ምሥጢረ ጥምቀት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ  

ግንቦት ፲፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? የትንሣኤ በዓል እንዴት ነበር? ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በማስቀደስ አከበራችሁተ አይደል! የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በዓል የደስታ በዓላችን ነው! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሠረት እስከ በዓለ ሃምሣ (ጰራቅሊጦስ) ይታሰባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሰንበት ትምህርት ቤት በመግባትም ተማሩ አገልግሉ፤ በቤተ እግዚአብሔር ማደግ መታደል ነውና! ሌላው ደግሞ በዘመናዊ ትምህርታችሁም በርቱ! ሁለተኛው የመንፈቀ ዓመት ትምህርት እየተገባደደ ስለሆነ በተማራችሁት መሠረትም ስለምትፈተኑ በርትታችሁ ማጥናት አለባችሁ፡፡ መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ፤ ባለፈው ምሥጢረ ሥጋዌን ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ  ምሥጢረ ጥምቀትን እንማራለን፤ ተከታተሉን!

ጥምቀት የሚለውን ቃል ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ባዘጋጁት መዝገበ ቃላት ላይ እንዲህ ያብራሩታል፤ “ማጥመቅ፣ አጠማመቅ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ሥራ (በጥሩ ውኃ)፣ በጸበል የሚፈጸም” (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፭፻፫) ጥምቀትን እንጠመቅ ዘንድ ያዘዘንና ሥርዓቱንም የሠራልን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለእኛ አብነት ሊሆነን ጌታችን ከቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዘንድ በመሄድ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ሥርዓትን ሠራልን፤ እንደገናም በትምህርቱ ‹‹ …ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንገሥት ሊገባ አይችልም…፡፡›› በማለት ለኒቆዲሞስ ባስተማረው ትምህርቱ ገልጦልናል፡፡ (ዮሐ.፫፥፭)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጥምቀት በብሉይ ኪዳን በብዙ ምሳሌ ስትነገር ስትመሰል ነበር፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ሥርዓቱን ሠራልን፡፡ ለእኛ አርአያ በመሆን ከተጠመቀ በኋላ መጠመቅ እንደሚገባን ደግሞ አስተማረን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና እኛ የምንጠመቀው ጥምቀት ልዩነት አለው፤ እስኪ ጌታችን ለምን ተጠመቀ የሚለውን በመጠኑ እንመልከት፤ ከዚያ ደግሞ እኛ ለምን እንደምንጠመቅ እንመለከታለን፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ምክንያት

  • ለእኛ አርአያ ለመሆን፡- ጌታችን እንፈጽማቸው ዘንድ ያዘዘንን እርሱም እየፈጸመ አሳይቶናል፤ ተጠመቁ ሲለን ቅድሚያ ተጠምቆ አሳይቶናል፤ ትሕትናውንም ሊያስተምረን ከመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ በመሄድ ተጠመቀ፡።
  • ትንቢቱን ለመፈጸም፡- ጌታችን በውኃ እንደሚጠመቅ ትንቢት ተነግሮ ነበር፤ ከትንቢቶችም መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ አቤቱ ውኆች አዩሁ ውኆች አይተው ፈሩ፤ የውኆች ጥልቆች ተነዋወጡ፤ ውኆታቸውም ጮኹ፤ ደመናት ድምጽን ሰጡ..፡፡›› (መዝ.፸፮፥፲፮) በመሆኑም ጌታችን እንደሚጠመቅ በሚጠመቅበትም ጊዜ ድንቅ ተአምር እንደሚደረግ ትንቢት ተነግሮ ስለነበር፤ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ተጠመቀ፡፡
  • የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፡- በምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርታችን ላይ እንደተማርነው አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን በበሉና ከገነት በተባረሩ ጊዜ ጠላት ሰይጣን ‹‹ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ፤ አዳም የዲያብሎስ ባርያው ሔዋን የዲያብሎስ ገረዱ›› የሚል የዕዳ ደብዳቤ አጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ ወንዝ አንዱን ደግሞ በሲዖል ውስጥ ደብቆት ነበር፤ ጌታችን የዕዳ ደብዳቤያችን በተደበቀበት ዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ ያንን የዕዳችንን ጽሕፈት ደመሰሰልን፡፡ ‹‹…በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው…›› እንዲል፡፡ (ቆላ.፪፥፲፫)
  • የሦስትነቱን ምሥጢር ሊገልጥልን፡- በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርታችን ላይ ቅድስት ሥላሴ አንድም ሦስትም እንደሆኑ ተምረናል፤ ሦስትነታቸው በስም፣ በአካል፣ በግብር ነው፤ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ የቅድስት ሥላሴ ሦስትነት ተገለጠ፤ ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊው እንዲህ በማለት ጽፎልናል፤ ‹‹…ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም ድምጽ ከሰማይ መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ…፡፡›› (ማቴ.፫፥፲፮-፲፯) በሰው ዘንድ ስውር የነበረው ምሥጢረ ሥላሴ ተገለጠ፤ እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ መሠከረ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወረደ፤ በዚህም ምሥጢረ ሥላሴን ገለጠልን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት ምክንያት ይህ ነው፤እኛ ለምን እንደምንጠመቅ ደግሞ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

  • የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን፤ ጌታችን ለአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹..ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው…›› በማለት እንዳዘዛቸው ከእርሱ ልጅነትን ለማግኘት በክርስትና ስም ልንጠራና የመንግሥተ ሰማያት ልጆች (ወራሾች) ለመሆን እንጠመቃለን፡፡ (ማቴ.፳፰፥፲፱)
  • በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታላቅ ስም ክርስቲያን ተብለን እንጠራለን፤ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን፤ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ‹‹…ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ…›› በማለት እንዳስተማረው የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበትን  ዳግም ልደትን እንወለዳለን፡፡ (፩ጴጥ.፩፥፳፫) ንጽሕናና ቅድስናን እናገኛለን፤ ጌታችንን ሕጉን በመፈጸም እንመስለዋለን፤ አርአያውን ተከትለን በጥምቀት አዲስ ሕይወትን አግንተን መንግሥቱን እንወርሳለን፡፡
  • የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን፡- ስንጠመቅ ክርስቲያን ተብለን ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተካፋዮች እንሆናለን፤ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሕዝቦች የአብርሃም ልጆች የሚባሉትና በእግዚአብሔር የሚያምኑት የሚለዩት በመገዘራቸው ነበር፤ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ክርስቲያን ተሰኝተን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን እንጠመቃለን፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እጅግ ጥልቅና ሰፊ ከሆነው ከምሥጢረ ጥምቀት ትምህርት በመጠኑ ተመልክተናል፤ አምላካችን ለምን እንደተጠመቀ እኛ ለምን እንደምንጠመቅ በመጠኑ ተማርን፤ የጥምቀት በዓል ብለን በየዓመቱ ጥር ፲፩ (ዐሥራ አንድ) ቀን የምናከብረው ጌታችን የተጠመቀበትን በዓል ነው፡፡ በቀጣይ ስለ ሰዎች ልጆች አጠማመቅ ሥርዓትና በተወለድን በስንት ቀናችን እንደምንጠመቅ እንማራለን፤ ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!