደላቱ መቀያየር ሊሰጠን የሚችለው ፍች እኛ ልናስተላልፈው ከፈለግነው የተገለበጠ ይሆናል፡፡

ለምሳሌ ሠረቀ በሥጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ፣ ወአድኃነነ በሚለው ላይ ሰረቀ በሥጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ ወአድኃነነ ብለን ብንጽፍ የምናገኘው ፍች፣ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር በሥጋ ተወልደና አዳነን የሚለውን ሳይሆን፤ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር በሥጋ ሰረቀና አዳንን የሚለውን ይሆናል፡፡ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር መወለዱን ሳይሆን ሌብነትን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ይህንንስ አይሁድም አላሉት የተባለውን ነገር ይፈጠርብናል፡፡ የአንዲት ፊደል መለወጥ ይህን ያህል ስሕተት ትፈጥርብናለች፡፡

ሌላም ምሳሌ እናንሳ፡፡  ፈፀመ፣ ነጨ፣ አሰረ በሚለው ቦታ ፈጸመ የሚለውን “ጸ” ለመጠቀም ብንፈልግ የሚሰጠን ፍች እኛ ካሰብነው የተለየ ይሆናል፡፡ በምሳሌ ቢቀመጥ “ኦ ባዕል ሶበ ታከይድ እክለከ ኢትፍፅሞ አፉሁ ለብዕራይከ፤ እህልህን በምታበራይበት ጊዜ በሬውን አፉን አትሰረው፣ ለሚሠራ ደሞዙ ይገባዋልና” (፩ጢሞ.፭፣፲፰) በሚለው ቦታ ኢትፍጽሞ አፉሁ የሚለውን ብንጠቀም የምናገኘው ፍች ባለጸጋ ሆይ እህልህን በምታበራይበት ጊዜ የበሬህን አፉን አታፍነው የሚለውን ሳይሆን የበሬህን አፉን አትጨርሰው የሚለውን ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ የግእዝ ቋንቋ ፊደላት እያንዳንዳቸው ሀልዎተ እግዚአብሔርን የሚያስረዱ፣ ሥርዓተ አምልኮን የሚያሳውቁ፣ የየራሳቸው ጥልቅ መልእክትን የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ እንዲሁም ፊደላቱ መግባት በሌለባቸው ቦታ ሲገቡም የሚፈጠረው ስሕተት የዚያን ያህል እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም የፊደላቱን ትርጉም ጠንቅቀን አውቀን በየራሳቸው ቦታ እንድንጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ይገልጽልን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡ ይቆየን