ምኲራብ

መጋቢት 18ቀን 2005 ዓ.ም.

በዳዊትደስታ

የዐብይ ጾም ሦስተኛው ሰንበት ምኲራብ ይባላል፡፡ ይህም ምኲራብ ከክርስቶስ ልደት በፊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የእግዚአብሔር አማኞች ለጸሎት የሚሰባሰቡበት ቤት ስም ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ወደ ምኲራባቸው በመግባት ሰዎችን አስተምሯል፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔር መመስገኛ የሆነውን ምኲራብ ገበያ አድርገውት ስላገኘም “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፏል እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” /ማቴ.21፥12-13/ በማለት ገሥጾ በዚያ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ሁሉ በትኗቸዋል፡፡ ይህንን ምክንያት በማድረግ ሦስተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ምኩራብ በሚል ሰያሜ ይጠራል፡፡ በምኲራብ ገብቶ እንዳስተማረ የሚያሳስብ ዕለት የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ዮሐ.12 እስከ ፍጻሜው ያለው ነው፡፡

ቅድመታሪክ
ስለምኲራብ /ሲናጎግ/
ምኲራብ ማለት የአይሁድ የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና እንደ ሥርዓቱ የተመሠረተ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ መቀጠል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት የሚያጠፋ ቤተ መቅደስ የሚያፈርስና የሚያቃጥል አረማዊ ንጉሥ ተነሣ፡፡ 

አረማዊው ንጉሥ ናቡከደነጾር ቤተ መቅደሱን አፍርሶ ሕዝበ እስራኤልን ወደ ባቢሎን አፍልሶ ስለነበር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አይሁዶች በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎትና በማኅበር ለማመስገን ቤቶችን ሊሠሩ እንደጀመሩ ይነገርላቸዋል ሕዝ.11፥16፡፡

በምኩራቦችም የብሉይ ኪዳን ማምለኪያ አምልኮታቸውን ይፈጽሙ ስለነበረና ምኲራቦቻቸውም ብዙ ስለ ነበሩ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋዌ ምስጢር ተገልጾ በተዋሕዶ ከብሮ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜም ተከታዮቹን ሐዋርያትን እየላከ በምኲራቦቻቸው ያስተምራቸው ነበር፡፡ /ማቴ.4፥23፣ ሐዋ.6፥9፣ 13፥5፣ 14፥1፣ 17፥16-18/፡፡ በብሉይ ኪዳን ታሪክና ለአይሁዳውያን ሕግ አሥር የሚያህሉ ወንዶች በአንድ ማኅበር ቢገኙ ምኲራብ ለመሥራት ይፈቀድላቸዋል፡፡ እንዲሁም በሚያንጹት ምኲራብ ውስጥ ሕግና ነቢያት የተጻፈባቸው የብር ጥቅልሎች /Scroll/ በአንድ ሳጥን ወይም ማኅደር ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ /ፅላትበታቦት፣ ዳዊት በማኅደር እንደሚቀመጥ/ ማለትነው፡፡ ምኲራብ እንደ ደብተራ ኦሪት ሁሉ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጽምበት ሕንፃ ነው፡፡